97797 contract/ contract of sale/

አንድ የሽያጭ ውል የእጅ በእጅ ሽያጭ ውል ነው ለማለት ስለሚቻልበት አግባብ የፍ/ብ/ሕ/ አንቀጽ 2278(1)

የሰ//.97797 መስከረም 28/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡-ተገኔ ጌታነህ

 

ተሻገር ገ/ስለሴ ብርሃኑ አመነው ሸምሱ ሲርጋጋ አብረሃ መሰለ

አመልካች፡- ናሽናል ስሚንቶ አ/ማህበር አልቀረቡም

 

ተጠሪ፡- አቶ ብርሃኑ ግደይ   ጠበቃ አቶ በላቸው ዘመድኩን ቀረቡ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የሽያጭ ውል አፈፃፀም የተመለከተ ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ የአሁን ተጠሪ ነው፡፡ የክሱም ይዘት ከአመልካች ጋር መጋቢት 30 ቀን 2003 ዓ/ም በተደረገ የሽያጭ ውል ስምንት ሺህ ኩንታል (8000) ስሚንቶ የአንዱ ኩንታል ብር 255.41 ሂሣብ ቫት እና ታርንኦቫር ታክስ ጨምሮ ነው 2,360,000 (ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ስልሣ ሺህ) መክፈሉን እና አመልካች (ሸጭ) 7272 ኩንታል ሲምንቶ ካሰረከበ በኃላ 723 ኩንታል ስሚንቶ ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ይህንኑ ቀሪ ስሚንቶ ተገዶ እንዲያሰረክብ አለያም ዋጋውን ብር 214. 760 እንዲከፍል እንዲወሰን ጠይቋል በአመልካች በኩል የቀረበው ክርክር የዋጋ ለውጥ ሊደረግ እንደሚቻል አስቀድሞ መስማማታቸው በዚሁም መሠረት በየጊዜው የዋጋ ለውጥ ሲደረግ እንደነበርና ተጠሪም ይህንኑ አውቆ ሲረከብ እንደነበረ ገልጾ አጠቃላይ እስከ አሁን የተረከበው በየጊዜው ከነበረው ዋጋ ለውጥ አንፃር ተሰልቶ ቀሪ ብር 120 (አንድ መቶ ሃያ ብር) ብቻ መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ እንድደረግ ጠይቋል፡፡

 

ጉዳዩ በመጀመሪያ የዳኝነት ሥልጣን ያከራከረው የፌዴራል የመ/ደረጃ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከመረመረ በኃላ የስሚንቶ ዋጋ ለውጥ ወይም ጭማሪ መደረጉን የተጠሪ (የከሳሽ) ወኪል ያውቃል እንዲሁም ለተጠሪም አሳውቋል ዋጋ ጭማሪ የተደረገውም በስምምነታቸው    መሠረት


ነው በማለት ተጠሪ የተረከበው ሲምንቶ ሲሳላ የተከፈው ዋጋ ጋር ተቻችሏል ቀሪ ብር 120 (አንድ መቶ ሃያ ብቻ) ነው ሲል ክሱ ውድቅ አድርጓል፡፡

 

ይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ በግራ ቀኙ መካከል የተደረገው የሽያጭ ውል የእጅ በእጅ የሽያጭ ውል ነው በሚል ምክንያት የፍ/ብ/ሕጉን አንቀጽ 2278(1) በመጥቀስ የዋጋ ጭማሪ የማድረግ መብት የለውም በማለት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ቀሪውን ስሚንቶ ያስረክብ ወይም ዋጋውን ይመልስ በማለት ወስኗል፡፡ አመልካች ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት አለገኘም፡፡

 

ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ የቀረበው በዚህ ላይ ሲሆን የሰበር አመልካች አቤቱታ ተመርምሮ በግራ ቀኙ መካከል ውል ከተደረገበት ንብረት መጠን አኳያ የሽያጭ ውሉ የእጅ በእጅ የሽያጭ ውል ነው ማለት ይቻላል ወይስ አይችልም? የዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ ተጠሪ ስምምነት አልሰጠም የሚልውን አግበብነቱን ለመመርመር ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

 

