112328 contract/ sale of immovable property/ transfer of title

አንድን ንብረት የሸጠ ሰው የሸጠውን ንብረት ባለሃብትነት ለገዥው የማዛወር ግዴታ ያለበትና ይህንን ለመፈፀም አስፈላጊ የሆኑ ተግባራቶችን የማከናወን ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.2273፣2281፣1771(1)፣1757

 

የሰ/መ/ቁጥር 112328

 

የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመለካች፡- ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይ - ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን - ነ/ፈጅ ግርማ ዘለቀ - ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- አቶ ኤፍሬም አሸቱ - የቀረበ የለም

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የመኪና ሽያጭ ውልን መሰረት ያደረገ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- አመልካች መጋቢት 10 ቀን 2003 ዓ/ም ባወጣው የመኪና ሽያጭ ጨረታ ላይ ተሳትፈው የታርጋ ቁጥር 3-18353 ኢት የሆነውን መኪና በብር 127,915.55 (አንድ መቶ ሃያ ሰባት ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ አምስት ብር ከሃምሳ አምስት ሳንቲም) የገዙ ቢሆንም ለስም ዝውውሩ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተሸከርካሪውን ማጣሪያ ክሊራንስ እንዲመጣ መጠየቃቸውንና ተጠሪ አመልካችን በዚህ አግባብ እንዲፈፀም ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም አመልካች ለማስጠንቀቂያው በሰጠው ምላሽ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስም ዝውውሩ እንዲፈጸም ቃል የገባ ቢሆንም አለመፈጸሙን፣ በዚህ መሰረት አመልካች መኪናውን ለገዛው ተጠሪ ስም ለማዛወር የሚረዱ ሰነዶችን ለተጠሪ የማስረከብ ግዴታውን ያልፈፀመ  እና የመኪናው የኪራይ ገቢ ዋጋ በቀን ገቢ ተሰልቶ ብር 205,000.00(ሁለት መቶ አምስት ሺህ) ጥቅም የቀረባቸው መሆኑን ዘርዝረው አመልካች ለተጠሪ መኪናው ከግብርና ታክስ እዳ ነፃ የሆነበትን የክሊራንስ ሰነዶች እንዲያስረክብ፣ በቀን የታጣ ገቢ ብር 205,000.00 እንዲከፍል፣ ሰነዶቹን እስከሚያስረክብ ድረስ ያለውን ኪሳራ የመጠየቅ መብት እንዲጠበቅላቸው ይወሰን  ዘንድ


ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም፡- ተጠሪ አከራካሪውን መኪና ከአመልካች በጨረታ መግዛታቸውን ሳይክድ በመኪናው ላይ ምንም አይነት እዳና እገዳ የሌለበት መሆኑን፣ መኪናው ሲሸጥም የመኪናውን የባለቤትነት ደብተር/ሊብሬ/፣ ሌሎች ማስረጃዎችን በሙሉ ከነመለያው ለተጠሪ ማስረከቡን፣ ለሚመለከተው አካልም ስመ ሃብቱ እንዲዞርላቸው ነሀሴ 03 ቀን 2003 ዓ/ም ደብዳቤ የፃፈላቸውና ተጠሪም ግልባጩን ተረክበው የወሰዱና ለፕሮክጀት ስራ ተቋራጭ ነፃ በገቡ ማስረጃዎች ጋር በተያያዘ ከኢትዩጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በተፈጠረ ችግር ኃላፊነትት የለብንም በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ አመልካች ለተጠሪ መኪናው ከግብርና ታክስ እዳ ነፃ የሆነበትን  የክሊራንስ ሰነዶች እንዲያስረክብ፣ በቀን የታጣ ገቢ ብር 205,000.00 እንዲከፍል፣ ሰነዶቹ እስከሚያስረክብ ድረስ ያለውን ኪሳራ ደግሞ ተጠሪ የመጠየቅ መብት የተጠበቀ መሆኑን ገልፆ ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ  ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘት፡- ለክሱ መነሸ የሆነውን መኪና አመልካች በግልጽ ጨረታ ሽጦ የስም ዝውውር በተመለከተም በጨረታው መመሪያው መሰረት በሕግ የሚፈለገውን ተግባር ሁሉ አመልካች ድርጅት ፈጽሞ እያለ ንብረቱ ለስም ዝውውር ምንም አይነት እዳና እገዳ ሳይኖርበት የሕግና የፍሬ ነገር መሰረት በሌለበት አግባብ አመልካች ለክሱ ኃላፊ ተደርጎ የቀን ገቢ ብር 205,000.00 እና የጠበቃ አበል እንዲከፍል መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች አከራካሪውን መኪና ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉትን ሰነዶች ለተጠሪው አስረክቢያለሁ ብሎ ተከራክሮ ባለበት ሁኔታ የስር ፍርድ ቤት ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ያላስረከበ መሆኑን አመልካች አልካደም በሚል ምክንያት አመልካች ግዴታውን አልፈፀመም በማለት የተሠጠውን ውሳኔ አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል፡፡

