96548 extracontractual liability/ professional liability

በወሊድ ወቅት በህክምና ተቋሙና በሙያው ባለቤት ዘርፉ የሚጠይቀውን ጥንቃቄ ሳይደረግ በሚወለደው ህፃን ላይ የአካል ጉዳት ከደረሰ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1790፣2028፣2031፣2647 /2/ እና 2651

 

የሰ/መ/ቁ. 96548

 

መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ሌሊሴ ደሳለኝ

 

አመልካች፡- የሐያት ሆስፒታል ባለቤት አቶ ኢብራሂም ናውድ ጠበቃ ፍቅሬ ሞያ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን /የህፃን ሐምራዊ ቀለሙ ሞግዚት - ጠበቃ አሰፋ አሊ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ በወሊድ ወቅት በተጠሪ ሕፃን ላይ የደረሰውን የአካል ጉዳት በተመለከተ የጉዳት ካሳ ለማስከፈል የቀረበ  ክስን  መነሻ  ያደረገ  ክርክር  ነው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ  ሲታይ፡-  የስር ከሳሽ

/የአሁን ተጠሪ/ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበችው ክስ ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ሆስፒታል የነፍሰጡር ምርመራ ክትትል ሳደርግ ቆይቼ፣ መጋቢት 4 ቀን 1992 ዓ/ም በ2ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ይልማ አስረስ/ አዋላጅ ሀኪም አማካኝነት የወለድኩ ሲሆን የህፃን ሐምራዊ ቀለሙ እናት ከወሊድ በፊት በጥሩ ጤንነት ላይ የነበርኩኝ፤ በወሊድ ወቅት አዋላጅ ሐኪም በትክክለኛ የማዋለድ ሥርዓት የሙያ ግዴታቸውን መፈጸም ሲገባቸው ባለማድረጋቸው በቸልተኝነት ጉዳት የደረሰባት ልጅ እንድትወለድ አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ የጡንቻዎች መስነፍ፣ የብራካ መስለል፣ የቀኝ እጅ መስነፍ እና መዘርጋት ችግር አጋጥሟታል፣ ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ላይ በወሊድ ወቅት የደረሰባት ከፍተኛ የጤና ጉዳት ችግር ለወደፊት የትምህርት እና እንቅስቃሴ ቀጣይ ሕይወቷ ላይ ቋሚ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት እና ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ ስለዚህ ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ወደ ውጭ አገር ሄዳ ቀዶ ጥገና ሕክምና ማድረግ እንዳለባት በባለሙያ ስለተረጋገጠ ለውጭ አገር ሕክምና እና ለልዩ ልዩ ወጪ የሚያስፈልገው ብር 410,050  ለረዳት


ሰራተኛ ለወደ ፊት ለ60 ዓመት የሚያስፈልገው በወር ብር 171.00 ለ60 ዓመት ሲደመር 5 ፐርሰንት ጭማሪ 799,923 ፀጉሯን ለማሰራት 406,511 ለተሸከርካሪ ሾፌር ደመወዝ ብር 811,391 ለወደ ፊት ለምትወልዳቸው ሶስት ልጆች ተንከባከቢ ሰራተኛ ብር 72,000 ጂምና ለፊዚዮቲራፒ እንቅስቃሴ ብር 1,611,811 በጠቅላለው ብር 4,111,686.00 /አራት ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ ስድስት/ ስለሆነ እና በርትእ የሚወሰን የሞራል ካሳ እና ከሕጋዊ ወለድ ጋር ተከሳሾች በአንድነት እና በነጠላ እንዲከፍሉኝ፣ የወጪ ዝርዝር መብት እንዲጠበቅልኝ በማለት ከሳለች፡፡

 

