99124 contract/ sale of immovable property/ form

ተዋዋዮች የማይንቀሳቀስ ንብረት በሽያጭ ሲተላለፍ በህጉ በተደነገገው መሰረት ውል ለመዋዋል ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት ቀርቦ የማስመዝገብ ግዴታን ስምምነታቸው ላይ ካካተቱና ነገር ግን ይህንን ተፈፃሚ ማድረግ ካልተቻለ የተዘጋጀው ስምምነት ረቂቅ እንጂ ከጅምሩ ውል ነው ተብሎ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚገባቸውን ጉዳዮች ማንሳት ሰህተት ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.1723፣1810፣1885(1)

 

የሰ/መ/ቁ. 99124

 

የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ/ም

 

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

 

 

አመልካቾች ፡- 1ኛ  ወ/ሮ ስብለ ማሞ            ጠበቃ እሌኒ አስራት ቀረቡ 2ኛ አቶ ዳዊት ግርማ

ተጠሪዎች፡- 1 የ፲ አለቃ  ተስፋየ  በዛብህ ወራሾች 1. ወ/ሮ      ትግስት        ተስፋየ   - ቀርቧል

2. ወ/ሮ  አስራት  ተስፋየ -ቀርቧል

 

2ኛ ወ/ሮ ጥሩነሽ ሀይሉ -ወኪል ወ/ሮ ትግስት ተስፋዬ ቀርቧል፡፡ መዝገቡን መርምረን የሚከተውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን በዚሁ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካቾች ከሰሾች፤ የአሁኑ ተጠሪዎች ተከሳሾች በመሆን ተከራክረዋል፡፡ የስር ከሳሾች የካቲት 22 ቀን 2005ዓ/ም በተፃፈ አቤቱታ ያቀረቡት ክስ መሰረታዊ ይዘቱ በግራ ቀኙ ጥቅምት 30/2005ዓ/ም በተደረገው የሽያጭ ውል በኮ/ቀ/ክ/ከ/ወ/07 በተከሳሾች ስም ተመዝግቦ የሚገኘው የቦታው የስፋት መጠን 105ካ/ሜ ካርታ ቁጥር ኮ/ቀ/የማ/ን/መ/154/12199/00 የሆነውን ቤት በ800,000/ስምንት መቶ ሺ ብር /ሊሸጡልን የተዋዋልን ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሰነዶች ማረጋገጫ እና መዝገብ ጽ/ቤት እስከሚረጋገጥ ድረስ በቅድሚያ 50,000/ሀምሳ ሺ ብር/ በምስክር ፊት ቆጥረን ሰጠናል፡፡ ሆኖም ተከሳሾች ከዛሬ ነገ ሲሉ እሰከ ሶስት ወር ውል ያልፈፀሙ ሲሆን እንዲያውም አንደኛ ተከሳሽ የአእምሮ በሽተኛ እንደሆነ እና ውሉን በምናደርግበት ሰዓት ሁለተኛ ተከሳሽ  ይህኑን  ያልነገሩን  ሲሆን  በዚሁም  ምክንያት  ውሉ  ተፈፃሚ  መሆን እንደማይችል


ስለተረዳን ውሉን ማፍረሳችን እና የሰጠውን ብር 50,000/ አምሳ ሺ ብር/ ቀብድ የሰጠናቸውን እንዲመልሱልን በቀን 11/06/2005 ዓ/ም በፅሁፍ  ብንጠይቃቸው  ፍቃደኛ ስላልሆኑ ፍ/ቤቱ አንደኛ ተከሳሽ የአእምሮ በሽተኛ ስለሆኑ ውሉ እንዲፈርስልን እንዲሁም ቀብድ የወሰዱትን 50,000 ብር እንዲመልሱልን እና በውሉ መሰረት ስላልፈፀሙ መቀጮ 20,000 ብር እንዲከፍሉ እንዲሁም ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸው ዳንኝነት ጠይቀዋል፡፡

 

