105919 contract/ condominium/ exchange of houses

የኮንዶሚኒየም ቤት የደረሰው ሰው ሌላ የኮንዶሚኒየም ቤት ከደረሰው ሰው ጋር እጣው ከደረሰው አምስት ዓመት ባይሞላውም በልውውጥ(በስምምነት ሊቀያየሩ የሚችሉ ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14(2)

 

የሰ/መ/ቁ. 105919

ቀን ጥቅምት 4/2008ዓ.ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- ወ/ሮ መኪያ አብደላ -ጠበቃ ቶማስ ወ/ሰንበት ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ጣሰው ሸምሱ                       -ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የኮንዶሚኒየም ቤት ልውውጥ ውል መሰረት ያደረገ ክርክር ነው፡፡ በስር ፍ/ቤት ከሳሽ የአሁኑ ተጠሪ ሲሆን ክሱም ከአመልካች ጋር ባደረግነው የኮንዶሚኒየም ቤት ልውውጥ ውል መሰረት ቤቱን ታስረክበኝ የሚል ሲሆን አመልካች ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ውሉ በተንኮልና በማሳሳት የተደረገ ነው በሚል እንዲፈርስ እንዲወሰን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ያከራከረው የፌዴራል የመ/ደረጃ ፍ/ቤት በአመልካች  እና በተጠሪ መካከል የተደረገው የኮንዶሚኒየም ቤት ልውውጥ ውል የሚፈርስበት ምክንያት የለም አመልካች በዚህ የልውውጥ ውል መነሻም ተጨማሪ ብር 9000 (ዘጠኝ ሺ) መቀበላቸው ስለተረጋገጠ በውሉ መሰረት ይፈጸም በማለት ወሰነ፡፡

 

አመልካች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ አጽንቷል፡፡

 

ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ የቀረበው በዚሁ ላይ ሲሆን የሰበር ችሎቱም ኮንኮሚኒየም ቤት የደረሰው ሰው እስከ አምስት አመት ድረስ ቤቱን ለሌላ ሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ ይችላል ወይ? የሚለውን ጭብጥ ከአዋጅ ቁጥር 19/1997 አንቀጽ 14(2) አንጻር ለመመርመር ተጠሪ መልስ እንዲሰጡ አዝዟል፡፡


ተጠሪም በግራቀኙ መካከል የተደረገው የቤት ልውውጥ ውል ያልተሻረ እና ጸንቶ ያለ ስለሆነ ሊፈጸም ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥና የግራቀኙ ክርክር ባጭሩ ከላይ የተገለጸ ሲሆን እኛም ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ሲባል የተያዘውን ጭብጥ መሰረት በማድረግ አግባብነት ካለው ሕግ ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

 

ከመዝገቡ መገንዘብ እንደተቻለው መጋቢት 14ቀን 2001ዓ.ም በግራ ቀኙ መካከል በተደረገው የኮንዶሚኒየም ቤት ቅይይር ውል በአመልካች ስም በጀሞ 1ሳይት ብሎክ ቁጥር 1 የሕንጻ ቁጥር 93 የወለል ቁጥር 1 የቤት ቁጥር JG - B 93/9 የሆነው ቤት በተጠሪ ስም ያለው ጀሞ 1ሳይት ቁጥር - 163 ወለል ቁጥር 1 የቤት ቁጥር JC - B – 163/11 በሆነ ኮንዶሚኒየም ቤት በመለዋወጥ መስማማታቸውን ይገልጻል፡፡ የቤቶቹ ይዘት በተመለከተ በተጠሪ ስም ያለው ስቱዲዮ ሲሆን በአመልካች ስም ባለ አንድ መኝታ በመሆኑ ይህንኑ በገንዘብ ለማስተካከል ተስማምተው ብር 9000 (ዘጠኝ ሺህ) ተጠሪ ለአመልካች ለመጨመር መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡በክርክሩ ሂደትም አመልካች ብር 9000 መቀበላቸው ተረጋጧል፡፡

 

እንግዲህ ይህ የኮንኮሚኒየም ቤት ልውውጥ በአዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀጽ 14/2/ መሰረት የተከለከለ ነው ወይ? የሚለው ጭብጥ ምላሽ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

 

የአዋጁ አንቀጽ 14(2) ገዢው ጠቅላላው ዋጋውን ከፍሎ ቢያጠናቅቅም ቤቱን ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ ወይም በስጦታ ማስተላለፍ የሚችለው ቤቱን ከገዛ 5(አምስት) አመት ሲሞላው ብቻ ይሆናል በማለት ደንግጓል፡፡

 

ድንጋጌው በግልጽ ቃል የጠቀሰው ቤቱን በሽያጭ ወይም በስጦታ ማስተላለፍ የከለከለ መሆኑን ሲሆን አመልካች በማንኛውም መልክ ማስተላፍን ይከለክላል በሚል ህሳቤ ይከራከራሉ፡፡ የተያዘው ጉዳይ የኮንዶሚኒየም ቤት ልውውጥ እንጂ በሽያጭ ወይም በስጦታማስተላለፍ የተመለከተ ባለመሆኑ ሕግ አውጭው ይህንንም ለመከልከል ፈልጎ ቢሆን ኖሮ "በማናቸውም አኳኋን" ማስተላለፍ አይቻልም የሚል አጠቃላይ የሆነ ቋንቋ መጠቀም ይችል እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም፡፡

