106535 contract/ form/ witnesses

በጽሑፍ የተደረገ ውል ውስጥ እማኞች በመሆን የፈረሙ ምስክሮች ስለ ውሉ መኖር አለመኖር እንዳያስረዱ ክልከላ ማድረግ ተገቢ ስላለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.2005

 

የሰ/መ/ቁ.106535

ቀን 17/05/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመስል እንደሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- አቶ ረዲ ተፈራ ቀረቡ

 

ተጠሪዎች፡- 1ኛ አቶ አብሹ በቀለ          የቀረበ የለም 2ኛ አቶ ዳመሳ ኤርጳዛ

መዝገቡን ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል አዳሚ ቱሉ ወረዳ ፍ/ቤት የአሁኑ አመልካች በአሁኑ ተጠሪዎች በመ/ቁ. 21265 በቀረበው ክስ መነሻነት ነው፡፡ የክሱ ይዘት ባጭሩ የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ በሬ ሳይወሰደበት ዳለቻ በሬ ወሰደሃል በሚል ጥቁር ጋሬ የሆነ በሬ ግምቱ 8000 (ስምንት ሺህ) የሚያወጣ እንደወሰደበት የራሱ በሬ ከሌላ ሰው ጋር አግኝቶ የወሰደ ቢሆንም በሬውን አልመለስም በሽማግሌዎች አማካይነት በሬው ለመመለስ በ26/12/2005 በተፃፈ ውል በ03/13/2006 ዓ/ም በሬውን ለማቅረብ ተስማምተው እንደፈረሙ፤ 2ኛ ተጠሪም 1ኛ ተጠሪ በሬው የማይመለስ ከሆነ ዋስ እንደሆነ፣ በተጨማሪነትም 1ኛ ተጠሪ 27/08/2006 ዓ/ም በተፃፈው ውል ብር 6000.00

/ስድስት ሺህ/ ለመክፈል ፈርሞ የተቀበለ ቢሆንም ገንዘቡን ባለመክፈሉ ለመክሰስ እንደተገደደ በመሆኑም የበሬው ግምት 8,000.00 ብር ብድር 6,000.00 ከኪሰራና ወጪ  ጭምር እንዲከፈለው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡

 

የአሁኑ ተጠሪዎች በቀረቡት የመከላከያ መልስ 1ኛ ተጠሪ በሬውን አለማግኘቱን በሽማግሌዎች ፊት ተስማምተናል በማለት ያቀረበው ውል በሕግ ተሟልቶ የቀረበ አይደለም፤  03/13/2006 ዓ/ም የተባለው ቀን ስላልደረሰ አመልካች መክሰስ አይችሉም፤ የብድር ውሉ የተባለው    በሐሰት


የተዘጋጀ ሰነድ ነው፤ በ2006 ዓ/ም ይበል እንጅ በየትኛው ቀን እንደሚከፈል ስለማይገልጽ ውድቅ ሊደረግ ይገባል የሚል ይዘት ያለው መልስ አቅርበዋል፡፡ 2ኛ ተጠሪም ክሱ የመክፍያ ጊዜ የተባለው ቀን ከመድረሱ በፊት እንደቀረበ ዋስ ተጠያቂ የሚሆነው ዋና ተበዳሪ አልከፈልም የሚል ከሆነ ብቻ ስለመሆኑ በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል፡፡

 