 

የክርክሩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ባወጣው የመኪና ሽያጭ ጨረታ ላይ ተጠሪ ተወዳድረው ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ተሸከርካሪ መግዛታቸው ግራ ቀኙን ያላከራከረ   ነጥብ


መሆኑን፣ አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩት ለስም ዝውውሩ አስፈላጊ ከሆኑት ሰነዶች መካከል መኪናው እዳና አገዳ የሌለበት መሆኑን የሚገለፅ የክሊራስን ሰነድ ለተጠሪ የመስጠት ግዴታ አመልካች ያለው መሆን ያለመሆኑን ላይ ስለመሆኑ ነው፡፡

 

ከላይ እንደተገለጽው የተጠሪ ዋነኛ የዳኝነት ጥያቄ በውል ገዝቼዋለሁ የሚሉትን መኪና ስመሃብት በስማቸው እንዲመዘገብ መኪናው እዳና እገዳ የሌለበት ስለመሆኑ የሚያሳይ ሰነድ በአመልካች ይሰጠኝ ሲሆን በስሜ እንዲመዘገብ ለማድረግ አስፈላጊ ሰነዶች ከአመልካች አልተሰጠኝም የሚሉት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለ መኪናው ከእዳና እገዳ ነፃ መሆን የሚያሳይ የክሊራንስ ሰነድን ነው፡፡ አመልካች የመኪናውን የባለቤትነት ደብተር/ሊበሬ/ እና ሌሎች ማስረጃዎችን በሙሉ ከእነመለያው ለተጠሪ ማስረከቡን ገልፆ ለአቀረበው ክርክር  ተጠሪ ማስተባበያ ክርክርና ማስረጃ ያቀረበ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ አሳያስም፡፡ አንድን ንብረት የሸጠ ሰው በፍትብሐር ሕግ ቁጥር 2273 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የሸጠውን ንብረት ባለሀብትነት ለገዥው የማዛወር ግዴታ ያለበት ሲሆን ይኸም የሻጭ የንብረቱን ባቤትነት ለገዥ የማዛወር ግዴታ በምን መልኩ መፈፀም እንደሚገባው ህግ አውጭው ‹‹ሻጩ የሸጠውን ነገር የማያስነካ መብት ለገዥው ለማስተላለፍ አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮችን ለመፈፀም ግዴታ አለበት›› በማለት በፍትብሔር ህግ ቁጥር 2281 በግልጽ ከደነገገው የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም አመልካች ተጠሪ የመኪናን ሽያጭ በውሉ  መሠረት  እንዲፈጽሙና ስመንብረቱን ለተጠሪ ለማዛወር አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን መፈጸን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም የስም ሃብት ዝውውሩን ለማድረግ አስፈላጊ ተግባራት አልተከናወኑም የሚለው ገዥ እነዚህን በሻጭ ያልተከናወኑትንና የስመ ሃብት ዝውውሩን የሚያከናውን አካል ኃላፊነቱንና ተግባር ለመፈፀም የማያስችለው አስፈላጊ ተግባር ምን እንደሆነ እና አስፈላጊነቱን  ማስረዳት  መቻል አለበት፡፡

 

ከዚህ ውጪ ተገቢው ሰነድና ለሽያጩ መሰረት የሆነው ንብረት ርክክብ ተፈጽሞ እያለ ስመ ሃብቱ አልተዛወረልኝም በሚል ምክንያት ብቻ በሻጩ ላይ ክስ ማቅረብ እና ተቀባይነት የሚያገኝበት አግባብ የለም፡፡

 