ተጠሪዎች በ29/08/2005 ዓ/ም በተፃፈ የሰጡት መልስ በፍ/በብስ/ስ/ህ/ቁ.1810 መሰረት ውሉን የማፍረስ ስልጣን የላቸውም፡፡ 1ኛ ተከሳሽ የአእምሮ በሽተኛ አይደሉም እንጂ በሆኑ እንኳ እሳቸው ነበሩ ውሉ ይፍረስልን ብለው መጠየቅ የነበረባቸው፡፡ ከሳሾች ውሉን በፍቃዳቸው ካፈረሱት በውሉ ያስያዙት ቀብድና መቀጮ የጠየቁት ሕግን የተከተለ አይደለም፡፡ ስለሆነም ፍ/ቤቱ በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከበቂ ወጪና ኪሳራ ጋር ክሱን ውድቅ እንዲደረግ፡፡ ይህ የሚታለፍ ከሆነ ግን በፍሬ ነገሩ ላይ የተሰጠ መልስ 1ኛ ተከሳሽ ውሉን ከተዋዋልን በኋላ ውልና ማስረጃ ሂደን ልናስመዘግብ ስንል በእድሜው የገፋ ሰው ስለሆኑ ፍ/ቤት ሄዳችሁ አጽድቁ እንዲህ አይነት ዕድሜ የገፋ ሰው ፍ/ቤት ነው  የሚያፀድቀው በማለት እንዲመለስ አድርጎናል፡፡ ነገር ግን ከሳሽ የባንክ ብድር ስለሚያመልጠኝ እና ቅናሽ ቤትም ስላገኘን ቀብዱን መልሱ ብለው ጠየቁን እኛ ግን ፍ/ቤት ሄደናል፡፡ አላፈረስንም እነሱ ናቸው ያፈረሱት ስለሆነም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1885/1/2/ መሰረት ከሳሾች በውሉ መሰረት 20,000 ብር ለተከሳሾች እና 20,000 ብር ለመንግሰት በአጠቃላይ 40,000 ብር መቀጮ እንዲሁም ወጪና ኪሳራ በማስከፈል ክሱ ውድቅ ተብሎ እንዲወሰንላቸው በማለት መከላከያ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካከሄደ በኋላ ውሉ ያልተፈፀመው ተከሳሾች በውሉ መስረት ለመፈፀም ጥረት እያደረጉ እያለ በከሳሽ የባንክ ብድር ያመልጠናል በሚል እና ሌላ ቤት በማግኘት ውሉን በራሳቸው ፍቃድ ሰርዘው ሌላ ቤት የገዙ መሆናቸው ነው፡፡ ውሉ ያልተፈፀመው በከሳሾች ምክንያት ከሆነ ደግሞ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1885/1/ መሰረት ቀብድ የከፈለው ሰው በራሱ ፍቃድ ውል ከሰረዘ ቀብድውን መጠየቅ ሰለማይችል ከሳሾች የከፈሉት ቀብድ ብር ተከሻሾች መክፈል የለባቸውም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

አመልካቾች በስር ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የተፈፀመ ስሕተት የለበትም በማለት በትእዛዝ ሰርዞታል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ/ም በፃፉት የሰበር አቤቱታ በበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን  ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- ከተጠሪዎች ያደረግነው ውል በ1ኛ ተከሳሽ ፍቃድ


ጉድለት ምክንያት ሊፈፀም አለመቻሉ በተጠሪዎች የታመነ ሁኖ እያለ ክስ ለማቅረብ መብትና ጥቅም የላችሁም በማለት ውሰኔ መስጠቱ የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.33 እና 244 ድንጋጌ የሚቃረን ውሳኔ በመሆኑ፤ 1ኛ መልስ ሰጪ የሰነዶች መረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ቀረበው ስለሚዋዋሉት ጉዳይ አውቀው ፍቃዳቸውን ለመስጠት ባለመቻላቸው ምክንያት የሽያጭ ውሉ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 በሚደነግገው መሰረት ሊመዘገብና ሊፈፀም ያልቻለ መሆኑ፤ ጥቅማችን የጎዳ በመሆኑ ውሉ እንዲሰረዝ የመጠቅ መብት ያለን ሆኖ እያለ አትጠይቁም በማለት የተሰጠ ውሳኔ በመሻር በክሳቸው መሰረት እንዲወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

 

የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ በሰበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል  በመባሉ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት ግንቦት 8 ቀን 2006 ዓ/ም የተጸፈ መልስ አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 መሰረት በፍርድ ቤት ወይም በአዋዋይ ፊት ይላል እንጂ በአንዱ ብቻ እንዲደረግ አይልም፤ ውሉ ለመፈፀም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ውሉ አፍርሰናል የከፈልነው ቀብድ ይመለስልን ለማለት አይችሉም፤1ኛ ተዋዋይ የ፲ አለቃ ተስፋየ በዛብህ  የእእምሮ በሽተኛ አይደሉም እንጂ ቢሆኑ እንኳን በእሳቸው የችሎታ አለመኖር አመልካቾች የውል ይፍረስልኝ ጥያቄ ማቅረብ አይችሉም፤የስር ፍርድ ቤት ቀብድ አይመለስም ሲል የሰጠው ውሳኔ ህጉን መሰረት ያደረገ ስለሆነ የሚነቀፍበት ምክንያት ስሌለ የአመልካቾች አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በማጽናት እንዲሰናበቱ በመጠየቅ መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡ አመልካቾችም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ እንደተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረቶች ባለቤትነት ወይም ባንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የአላባ ጥቅም መብት ወይም የመያዣ ወይም የሌላ አገልግሎት መብት ለመቋቋም ወይም ለማስተላለፍ የሚደረጉት ውሎች ሁሉ በጽሁፍና በሚገባ አኳኋን በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ውል የመዋዋል ስልጣን በተሰጠው ፊት መሆን እንዳለባቸው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.  1723(1) ተደንግጓል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረትን አስመልክቶ የሚደረግ ውል በተለየ ፎርም እንዲፈፀም ግድ ከሚሆነባቸው ሁኔታዎች አንዱ የሽያጭ ውል ነው፡፡  በአመልካቾችና  ተጠሪዎች መካከል የሽያጭ ውል ለማድረግ ያሰቡት ይህንኑ የህግ ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ውሉ ለመዋዋል ስልጣን ባለው አካል ቀረበው ለመፈፀም መሆኑን በግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች የታመነ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን በመከተል ወደ ውልና ማስረጃ ማረጋገጫና ምዝገባ ሰነዶች ተመላልሰው 1ኛ ተከሳሽ ስለሚዋዋሉት ጉዳይ ሀሰባቸውን ለመግለፅ በላመቻለቸው ውሉ ለማድረግ ያለተቻለ መሆኑን ይህም የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡


በተጠሪዎች በፍርድ ቤት ሊነዋዋል እየተቻለ አመልካቾች ፍቃደኛ አልሆኑም፤ፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 በአዋዋይ ፊት ብቻ አይልም በፍርድ ቤትም ሊደረግ የምችል ነው ከሁለቱ በአንዱ ሊደረግ ይችላል በማለት ያቀረቡት ተቀባይነት የለውም ምክንያቱ ህጉ ያሰቀመጠው በአመራጭ ነው፡፡ በፍርድ ቤት ወይም በአዋዋይ ፊት ሊደረግ እንደሚቻል ሲገልፅ ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ለተዋዋዮች የተተወ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የተመረጠው በአዋዋይ ስልጣን በላው አካል እንዲደረግ ነው፡፡ ስለዚህ በተስማሙት መሰረት ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው  አካል በመቅረብ በታሰበው መሰረት ሊፈፀም በለመቻሉ ረቂቅ ውል ከመሆን አልፎ ውል ነበረ ለማለት አይቻልም፡፡ ረቂቅ ከሆነ ደግሞ በማናቸው ሁኔታ ያሰቡትን ለመተውና የተከፈለ ገንዘብ ካለ ለማስመለስ ከመጠየቅ የሚከለክሉበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ ከመሰረቱ ውል ከሌለ ከውል ጋር ተያይዥነት ያላቸው  ውል  እንዲሰረዝ  የመጠየቅ  መብት  ያለው  ማነው?  የሚል  እና ፍ/ብ/ህ/ቁ.1808

/1/2/፤1810፤1885/1/ የተመለከቱት ተያያዥ ጉዳች ሊነሱ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የስር  ፍርድ ቤት በረቂቅ ደረጃ በቀረ ጉደይ ላይ አግባብነት የሌላቸው የህግ ድንጋጌዎች በመጥቀስ የአመልካቾች ክስ ውድቅ በማድረግ የተሰጠ ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም የሚከተለው ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.30711 ሐምሌ 2 ቀን 2005ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.140449 ታህሳስ 24 ቀን 2006ዓ/ም የተሰጠ ትእዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪዎች ለአመልካቾች ብር 50,000 /አምሳ ሺ ብር/ በዚህ ችሎት ውሳኔ  ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ተከፍሎ አስከሚያልቅ ድረስ ከ9% ወለድ ጋር ይክፈሉ፡፡

3.  በፍርዱ መሰረት እንዲያስፈጽም የውሳኔው ቅጂ ለፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ይላክ፡፡

4.  በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

5.   መዝገብ ተዘግተዋል ፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ፡፡

 

 

 

 

መ/ይ