ይህን ክስ በተመለከተ የሥር 1ኛ ተከሳሽ /የአሁን አመልካች/ በሰጠው መልስ፡- ከሳሽ የጉዳት ካሳ ክስ ለማቅረብ የሚችሉት ጉዳቱ በደረሰ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስለሆነ የቀረበው ክስ በይርጋ ይታገዳል፡፡ የ1ኛ ተከሳሽ ሆስፒታል በቂ መሣሪያዎች እና አስፔሻሊስት ሀኪም በማቅረብ አገልግሎት የሚሰጥ ስለሆነ የራሱ ጥፋት የለበትም፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በስፔሻልስት ደረጃ የተመረቁ በሙያ ስነ ምግባራቸውና ጠንቃቀነታቸው መልካም ስም ያተረፉ ናቸው፣ ከሳሽ ቅድመ ውሊድ ክትትል ተከሳሹ ጋር ነው ያደረጉት፡፡ የከሳሽ እናት ለወሊድ ስትመጣና ከወሊድ በኃላ የጤና ችግር ነበረባት፡፡ ከሳሽ ሐኪሙ ቸልተኛ ነው ከማለት ውጭ ትክክለኛ የማዋለድ ስርዓት ምን እንደሆነ አልገለፁም፡፡ የሐኪሙ የኃላፊነት መስፈርት ምን እንደሆነ በመግለጽ አላስረዱም፡፡ የሕፀኗ ችግር ወይም ጉዳት ከሳሽን ተጠያቂ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ካሳውን ለመጠየቅ የሕክምና ቦርድ ውሳኔ አልቀረበም፡፡ ልጅቷ ሁሉንም ስራዎች መስራት የምትችል መሆኑን የከሳሽ ማስረጃ ያሳያል፡፡ የተጠየቀው ካሳም የተጋነነ እና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡ ሕፃኗ  ወደ ውጭ ሄዳ የቀዶ ሕክምና ማድረግ አለባት የተባለው አይመለከተንም ከሆነም ደግሞ ህክምናውን በሕንድ አገር በአነስተኛ ወጪ ማግኘት ይቻላል በማለት ዘርዝሮ የካሳው ጥያቄ እንደማይመለከተው በመግለጽ ተከራክሯል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ /ዶ/ር ይልማ አስረስ መጥሪያ በጋዜጣ ተድርጎለት ባለመቅረቡ ጉዳዩ እሱ በሌለበት እንዲታይ ተደርጓል፡፡

 

ከዚህ በኃላ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በማከራከር፣ የከሳሽን የሰው  ምስክሮች  ቃል በመስማት፣ የቀረበውን የሰነድ ማስረጃ በመመዘን በሰጠው ውሳኔ፣ የከሳሽ ህፃን በ1ኛ ተከሳሽ ሆስፒታል እና በ2ኛ ተከሳሽ አዋላጅነት ስትወለድ በወሊድ ወቅት የ”ፎርሲፕስ” መሳሪያ በመጠቀም እንዲወልዱ በማድረጉ በህፃኗ የቀኝ እጅ ጡንቻ ስንፈት እንደተከሰተ በሽታውም የብራቪያስ ነርቭ መጎዳት ሲሆን ይህ በሽታ ሊከሰት የቻለው በወሊድ ጊዜ በደረሰ ጉዳት እንደሆነ የቀረበው ማስረጃ ያስገነዝባል፡፡ ተከሳሽ ይህን ማስረጃ በማስተባበል በገባው የወሊድ ውል መሠረት ኃላፊነቱን የተወጣ መሆኑን አላስረዳም፡፡ 2ኛ ተከሳሽም ያለውን የሙያ ብቃት ተጠቅሞ ከሳሽ ያለ ምንም እንከን የማወለድ ስራቸውን የሰሩ መሆኑን አያመለክትም፡፡ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም፣ የገባውን የማዋለድ ግዴታውን ሊወጣ ባለመቻሉ በከሳሽ ላይ ለደረሰው


ጉዳት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1790 /1/ መሰረት ኃላፊነት አለበት፡፡ 2ኛ ተከሳሽም ሥራቸውን ሲሰሩ የወሰዱትን እርምጃ የተከተሉትን ፕሮሲጀር ያልማዘገበ ሲሆን ከሕፃኗ ትልቅነት የተነሳ 2ኛ ተከሳሽ ከፎርሲፕስ የማዋለጃ መሳሪያ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደነበረበት እንደሚያስገድዱ ያመለክታል፡፡ ይህን መሳሪያ ለመጠቀም የታካሚዋን ፍላጎች መጠየቅ ሲገባው የህን አላደረገም፡፡ ስለዚህ 2ኛ ተከሳሽ በሙያቸው ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ማድረግ ባለመቻላቸው የደረሰ ጉዳት በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2028 እና 2031 መሰረት ኃላፊነት አለባቸው በማለት ወስኗል፡፡ የካሳውን መጠን በተመለከተ የጥቁር አንበሳ እስፔሻሊሽት ሆስፒታል በሰጠው ማስረጃ ከጠቅላለ የሰውነት ክፍሉ 55 ፐርሰንት አከባቢ መሆኑን ስላራጋገጠ የመዕከላዊ ስታትስቲክስ በጻፈው ዳብዳቤ በአዲስ አበባ የተወለደች የአንድ ሴት ልጅ አማካይ ዕድሜ 68.9 ዓመት እንደሆነ ገልጿል፡፡ ሕፃኑ ለወደ ፊት የመኖር ዕድሜዋ 59.1 ዓመት ነው፡፡ ከሳሽ በሁለት እጅ የሚሰሩትን ስራዎች መሥራት እንደማትችል ተረጋግጧል፡፡ በርካታ ሥራዎች ራሷን ችላ መስራት አትችልም፡፡ ስለዚህ ተከሳሾች በአንድነትና በነጣለ ከሳሽ ረዳት ሰራተኛ ለመቅጠር የሚያስፈልገውን ብር 689,049.32 ከሳሽ ውጭ አገር ሄዳ ለመታከም የሚያስፈልጋት ወጪ ብር 346,250፣ ከሳሽ ለጅምና ለፊዚዮትራፒ እና ለሰውነት እንቅስቃሴ የሚያሰልጋት ወጪ ብር

