100651 unlawful enrichment/

አንድ ሰው በህግ ወይም የሚፀና ውል የሚሰጠው አንዳች መብት እንደሌለ እያወቀ የሌላ ሰው የሆነን ንብረት በእጁ ባደረገ ጊዜ ንብረቱ ሊያፈራ የሚችለውን የገንዘብ ግምት እንዲመልስ ሊወሰን የሚችል ስለመሆኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ.2178

 

የሰ/መ/ቁ. 100651

 

መሰከረም 27 ቀን 2008 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- ወ/ሮ መንበረ ሰፈርህ - አልቀረቡም

 

ተጠሪዎች፡- 1ኛ. ወ/ሮ ብርሃኔ ጌቴ የኤርሚያስ ምህረት እና የትዕግስተ ምህረት ሞግዚት 2ኛ. ወ/ሮ ባንቻየሁ አዝመራ የሊዲያ ምህረት እና የውባለም ምህረት ሞግዚት

3ኛ. ወ/ሪት አዜብ ምህረት - አልቀረቡም

 

መዝገቡ ለምርምራ የተቀጠረ ሲሆን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ከግራ ቀኙ የቀደመ ክርክር እና በሰበር መ/ቁ.78774 ጥር 29/2005 ዓ/ም ከተሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ መረዳት እንደሚቻለው አመልካች ከሟች አቶ ምህረት ታዬ ጋር በተደረገ የጋብቻ ውል የክርክሩን ንብረት የጋራ አድርገናል ቢሉም የጋብቻ ውሉ በፍርድ ቤት ያልጸደቀ በመሆኑ ምክንያት ንብረቶቹ የውርስ ሀብቶች ናቸው በሚል ለወራሾች /ለተጠሪዎች/ እንዲያስረክቡ ተወስኗል፡፡

 

ከዚህ በኋላ አመልካች ከሟች ባለቤታቸው ጋር በጋብቻ አብረው ሲኖሩበት የነበረውን የመኖሪያ ቤት ተጠሪዎች የኪራይ ግምት አውጥተው ሟች ከሞቱበት ሚያዝያ 30/2000 ዓ/ም ጀምሮ እስካስረከቡበት ጊዜ ድረስ የሚታሰብ ኪራይ እንዲከፍሉ እና ንብረቱንም እንዲያስረክቡ ተጠሪዎች በአመልካች ላይ በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ክስ አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም አመልካች ኪራይ አልከፍልም በማለት የሚከራከሩት ሚስት ነኝ በሚል ቢሆንም ሚስት የሆኑት እስከ ሟች እለተሞት ብቻ ነው ፤ ሟች ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ በንብረቱ ምንም መብትና ጥቅም ሳይኖራቸው በቤቱ መቀመጣቸው የህግ ድጋፍ የለውም ፤ በቤቱ ኪራይ መጠን ላይ ያቀረቡት ክርክርም የለም፡፡ በማለት በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2162 መሰረት ያላግባብ በቤቱ ለተጠቀሙበት በወር 600 ብር ሂሳብ ለ   4


አመት ብር 28,800 (ሃያ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ) አንዲከፍሉ እና ቤቱን እንዲያስረክቡ ወስኗል፡፡

 

በዚህ ውሳኔ ቅር ተሰኝተው አመልካች ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ በማሻሻል ኪራይ ሊታሰብ የሚገባ ተጠሪዎች ቤቱን ለመረከብ ከጠየቁበት ጊዜ ጀምሮ ነው ፤ ሟች ምህረት ታዬ ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ አመት ተጠሪዎች ቤቱን ለመረከብ አልጠየቁም ፤ ቤቱ እንዲለቀቅላቸው ባልጠየቁበት ሁኔታ ደግሞ አመልካች በቤቱ ለተጠቀሙበት ክፈሉ ሊባሉ የሚችሉበት ሁኔታ የለም በማለት የአንድ ዓመት ጊዜ ኪራይ ብር 7,200.00 ቀንሶ ብር 21,600 (ሃያ አንድ ሺ ስድስት መቶ) እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡

 

የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ አመልካች ግንቦት 5/2006 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ ከሟች ባለቤቴ ጋር በመሰረትነው ጋብቻ ምክንያት በጋራ ልንኖርበት በተሰማማነው መሰረት የኖርኩበተን ቤት ፤ ቤቱን ለሌላ ሰው በማከረየት ያገኘሁት ጥቅም ስለመኖሩ ማረጋገጫ ሳይቀርብ መብቴን ለማስከበር በክርክር የቆየሁበት ጊዜ ተሰልቶ ኪራይ እንድከፍል መወሰኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2162 ድንጋጌ በአግባቡ ሳይተረጎም በመሆኑና በቤቱም የኖርኩት በአሳማኝና በቂ ምክንያት በመሆኑ ኪራይ እንድከፍል የቀረበው ጥያቄ እና በስር ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

 