ከተዋዋዮቹ አንዱ ወገን የውል ግዴታውን ያልፈጸመ እንደሆነ ሌላው ወገን እንደነገሩ አጋጣሚ ሁኔታ ውሉ እንዲፈጸምለት የመጠየቅ መብት እንዳለው፣ ካልሆነም ውሉ እንዲፈርስ መጠየቅ እንደሚችል ወይም ውሉ መፍረሱን ለሌላው ወገን ሊገልጽ የሚችል መሆኑን የፍ/ህ/ቁ/1771(1) የሚደነግግ ሲሆን በውሉ አለመፈጸም የተነሳ ጉዳት የደረሰበት ከሆነም ኪሳራ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት ያለው መሆኑን የድንጋጌው ንዑስ ቁጥር 2 ያመለክታል፡፡ ውሉ ተዋዋዮቹ በአንድነት የሚፈጽሙትን ግዴታ (simultaneous performance) የሚጥል ሆኖ ከተገኘም ተዋዋዩ የተዋዋለበትን ግዴታ በውሉ እንደተመለከተው እንዲፈጸምለት    የሚጠይቀው


ወገን ከውሉ ስምምነት የተነሳ እሱም በበኩሉ ያለውን ግዴታ ወዲያውኑ መፈጸም ወይም ለመፈጸም የተዘጋጀ መሆኑን ማረጋገጥ የሚገባው መሆኑን የፍ/ህ/ቁ/1757 ያስገነዝባል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ አመልካችን ሊከሱ የቻሉት የስመ ሃብቱን ዝውውር በሚያደርጉት እለት በመኪናው ላይ የእዳና እገዳ ነፃ መሆኑን የሚያሳይ የክሊራንስ ሰነድ ከገቢዎችና ጉምሩክ ተጠይቀው ይኼው ሰነድ በአመልካች ሊቀርብላቸው ባለመቻሉ ነው፡፡ ይሁን  እንጂ ይህን የክሊራንስ ሰነድ ማቅረብ የአመልካች ግዴታ ስለመሆኑ የሚያሳይ የውል ግዴታ የሌለ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ሰነዱን ራሳቸው ለመውሰድ ያላስቻላቸው ምክንያት ስለመኖሩ ወይም የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ክሊራንስ የከለከላቸው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ተጠሪ አላቀረቡም፡፡ ተጠሪ ስመ ሃብቱን ለማዛወር የሚያስችለው አስፈላጊ ተግባር በአመልካች መከናወን ያለበት ስለመሆኑ ባላስረዱበት ሁኔታና አመልካች ደግሞ መኪናውንና አስፈላጊ ሰነዶችን ለተጠሪ ማስረከቡን ገልፆ በተከራከረበት አግባብ የስር ፍርድ ቤት አመልካች አስፈላጊ ሰነዶችን ያላስረከበ መሆኑን አልካደም በማለት የደረሰበት ድምዳሜ ለጉዳዩ የቀረበውን የግራ ቀኙን ክርክር ይዘት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 235 እና 83 ድንጋጌዎች ይዘት ያላገናዘበ ሁኖ አግኝተናል፡፡ እንዲሁም ተጠሪ አመልካች ነሐሴ 03 ቀን 2003 ዓ/ም በፃፈለት  ደብዳቤ መነሻ  ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሂደው መኪናው ከእዳና እገዳ ነጻ ስለመሆኑ የሚያሳይ የክሊራንስ ሰነድ ማግኘት ያልቻሉ መሆኑን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2001፣ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 258 እና 259 ድንጋጌዎች ይዘት መሰረት ባላስረዱበት ሁኔታ አመልካች ለክሱ ኃላፊ መደረጉ ከማስረዳት ሽክም አንፃር ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ ስለሆነም አመልካች የሸጠውን መኪና ስመንብረት (ባለሀብትነት) ለተጠሪ ለማዛወር አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን የመፈፀም ግዴታና ሀላፊነት ስላለመወጣቱ ተጠሪ ባለስረዱበት ሁኔታ አመልካች ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉ ሰነዶች ያላስረከበ መሆኑን አልካደም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘውን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 197988 በ19/09/2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 137860 በ06/08/2007 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪ ከአመልካች ለገዛው ተሸከርካሪ ስመ ሃብት ዝውውር ያልፈፀመው አስፈላጊ ተግባር ስለመኖሩ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2273 እና 2281 ድንጋጌዎች አግባብ ተጠሪ ስላላስረዱ  አመልካች ለክሱ ኃላፊ የሚሆንበት የሕግ አግባብ የለም ብለናል፡፡


3. ለክርክሩ ምክንያት የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