1,453,035.17 የሞራል ካሳ ብር 1000 በአጠቃላይ 2,489,334.49 የጉዳት ካሳ ገንዘብ ክስ ከቀረበበት ከታህሳስ 30 ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታሰብ 9 ፐርሰንት ወለድ ጋር ለከሳሽ እንዲከፍሏት በማለት ወስኗል፡፡ ወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብትም ጠብቋል፡፡ ከሳሽ ለፀጉር ማስሪያ ለሾፌር ደመወዝ ለወደፊት እወልዳለሁ ላለቻቸው ልጆች ለእንክብካቤ ያስፈልጋል በማለት የጠየቀችውን ወጪ በተመለከተ ፍ/ቤቱ ውድቅ በማድረግ ወስኗል፡፡ የሥር 1ኛ ተከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ይግባኙን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ ምክንያቱን በመግለጽ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔን የሚያስለውጥ የሕግም ሆነ የፍሬ ነገር ምክንያት አላገኘንም በማለት አጽንቷል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በ06/05/2006 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ ተጠሪ ሐኪሙ የፈፀመውን ቸልተኝነት የማስረዳት ኃላፊነት እያለባት ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ጉዳቱ የመጣው በተፈጥሮ መሆኑን ሐኪሙ ስህተት አለመፈጸሙን አመልካችም ሆነ ሐኪሙ አላስረዳም በማለት የማስረዳት ሸክሙን ማዞሩ የህግ አግባብ የለውም ፡፡ የሕክምና ታሪክ አለመመዝገብ ለተጠሪ ወሊዱ ችግር ያለበት መሆኑን አለማስረዳት በፎርሲፕርስ ለመውለድ የተጠሪን ፈቃደኝነት አለመጠየቅ በሕይወት ማዳን ጥድፊያ ጊዜ ሊታለፍ የሚችሉ ሲሆን ስህተት የሚሆኑት ጥድፊያ የሌለ መሆኑን ማስረዳት ሲቻል   ነው

፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ተጠሪ የመውለድ ሁኔታ ጥድፊያ ውስጥ ስለገባች ሐኪሙ ተገቢውን ወስኖ የሙያ ግዴታውን መወጣቱ በቸልተኝነት /ስህተት/ መኖሩን አያመለክትም፡፡ አመልካች   በበኩሉ


የጠራቸውን ሐኪሞች ምስክርነት የተወው የባለሙያ ምስክር በየትኛውም ወገን ቢቀርብ የሚመዘነው በመዕከላዊነት እና የባለሙያ ምስክር ለማስተባበል ሌላ የባለሙያ  ምስክር አይቀርብም በሚል መርህ ነው፡፤ አመልካች ግን ተጨማሪ የባለሙያ ምስክር ከኢትዮጵያ የማህጸንና ፅንስ ባለሙያዎች ማህበር እንዲቀርብለት የጠየቀው ማስረጃ አለመቅረቡ አለአግባብ ስለሆነ ሊቀርብልን ይገባል ፡፡ ተጠሪ በእንግሊዝ ሀገር በግል ሆስፒታል ውስጥ ከሚሰሩት የሕክምና ባለሙያ የተገኘ የሕክምና ዋጋ ተመን የእንግሊዝ ፓውንድ 9625 ከኢንተርኔት የተወሰደ የላኪው ማንነት የማይታወቅ ሰለሆነ እንደማስረጃ ሊወሰድ አይገባም በማለት አመልካች ቢከራከርም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ሰነድ የሰነድ ማስረጃ ከሚታወቅ ተቋም መቅረብ አለበት፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ገብቶ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት መመዝገብ አለበት፡፡ ይህ ሰበር ችሎትም በመዝ.ቁ .32282 ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ይህን የማይታወቅ የጉዳት ተመን እንደማስረጃ አድርጎ ወስዶ ውሳኔ መስጠት መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስለሆነ ውድቅ እንዲደረግልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