የስር ፍርድ ቤትም የገንዘብ ብድር ውል ስምምነት አለ ወይስ የለም? ተጠሪዎች የበሬውን ግምት መክፈል አለባቸው ወይስ የለባችውም? የሚል ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን ከመረመረ በኃላ በአመልካች የቀረበው የውል ሰነድ ሰርዝ ድልዝ ስላለው አመልካች ኦርጅናሉ እንዲያቀርብ የታዘዘ ሲሆን በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አመልካች ኦርጅናል ነው ያለውን ውል ያቀረበ ሲሆን አመልካች መጀመሪያ ክስ ሲያቀርብ በ26/12/2005 ዓ/ም በተጻፈ ውል በማለት የተገለጸ ሲሆን እንደማስረጃ በቀረበው ውል ላይ ደግሞ በ2006 ዓ/ም የሚለውን በመሰረዝ 2005 ዓ/ም እንዳደረገ በችሎቱ ትዕዛዝ ከቀረበው ኦርጅናል ውል መረዳት እንደተቻለ፤ 2ኛ ተጠሪ በተመለከተውም 1ኛ ተጠሪ በሬው ስለ አገኘ የራሴ በሬ እንዲመስል ፈርሞልኛል የሚለው ከመነሻው የሰው ንብረት የወሰደ ሰው በሽማግሌ ታምኖበት ሳይገደድ ወሰደ የተባለው ንብረት ከከፈለ በኃላ እንዲመልስልኝ በማለት መስማማት የህግ መሠረት ያለው አለመሆኑን ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ውል እንደኛው በምስክሮች የተፈረመ አለመሆኑን ውሉ ነው የተባለው በአመልካች ተሰርዞ የቀረበ ስለ መሆኑ በመረጋገጡ አመልካች በቀረበው ክስ ማስረጃ መስማት ሳያስልግ ውድቅ በማድረግ ተጠሪዎች በነጻ አሰናብተዋል (ወስነዋል)፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በስር ወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከከራከረ በኃላ ኦርጅናል ውሉ የተሰረዘ ነገር እንዳለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማረጋገጡ ውሉ የተፃፈበትና የሚጠናቀቅበት ቀን ወደ ኃላ የሚቆጥር መሆኑ ሲታይ ውሉ የእውነት እንደልሆነ የሚያሳይ እና የህግ መሰረት የሌለው ነው ተብሎ በስር ፍ/ቤት ውድቅ መደረጉ ስህተት የለበትም በማለት  አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ አመልካች በጉዳዩ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈፀመዋል በማለት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ተቀበይነት አለገኘም፡፡ የአሁኑ  ሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

ጉዳዩ ለሰበር ቀርቦ እንዲመረመር በመደረጉ አመልካች በስር ፍርድ ቤቶች ተፈፀመ ያለውን ስህተት በመዘርዘር ያቀረበ ሲሆን የሰበር አቤቱታው መስረታዊ ይዘትም በክሱ የጠቀሰቸው ምስክሮች ሳይሰሙ ክሱ ውድቅ መደረጉ በሕጉ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡ ጥሪ የተደረገላቸው ቢሆንም ባለመቅረበቸው መጋቢት 09 ቀን 2007 ዓ/ም መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል፡፡


የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካለቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር ብቻ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ ለክርክሩ መነሻ በሆኑ ውሎች ላይ ስማቸው የተጠቀሱ እማኞች ቀርበው ስለ ውሎቹ መፈፀም አለመፈጸም መኖር ያለመኖር ምስክርነታቸው ሳይሰጡ ውሉ ስርዝ ድልዝ አለበት ተብሎ የአመልካች ጥያቄ ውድቅ መደረጉ በህጉ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚል ነው፡፤

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁኑ አመልካች የተወሰደባቸው በሬ እንዲመለስላቸው በብሄረሰቡ ሽማግሌዎች የተደረገ ስምምነት ስለመኖሩ እና 1ኛ በብድር መልክ የወሰደው ገንዘብ እንዲከፍል፤ 2ኛ ተጠሪም የ1ኛ ተጠሪ በሬ ከመመለስ ጋር በተያያዘ የተገበው ግዴታ ላይ ዋስ ስለመሆኑን ነው፡፡ ተጠሪዎች የቀረበባቸው ክስ ክደው ተከራክረዋል፡፡ የስር ፍ/ቤት የአመልካች ጥያቄ ውድቅ ያደረገው በአመልካች እና ተጠሪዎች ተደረገ የተበለው ውል ስርዝ ድልዝ አለበት በሚል ነው፡፡

 