 

በመሰረቱ እዚህ መነሳት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ በአንድ በኩል አንድ ዜጋ ባፈራው ንብረት የመጠቀም ሙሉ መብት ያለው መሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ በተያዘው የኮንዶሚንየም ቤት አጠቃቀም መብት ላይ በጊዜ ገደብ በተወሰነ ሁኔታ ገደብ ማድረጉን አስፈላጊነትና አላማ በማመዛዘን  የሕጉን አላማ በሚያሳካ መልኩ ማስተግበር መቻሉን ማረጋገጥ ነው፡፡


ስለሆነም በእጣ የደረሰው ሰው ቤቱን በሽያጭም ሆነ በስጦታ ለሶስተኛ ወገን እስከአምስት አመት ጊዜ ድረስ ማስተላለፍ አይችልም ተብሎ በሕገ መብቱ ሲገደብ ታሳቢ የተደረገው ጥቅም የራሱ የመብቱ ተጠቃሚ የሆነው ባለእጣ መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ ይኸውም የአዋጅ መግቢያ እንደሚያመላክተው በከተማ ውስጥ ያለውን አነስተኛ የመጠለያ ችግር መቅረፍ እና በሂደትም ነዋሪው የቤት ባለቤት እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

 

ከዚህ አኳያ የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ የደረሰው የከተማው ነዋሪ በተለያዩ ጊዜያዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ተገፋፍቶ ቤቱን በሽያጭ ወይም በስጦታ የሚያስተላልፍ ከሆነ ነዋሪው የቤት ባለቤት እንዲሆን በሕጉ ታስቦ የተሰራው ስራ መክኖ ይቀራል የሚል ህሳቤ በመያዝ ምናልባት ችግሮች እንኳን ቢኖሩበት ወይም ሌላ ማህበራዊ ምክንያቶች ቢያስገድዱት በ5አመት ቆይታ ጊዜ ስለጥቅምና ጉዳት የማሰላሰያ ጊዜ አግኝቶ አመዛዝኖ ከውሳኔ ይደርሳል ተብሎ ተገምቶ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 

ስለሆነም ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አመልካችና ተጠሪ ያደረጉት ውል የኮንዶሚኒየም ቤት ልውውጥ እስከሆነ ድረስ አንዳቸውም ያለቤት ቀርቷል የሚያሰኝ ባለመሆኑ የህጉን ሃሳብና አላማ ይጥሳል ወይም ሕገ-ወጥ ውል ነው ለማለት አልተቻለም፡፡

 

ይህ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ/ቁጥር 65140 አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀጽ 14(2) ጠቅሶ ውሉ ሕገወጥ ነው በማለት የሰጠው ፍርድ ለተያዘውም ክርክር ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል በማለት በአመልካች በኩል የቀረበውን ክርክር መሰረት አድርገን በመ/ቁጥር 65140 የተሰጠውን ፍርድ ይዘት ስንመረምር ተጠቃሹ መዝገብ ላይ የቀረበው ክርክር የኮንዶሚኒየም ቤት በሽያጭ ለማስተላለፍ የተደረገ ውል የሚመለከት ሆኖ አግኝተናል፡፡ ስለሆነም በዚህ መዝገብ ከተያዘው ኮንዶሚኒየም ቤት በልውውጥ ማስተላለፍ ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ አግባብነት የለውም ብለናል፡፡

 

ሲጠቃለል አመልካች የኮንዶሚኒየም ቤት ልውውጥ አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀጽ 14(2) ድንጋጌ የተላለፈ ሕገ-ወጥ ውል ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ስለሆነም በስር ፍ/ቤት በዚህ ረገድ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡

 

በሌላ በኩል አመልካች በስር ፍ/ቤት ለቀረበባቸው መልስ ሲሰጡ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ የቤቱን ማጠናቀቂያ ስራዎች ለመስራት ብር 12,000 (አስራ ሁለት ሺህ) ወጪ  ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ማስረጃ አለኝ ሲሉ ዘርዝረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ


ሲያቀርቡ   ተጠሪ   ይህንን   ገንዘብ  እንዲተካላቸው   በተለዋዋጭ   (በአማራጭ)   ዳኝነት   የጠየቁ ስለመሆኑ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ይዘት አያመለክትም፡፡

 

ስለሆነም ውሉ የጸና ነው የሚለው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ በዚህ ሰበር ችሎት የሚሻርበት ህጋዊ ምክንያት ባለመገኘቱ አመልካች ከውሉ በኋላ አወጣሁ ያሉት ብር 12,000 አስመልክቶ ወደፊት የሚጠይቁት ዳኝነት ካለ ይህ ፍርድ አያግዳቸውም ብለናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል መ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 60424 በ22/5/2005 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 132260 በ4/02/2007ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2.  የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ

3. በዚህ መዝገብ ታህሳስ 15 ቀን 2007ዓ.ም የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡ ይጻፍ፡፡ የስር ፍ/ቤት መዝገብ በመጣበት ሁኔታ ይመለስ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት መ/ይ