 

ይህ ሰበር ችሎት መዝገቡን በመመርመር ህፃን ሐምራዊ ቀለሙ በወሊድ ጊዜ የደረሰባት ጉዳት በቸልተኝነት ለመፈጸሙ የቀረበ ሙያዊ ማስረጃ ሳይኖር የኃላፊነት ውሳኔ በስር ፍ/ቤቶች ተሰጥቷል፡፡ ይህ ቢታለፍ የካሳ መጠኑን በተመለከተ የቀረበ ተጨማሪ ማስረጃ ሳይኖር በኢንተርኔት የተገኘን መረጃ መሰረት በማድረግ ወሳኔ የመሰጠቱን አግባብነት ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ በታዘዘው መሠረት የካቲት  03 ቀን 2006 ዓ.ም የተጻፈ መልስ ቀርቧል ፡፡ የመልሱም ይዘት ፡- የቀረበው ክርክር የፍሬ ነገር እና የማስረጃ ጉዳይ ሰለሆነ የዚህ ችሎት ስልጣን ስላልሆነ ሊስተናገድ አይገባም፡፡  የተጠሪን የማስረዳት ሸክምን በተመለከተ 1ኛ በሀኪሙ በኩል ግዴታ የነበረ መሆኑን፣ 2ኛ ሐኪሙ በውል ግንኙነት ሊፈጽም የሚገባውን ታካሚዋን የማዋለድ አገልግሎት ወይም እናት እና የልጅን በሰላምና በጤንነት የማለያየት ስራ አለመፈፀሙን 3ኛ የውል ግዴታውን ሙያው በሚጠይቀው ክህሎት ጥንቃቄና በተገቢው ሁኔታ ባለመፈፀሙ በህፃኗ ላይ የብራክያስ ነርቭ መጎዳት/የቀኝ ጡንቻ ሰንፈት /ጉዳት የደረሰባት መሆኑ ይህም በወሊድ ጊዜ ከውጭ በኃይል ጉተታ በደረሰ ጉዳት መሆኑን በተጠሪ በኩል በ12 ስፔሻሊስት ዶክተሮች ምስክርነት ፣በራሱ በአመልካች የተሰጡ የሰነድ ማስረጃዎች ፣ በአለርት ሆስፒታል፣ በቤተል ቲቺንግ ሆስፒታል በድንበሯ ሆስፒታል ፣ በኢንተርሜዲካል ዲያግኖስቲክ እና ኢሜጂንግ ማዕከል፣ በጥቁር አንበሳ የሐኪሞች ቦርድ፣ የተጎጂዋ የምስክርነት ቃል ጉዳቱንም ቀርባ ለፍ/ቤት አሳይታ በእናቷ እና በአባቷ የምስክርነት ቃል ያስረዳች ሲሆን በአመልካች በኩል አንዳችም የማስተባበያ መከላከያ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ከውጭ አገር የመጣውን አስፈላጊ የሆነውን የሕክምና ወጪን የሚያስረዳውን የሰነድ ማስረጃ በተመለከተ አመልካች በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት አልተመዘገበም፣በማስረጃነት