የተጠሪ ጠበቃ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት የለውም በአግባቡ ነው በማለት ተከረክሯል፡፡ የጉዳዩ አመጠጥና የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተገለፀ ሲሆን እኛም ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ከህጉ ጋር አገናዝበናል፡፡ ከመዝገቡ መገንዘብ እንደተቻለው በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የተነሳው ክርክር መሠረቱ መጋቢት 30 ቀን 2003 ዓ/ም የተደረገ ውል ነው፡፡ በዚህ የሽያጭ ውል ላይ የ8000 ኩንታል ስሚንቶ ዋጋ ተጠሪ ብር 2,360,000 መክፈሉም ተረጋግጧል፡፡ የስሚንቶ ርክክብ አፈፃፀም በተለያየ መጠን በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀመ ሲሆን በጥቅሉ ከ6 ወራት ያላነሰ ጊዜ ወስዷል፡፡ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል በተደረገ ውል ክፍያ የተፈፀመበት ደርሰኝ (ሰነድ) የእጅ በእጅ ሽያጭ የሚል ሲሆን በፍ/ብ/ሕጉ አንቀጽ 2278(1) በሚደነግገው አግባብ ይህ ውል የእጅ በእጅ ሽያጭ ውል ይሰኛል ወይ የሚለው ነጥብ ምለሽ የሚያሸው ሆኖ አግኝተናል፡፡ ምክንያቱም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሠረት ያደረገው ይህንኑ ድንጋጌ በመሆኑ ነው፡፡

 

የፍ/ብ/ሕ/ አንቀጽ 2278(1) በውሉ የተነገረ ተቃራኒ ነገር ከሌላ በቀር የተሸጠውን ማስረከብ ከዋጋው መከፈል ጋር በአንድ ጊዜ መሆን አለበት በማለት ይገልፃል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መንፈስ መረዳት የሚቻለው የዋጋ ክፍያ እና የተሸጠው ነገር ርክክብ በአንድ ጊዜ የተፈፀመ እንደሆነ በእርግጥም የእጅ በእጅ ሽያጭ ተደርጓል ለማለት የሚቻል መሆኑን ነው፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ የ8000 ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ውሉ ሲፈፀም የከፈለ ቢሆንም እቃውን የተረከበው ግን በተለያየ መጠን በተለየየ ጊዜና ዋጋ ልክ ስለመሆኑ በስር ፍርድ


ቤት ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እንደ ሕጉ ህሳቤ የእጅ በእጅ ሽያጭ ነው ብሎ ለመደምደም የሚቻል ሆኖ አላገኘንም፡፡

 

ከዚህም ባሸገር ተጠሪ ሲሚንቶ የተረከበው ውል ከተደረገ በኃላ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ በተለየየ ጊዜና መጠን ከመሆኑም በተጨማሪ የዋጋ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል አመልከች አስቀድሞ በሰጠው ፕሮፎርማ ላይ ከማስታወቁም አልፎ ስሚንቶ ርክክብ ሲደረግ በየጊዜው የነበረውን የዋጋ ለውጥ ተጠሪ ለወከለው ተረካቢ ማስታወቁን በዚሁ አግባብም የመረካከቢያ ሰነድ ላይ ይፈርም እንደነበር በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ማስረዳቱን የሥር ፍርድ ቤት በማስረጃ ያረጋገጠው ፍሬ ነገር ነው፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንን በማስረጃ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ወደ ጎን በመተው ሽያጩ የእጅ በጅ ሽያጭ ነው በሚል ምክንያት ብቻ አልፎታል፡፡

 

ስለሆነም በአመልካች እና በተጠሪ መከከል የተደረገው የስሚንቶ ሽያጭ ውል 8000 (ስምንት ሺህ) ኩንታል ስሚንቶ በአንድ ጊዜ ተጠሪ የተረከበው ካለመሆኑም በላይ አመልካች የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል አስቀድሞ አሰውቆ በዚሁ አግባብ መዋዋላቸው አልፎም አመልካች የዋጋ ጭማሪ ስለማድረጉ በመረካከቢያ ሰነድ እያረገገጠ ተጠሪም ይህንን ሳይቃወም ተረክቦ እያለ አሁን የዋጋ ጭማሪ መደረጉ አግባብ አይደለም የሚልውን ክርክር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተቀብሎ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሻሩ የሕጉን ይዘት የግራ ቀኙን ውል እና በማስረጃ የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር ያላገናዘበ በመሆኑ ውሳኔው መሠረታዊ የህግ ስህታት የተፈፀመበት ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

 

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 128323 ጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ እና ይህንኑ ፍርድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በፍ/ብ/ይ/መ/ቁጥር 94351 ታህሳስ 30 ቀን 2006 ዓ/ም በማፅናት የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348(1) መሠረት ተሸሯል

2.  የፌዴራል የመ/ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 03910 በ05/03/05 የሰጠው ፍርድ ፀንቷል

3.  ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ ብለናል፡፡ የስር ፍርድ ቤት መዝገብ ይመለስ

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 
 
 

Google Adsense