በመሰረቱ አመልካች ክሱን ለማስረዳት የሰው እና የሰነድ ማስረጃ በመዘርዘር ያቀረበ ስለመሆኑ የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ የስር ፍ/ቤት ውሳኔው ላይ እንዳስፈረው ውሉ የተሰረዘ በመሆኑ በምስክሮች ማረጋገጥ ወይም ማጣራት አይቻልም ከሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን መረዳት ይቻላል፡፡ የስር ፍርድ ቤት የስው ምስክሮች ለመስማት አልገደድም ለማለት እንደመነሻ የወሰደው የፍ/ሕ/ቁ. 2005 በጽሑፍ ውስጥ ያሉ ቃላት በሰው ምስክር ለማስረዳት አይቻልም የሚል ይዘት ያለው ድንጋጌ ነው ከሚል እሰቤ ስለመሆኑ ተረድተናል፡፡ ይሁንና አመልካች እንዲሰሙለት እየጠየቀ ያለው በሁለቱም ውሎች ላይ እማኞች ናቸው ተብለው የፈረሙ ምስክሮች እንጅ በውሉ ላይ ያልተጠቀሱ ሌሎች ምስክሮች አይደሉም፡፡ በመሆኑም ከላይ የተመለከተው ድንጋጌ ክልከላ የሚያደርገው አከራከሪ በሆነው ውል ላይ ይዘቱ ላይ ምስክሮች እንደይሰሙ እንጅ በጉዳዩ ላይ እማኞች በመሆን የፈረሙ ምስክሮች ካሉ ስለ ውሉ መኖር አለመኖር እንዳያስረዱ ክልከላ ስለማደረጉ ህጉ አያሳይም፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግራ ቀኙ ለክርክሩ ምክንያት በሆነው ውል ላይ አልተማመኑም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች ክሱን ለማስረዳት የጠቀሳቸው የሰው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃ ሊመረመርሉት ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአመልካች የቀረቡ ምስክሮች ከሰማ በኃላ የሰጡት ቃል በህጉ አግባብ መዝኖ ምክንያት በመስጠት ሊቀበለው ወይም ላይቀበለው ይችላል፡፡ ነገር ግን የአመልካች ምስክሮች አከራካሪ በሆነው የውል ጉዳይ ምን ዓይነት ምስክርነት እንደሚሰጡት ሳይታወቅ ከወዲሁ ሳይሰሙ በጽሁፍ ሰነድ ላይ ብቻ ተመስርቶ የአመልካች ክስ ውድቅ ማድረጉ በህጉ አግባብ ሆኖ አልተገኘም፡፡ የአመልካች ምስክሮች እንዲሰሙ ካልተደረገ ያቀረበው ክስ ለማስረዳት የሚቸገር ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡


አመልካች እና ተጠሪዎች የሚከራከሩበት መሰረታዊ የውል ይፈጸምልኝ ክስ በተጠሪዎች የተከደ በመሆኑ ግራ ቀኙ በተካካዱበት ነጥብ ላይ አመልካች ማስረጃ የማቅረብ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ በአመልካች የቀረበው ክስ ውድቅ ሊደረግ የሚችለው ያቀረበቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በሕጉ አግባብ ተስምተው የሰጡት ቃል ይዘት ተመዝኖ በምክንያት የተደገፈ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የስር ወረዳ ፍርድ ቤት እና ጉዳዩን በየደረጃው በይግባኝ እና በሰበር የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች የአመልካች ክሱን የማስረዳት ማስረጃ የማስማት መብቱ አልፈው ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 238 (1) 255፣ 257፣259 እና 261 መሰረታዊ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያላገነዘበ ነው ብለናል፡፡ ስለሆነም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እና ትዕዛዝ የአመልካች የመደመጥና ክሱን የማሳረዳት መብቱ ያለከበረ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ በዚሁም ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የአዳሚ ቱሉ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 21265 በ11/10/2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወ/ቁ. 38245 በ14/01/2007 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 187691 በ02/03/2007 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሸሯል፡፡

2. የአዳሚቱሉ ወረዳ ፍርድ ቤት የተዘጋውን የመዝገብ ቁጥር 21265 በመክፈት በፍርድ ይዘቱ በተገለጸው መንፈስ አመልካች በክሱ የጠቀሳቸው እና ለክርክሩ ምክንያት በሆኑ ውሎቹ ላይ እማኞች የነበሩ ግለሰቦች ቀርበው ግራ ቀኙ እያከራከራ ያለው ውል መፈጸም ያለመፈጸሙን ውሉ መኖር ያለመኖሩን ምስክርነታቸው እንዲሰጡ ከተደረገ በኃላ የሰጡት ቃል በህጉ አግባብ ተመዝኖ ጉዳዩ ተገቢ ህጋዊ ውሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 343 (1) መሠረት መልሰንለታል፡፡ ይፃፍ፡፡

3.  ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ

መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ተመለሰ

 

 


 

 

ሩ/ለ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