ሊታይ አይገባም በማለት ያቀረበው ክርክር በስር ፍ/ቤት ፈፅሞ ያልተነሳ ጉዳይ ስለ ሆነ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሊነሳ አይችልም፡፡ ታካሚዋ በወሊድ ወቅት ችግር ያለበት ወሊድ ምልክቶች/ Risk factors/ መኖራቸው ከታወቀ ባለሙያ ሐኪሙ በፎርሴፕስ /የብረት መጎተቻ መሣሪያ/ ተጠቅሞ ፅንሱን በኃይል ከመጎተት ሌሎች ጥንቃቄ የሚፈልጉ የሙያ ወሳኔዎችን መስጠት ነበረባቸው ፣ በነበረው ሁኔታ ግፊ ማለት አልነበረባቸውም ፣ በፎርሲፕስ መጎተት አልነበረባቸውም፡፡ ፎርሴፕስና ምጥ የሚያፋፍም መድኃኒት መጠቀም አልነበረባቸውም ፡፡ የሥር 2ኛ ተከሳሽ ይህን ሁኔታ በመገንዘብ ሌሎች አማራጭ ዘዴዎችን መጠቀም ነበረበት፡፡ ይህ ደግሞ የሐኪሙ ጥፋት መሆኑን ያመለክታል፡፡ የተጠሪ የባሙያ ምስክሮች ሁሉም እንዳስረዱት ሐኪሙ የታካሚዋ ካርድ ሪኮርድ አልተሞላም ፣ የተመዘገበ ነገር አልተገኘም፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት መሆኑን መስክሯል፡፡ ስለዚህ ተጠሪ አመልካችን ጨምሮ የስር ተከሳሾች ህፃኗ ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው በበቂ ማስረጃ ያረጋገጠች ስለሆነ አመልካች በማስረጃ ያስተባበለው ነገር ስለሌለ የሥር ፍ/ቤቶች የጉዳት ካሳውን እንዲከፍሉ የሰጡት ውሳኔ የማስረጃ ስህተትም ሆነ የሕግ መሰረት ስለሌለ የቀረበው አቤቱታ ፍሬ ነገር እና የማስረጃ ክርክር ስለሆነ ውድቅ ተደርጎ ወጪና ኪሳራ እንዲከፍል እንዲወሰንበት በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካች መጋቢት 01 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ የሠበር አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ እንደተመለከተ ሲሆን ፣ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው  የሕግ  ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ አቤቱታው ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንፃር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ከወሊድ በፊት የቅድመ ወሊድ ክትትል አመልካች ሆስፒታል ዘንድ ስታደርግ እንደነበር ግራ ቀኙ አልተካካዱም ፡፡ይህ ማለት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ሲባል አመልካች ዘንድ ቅድመ ወሊድ ክትትል ስታደርግ እንደነበር እና በወሊድ ወቅት ተገቢውን ሕክምና በማግኘት በሰላም ፣ጤናማ ልጅ ለመውለድ ሲባል እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡ አመልካች ደግሞ በሚያቀርበው ባለሙያዎች እና የሕክምና መሳሪያዎችን ተጠቅሞ በገባው ውል መሠረት ግዴታውን በሚገባ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ አንፃር የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2639፣2641፣2642 መመልከት ይቻላል፡፡ አመልካች ያለውን የሕክምና መሳሪያዎች እና ባለሙያዎችን አቀናጅቶ በወሊድ ወቅት እናትና ልጅን የመለያየት ስራ የሙያው ግዴታ በመወጣት እናትና ልጅን በሰላም እና በሙሉ ጤንነት ማለያየት አለበት፡፡ አመልካች ለሕክምና አገልገሎት የሚያስፈልገውን መሳሪያዎች ማቅረቡ ብቻ በቂ አይደለም ነገር ግን እንዚህን መሳሪያዎችን በመጠቀም ባለሙያው ያለውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ የማዋለድ ውሉ የሚጥልበትን ግዴታ መፈፀም አለበት፡፡ አመልካች ለሕክምናው የሚያስፈልገውን መሳሪያዎች ቢያቀርብም እንኳን የሥር 2ኛ ተከሳሽ እነዚህ መሳሪያዎችን