ተጠሪዎች በበኩላቸው በሰጡት መልስ ቤቱን እንዲያስረክቡና ለተገለገሉበት ኪራይ እንዲከፍሉ ለአሁኑ የሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነውን ክስ ማቅረባቸው የሚነቀፍ ባለመሆኑ ፤ በሟችና በአመልካች መካከል የነበረው ጋብቻ በሞት ምክንያት የፈረሰ በመሆኑ ሟች ከሞቱበት ከሚያዝያ 30/2000 ዓ/ም ጀምሮ ቤቱን ማስረከብ ሲኖርባቸው ክርክር በማቅረብ በተጠሪዎች የውርስ ሃብት ያላግባብ መጠቀም የሚገባቸው ባለመሆኑ ፤ ተገቢ ያልሆነ ክርክር በማቅረብ ፍርድ እስኪሰጥ ድረስ በውርስ ሃብት ያላግባብ መገልገል አለብኝ የሚለው ክርክርም የህግም ሆነ የፍትህ መሰረት የሌለው በመሆኑ የተገለገሉበትን ኪራይ እንዲከፍሉ እና ቤቱን እንዲያስረከቡ መወሰኑ  ትክክል ነው ተብሎ የሰበር አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ አመልካችም ክርክራቸውን በማጠናከር የመ/መልስ ሰጥተዋል፡፡

 

ከላይ ባጭሩ የተገለጸው የጉዳዩን አመጣጥ ለማመልከት ሲሆን የግራ ቀኙን ክርክር እና የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ከህጉ ጋር በማያያዝ መርምረናል፡፡

 

እንደመረመርነው አመልካች ለተገለገሉበት ጊዜ ኪራይ እንዲከፍሉ በተወሰነባቸው ቤት ውስጥ ከሟች ባለቤታቸው ምህረት ታዬ ጋር ተጋብተው ይኖሩበት እንደነበር ግራ ቀኙ   አላከራከረም፡፡


የአሁን ተጠሪዎች የውርስ ሃብት ነው የተባለው ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ቤት አመልካች በጋብቻ ውል የጋራ የተደረገ ነው የሚል ክርክር አቅርበውበት የነበረ ሲሆን ክርክሩን በቅድሚያ የተመለከተው የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት የጋራ ሃብት ነው ተብሎ ተወስኗል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በይግባኝ እና በሰበር ሲያከራክር ቆይቶ በፊዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጥር 29/2005 ዓ/ም በተሰጠው ውሳኔ የጋብቻ ውሉ በፍ/ቤት ያልጸደቀ በመሆኑ ምክንያት ንብረቱ የውርስ ሃብት ነው በሚል ተወስኗል፡፡

 

ግራ ቀኙ በክርክር መቆየታቸው በተረጋገጠበት ሁኔታ አመልካች ከባለቤታቸው ሞት በኋላ በቤቱ ለተጠቀሙበት ጊዜ አላግባብ ጥቅመ አግኝተዋል ተብሎ በንብረቱ በተገለገሉበት ልክ ኪራይ እንዲከፍሉ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2162 ተጠቅሶ መወሰኑ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም፡፡

 

በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2162 እንደተደነገገው በሌላ ሰው ሀብት በሆነ ነገር በመገልገል በቂ ባልሆነ ምክንያት ጥቅም ያገኘ ሰው አላግባብ ባገኘው ጥቅም መጠን ለባለሃብቱ የመመለስና የመካስ ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ ይደነግጋል፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ከባለቤታቸው ሞት በኃላ በቀደመው መልኩ በቤቱ መገልገል መቀጠላቸው እና ቤቱ የጋብቻ የጋራ ሃብት ነው በማለት ክርክር አቅርበው በክርከራቸው መሰረት ተወስኖላቸው የነበረ መሆኑ ሁሉ ሲታይ በቤቱ የተገለገሉት በቂ ምክንያት በሌለበት ነው የሚሰኝ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በህጉ መንፈስ አላግባብ ጥቅም አገኙ የሚሰኝ ሆኖ አይታይም፡፡ ከዚህም ሌላ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.2178 ይዘት መረዳት እንደሚቻለው አመልካች ንብረቱ ሊያፈራ የሚችለውን የገንዘብ ግምት እንዲመልሱ ሊወሰን የሚችለው በንብረቱ ላይ አንዳች መብት እንደሌላቸው እያወቁ በእጃቸው አድርገው እንደሆነ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ የተረጋገጡው ከላይ የተመለከተው ፍሬ ነገሮችን ይህን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በመሆም አመልካች ያላግባብ በልጽገዋል ተብሎ ገንዘብ እንዲመልሱ እና ተጠሪዎችን እንደ ክሱ የተሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ተከታዩ ተወስኗል፡፡


 ው  ሳ ኔ

 

1ኛ. የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤተ በኮ/መ/ቁ. 135467 የካቲት 7/2006 ዓ/ም ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሁም የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ.25610 ሚያዝያ 7/2005 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

 

2ኛ. አመልካች በቤቱ ለተገለገሉበት እንዲከፍሉ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል፡፡

 

3ኛ. የስር ፍ/ቤቶች ያሳለፉት ቀሪው ፍርድ እና ውሳኔ የጸና ነው ብለናል፡፡

 

4ኛ. የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