በመጠቀም የሕክምና ሙያው የሚጠይቀውን ሄደት በመጠበቅ ተጠሪን በሙሉ ጤንነት ካላዋለደ ከተጠያቂነት የሚያመልጥበት ሁኔታ የለም የአመልካች ተቀጣሪ ሰራተኛ የሆነው የሥር 2ኛ ተከሳሽ የሙያ ሰነ-ምግባሩ የሚጠይቀውን ሁሉ በመፈፀም እውቀቱን እና ክህሎቱን በመጠቀም ከአንድ አዋላጅ ሐኪም የሚጠበቀውን ሁሉ ያደረገ እንደሆነ እና ከዚህ ውጭ በሆነ ለምሳሌ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት በእናትም ሆነ በተወለደች ሕፃን ላይ ጉዳት የደረሰ እንደሆነ አመልካችንም ሆነ የሥር 2ኛ ተከሳሽን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ይሆናል ፡፡ አመልካችም ሆነ የሥር 2ኛ ተከሳሽ ከተጠያቂነት ነፃ ለለመሆን 2ኛ ተከሳሽ ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ሙያው በሚጠይቀው መሰረት የፈፀመ መሆኑን አግባብነት ባለው ማስረጃ ያስረዱ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አመልካች የሕክምና አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ሐኪሙ የሚጠበቅበትን ግዴታ መወጣቱን በቅድሚያ የማስረዳት ግዴታ/ሸክም የእርሱ ነው፡፡ አመልካች የሱ ተቀጣሪ ባለሙያ የሕክምና ሙያው በሚጠይቀው መሠረት ምንም ስህተት ፣ጥፋት፣ ቸልተኝነት ሳይኖር ስራውን መስራቱን በቅድሚያ የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም የሕክምና አገልግሎት ውሉን በገባ ጊዜ በወሊድ ወቅት እናትና ልጅን በሰላምና በሙሉ ጤንነት ለመለያየት ግዴታ ስለገባ ነው ታካሚዋ በሕክምና ወቅት ጉዳት የደረሰባት እንደሆነ የሕክምና አገልግሎት ሰጭውን ተቋም እና ሐኪሙ ለደረሰባት ጉዳት ተጠያቂ ናቸው በማለት በኃላፊነት የመጠየቅ መብት አላት፡፡ ይህን ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.2647 /2/ እና 2651 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ ይቻላል አመልካችም ሆነ ሐኪሙ ደግሞ በወሊድ ወቅት ምንም አይነት ስህተትም ሆነ ቸልተኝነት አለመፈፀሙን በተሻለ ማስረጃ የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው ፡፡ ከዚህ በኋላ ታካሚዋ የአመልካች ሐኪም ጥፋት የፈፀመ መሆኑን በማስረጃ የማስተባበል፣ በማስረጃ የማስረዳት ሸክም አለባት፡፡

 

በዚህ አግባብ አሁን የተያዘው ጉዳይ ሲታይ ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ተጠሪን በወለደች ወቅት ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ጉዳት እንደደረሰባት አመልካችም አልካደም፡፡ ከዚህም በላይ አመልካች የሰጠው ማስረጃን ጨምሮ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ በወሊድ ወቅት አካላዊ ጉዳት የደረሰባት  መሆኑን  የሚያስረዳ  መሆኑን  በሥር  ፍ/ቤት የተረጋገጠ  ፍሬ ነገር   ነው

፡፡አመልካች በካርድ ው.12058 በ22/03/2000 ዓ.ም በፃፈው ሰነድ ሐምራዊ ቀለሙ ስትወለድ ክብደቷ 4.3 ኪ.ግ እንደሆነች፣የቀኝ እጅ ክንድ መስነፍ፣ የብራኳ መስለል የነበረባት እንደሆነ፣ የብራሺጋያል ፓልሲ የሚባል የነርቭ በሽታ እንዳለባት እና ይህ በሽታ በወሊድ ጊዜ በደረሰ ጉዳት የተከሰተ መሆኑን ፣ሕፃኗ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባት ያመለክታል ፡፡ ሌላው ከአለርት አገር አቀፍ ሪፈራል ማዕከል ፣ ኦፕሬሽናል ቴራፒ ምርመራ አገልግሎት ማስረጃ ድንበሯ የእናቶችን ሕፃናት ሆስፒታል ፣ኢንተርሜዲካ ዲያግኖስቲክ እና ኢሜጂንግ ማዕከል ፣ቤተል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል ፣ከፕሪንሰስ ግሬስ ሆስፒታል የቀረቡ ማስረጃዎች ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ በወሊድ ወቅት በደረሰባት ጉዳት በክሱ ላይ የተጠቀሰው የአካል ጉዳት የደረሰባት መሆኑን


እንዲሚያረጋግጥ የሥር ፍ/ቤቶች አመለክቷል፡፡ የተጠሪ የሰው ምስክሮችም በሰጡት የምስክርነት ቃል ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ የተባለው ጉዳት የደረሰባት እንደሆነ  መመስከራቸውን የሥር ፍ/ቤቶች መዝገብ ያመለክታል፡፡

 

የሰው ምስክሮች እንዳመለከቱት 2ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ይልማ አስረስ ወ/ሮ አስቴርን ሲያዋልዱ የተከተሉትን ፐሮሲጀር እና የወሰዱትን እርምጃዎችና አማራጮችን አለመመዝገቡን መመስከራቸው የሥር ፍ/ቤት አረጋግጧል፡፡ ይህም በመንግስት ሆስፒታል ለምሳሌ እንደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንኳን ሙሉ ለሙሉ እንደማይተገበር ምስክሮች ገልፀው፣ይህ ማለት ግን ይህን አለመመዝገብ ትክክል ነው ማለት እንዳሆነ አስረድተዋል ፡፡ ይህ ደግሞ የአመልካች ባለሙያ የነበረው አዋላጅ ሐኪም /የሥር 2ኛ ተከሳሽ / ሙያው በሚጠይቀው መሰረት ተጠሪን ሲያክም ለምን የተወሰደውን አማራጭ ሊወሰድ እንደቻለ አለመመዝገቡ በራሱ ጥፋት መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሐኪሙ ይህን ባለመመዝገቡ የወሰዳቸው እርምጃዎች/ አማራጮች ልክ ነበሩ ለማለት የሚያስችል ነገር የለም ሐኪሙ /የሥር 2ኛ ተከሳሽ/ ለምን ምጥ የሚያፋፍም መድኃኒት እና ፎርሲፕስ መሳሪያ ተጠቅሞ ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙን በመጎተት እንድትወለድ እንዳደረገ ምንም የሚያመላክት ነገር የለም ፡፡ የአመልካች ባለሙያ ይህን የታካሚዋን ታርክ በአግባቡ ባለመመዝገቡ አመልካች አሁን ላይ ቆሞ ባለሙያው ያን ጊዜ የወሰደውን እርምጃ ልክ ነው በማለት በማስረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖሩ የክርክሩ ሄደት አያሳይም ይህ በእንዲህ እንዳለ አመልካች በበኩሉ 2ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙን በምትወልድበት ወቅት የወሰደው እርምጃ ትክክል እንደነበረ ህፃኗ ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት ከሐኪሙ ጥፋት ጋር የማይገናኝ እና ምንም አይነት ቸልተኝነት እንደሌለበት ለማስረዳት ምንም አይነት ማስረጃ አለመቀረቡን እሱም አይክድም የስር ፍ/ቤቶችም ይህንን በሚገባ አረጋግጠዋል፡፡ አመልካች የሥር 2ኛ ተከሳሽ እናትና ልጅን በሙሉ ጤንነት እንዳለያየ ምንም አይነት ማስረጃ ባለቀረበበት በውሉ መሰረት ግዴታውን እንደተወጣ አስመሰሎ የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት የሚያገኝበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ አመልካች ተቀጣሪ ሐኪሙ /የሥር 2ኛ ተከሳሽ/ ሙያው በሚያዘው መሰረት ታካሚዋን በሚያዋልድበት ወቅት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ሳይመዘግብ ሲቀር ተከታትሎ ማስተካከል ሲገባው አሁን ባለሙያው ይህን አለማድረጉ እንደጥፋት አይቆጠርም በማለት የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡ አመልካች በሥር ፍ/ቤት ባቀረበው መልስ የሰው ማስረጃ ዝርዝር ስር የኢትዮጵያ የማህጸንና የፅንስ ባለሙያዎች ማህበር እንደማስረጃ የጠቀሰ ሲሆን፣ የሰው ማስረጃ ማሰማት አልፈልግም በማለት የሥር ፍ/ቤት እንዲያልፍ ካደረገ በኋላ ፣ይህ ማስረጃ አይደለም በማለት ያቀረበው ክርክርም  የማስረጃ አቀራረብና አቀባበል መርህን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች  አመልካች  እና  ሐኪሙ  ዶ/ር  ይልማ  አስረስ  የሚጠበቅባቸውን  የውል  ግዴታ


ባለመወጣታቸው በሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት ኃላፊነት ስላለበት የጉዳትካሳም ለመክፈል ግዴታ አለባቸው በማለት የሰጡት ውሳኔ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.1790፣2028፣2031፣2647 /2/ እና 2651/ አንጻር ሲታይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው ሆኖ አግኝተናል፡፡

 

የካሳውን መጠን አወሳሰን ስንመለከተም ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ሁለት እጆቿን በመጠቀም ሁሉንም ስራ መስራት እንደማትችል የተጠሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ማረጋገጣቸውን የሥር ፍ/ቤቶች መዝግቧል፡፡ በዚህ ምክንያት የሥር ፍ/ቤቶች ለሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ አጋዥ ሰው እንደሚያስፈልጋት በፍሬ ነገር ደረጃ አረጋግጦል ፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ በተለያዩ ስራዎች ሕፃኗን የሚያግዝ ሰው በነጻ ያለ ክፍያ ማግኘት ይቻላል ተብሎ ስለማይገመት ክፍያ እንደሚያስፈልግ የሚያከራክር አይሆንም ፡፡ ነገር ግን ሕፃኗ ለመስራት ለማትችላቸው ስራዎች ስራተኛ ቀጥሮ ለማሰራት ለወደ ፊቱ በየወሩ እና በየአመቱ ይህን ያህል ገንዘብ ይከፈላል ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2102 መሰረት ዳኞች በርትዕ የካሳን መጠን የመወሰን ስለጣን እንዳለቸው ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ ይህ ችሎት እንደተገነዘበው ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ለወደ ፊቱ ሕይወቷን ምቹ ለማድረግ መሥራት የማትችላቸውን ሥራዎች የሚያግዛትን ሰራተኛ ለመቅጠር ለረዳት ሰራተኛ በርትዕ ብር 300‚000 /ስስት መቶ ሺህ ብር /ያስፈልጋታል ብለናል፡፡ ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ጤንነቷን በመልካም ሁኔታ ለመጠበቅ የአካ እንቅስቃሴ፣ ጂምና ፈዚዮትራፒ እንደሚያስፈልጋት በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ይህም ደግሞ ለወደፊቱ በሳምንት ፣በወር ይህን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል ለማለት የሚያስቸግር ስለሆነ በርትዕ ግን ለመወሰን እንደሚቻል ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ በዚህም መሠረት ሕፃኗ ለወደ ፊት ጂምና ፊዚዮትራፒ የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስፈልጋት ወጪ በርትዕ ብር 500‚000/አምስት መቶ ሺህ/ ሊከፈላት ይገባል ብለናል፡፡

 

ሌላው ሕፃን ሐምዊ ቀለሙ ለደረሰባት የአካል ጉዳት ወደ ውጭ አገር ሄዳ ጥገና ሕክምና ማድረግ እንዳለባት እና ለዚህም ወደ እንግሊዝ አገር ሄዳ ለመታከም በአጠቃላይ ብር   346‚250

/ሶስት መቶ አርባ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ / ለተጠሪ ሊከፈል ይገባል በማለት የሥር ፍ/ቤት የሰጡትን ውሳኔ በተመለከተ አመልካች ባቀረበው ተቃውሞ ፣ይህ ማስረጃ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ገብቶ በውልና ማስረጃ ስላልተመዘገበ  እንደማስረጃ  መወሰድ አልነበረበትም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን አመልካች ሚያዝያ 13 ቀን 2002 ዓ.ም በከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበው መልስ ይሀን ማስረጃ በተመለከተ ያቀረበው ክርክር ቢኖር ሕንድ አገር ተመሳሳይ አገልግሎት በአፖሎ ሆስፒታል በጣም አነስተኛ በሆነ ወጪ ለማግኘት እንደሚቻል ለመጠቆም እንወዳለን የሚል ነው፡፡ ስለዚህ አመልካች ከዚህ ውጭ የአቀረበው ማሰረጃ ተቀባይነት የለውም በማለት አሁን የሚያነሳውን ክርክር በሥር ፍ/ቤት በማንሳት የተከራከረው ነገር ባመኖሩ በዚህ ሰበር


ችሎት ይህን ማስረጃ በተመለከተ ያቀረበው አዲስ ክርክር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.329 /1/ መሰረት ተቀባይነት የለውም ፡፡ ይህ በመሆኑ የሥ/ፍ/ቤቶች ሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ወደ ውጭ አገር ሄዳ ለመታከም የሚያስፈልጋት ወጪ የወሰኑት ገንዘብ በምንም መልኩ የተጋነነ አይደለም ብለናል፡፤ ስለዚህ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍ/ቤቶች የካሳ መጠን በተመለከተ የሰጡትን ውሳኔ ብቻ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መሰረት በማሻሻል በአብላጫ ድምፅ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳኔ

 

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.90681 መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.89303 በ30/03/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ የካሳ መጠንን በተመለከተ ብቻ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት በድምፅ ብልጫ ተሻሽሏል፡፡

2. አመልካች እና የሥር 2ኛ ተከሳሽ በሕፃን ሐምራዊ ቀለሙ ላይ በወሊድ ወቅት ለደረሰባት የአካል ጉዳት ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ፣ በአንድነትና በነጠላ በፍርድ ሐተታው ውስጥ በዝርዝር እንደተመለከተው በአጠቃለይ ብር 1‚147‚250.00/አንድ ሚሊዬን አንድ መቶ አርባ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር/ የጉዳት ካሳ ለተጠሪ ሊከፍሏት ይገባል ብለናል፡፡

3.  የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ ብለናል፡፡

4.  ግራ ቀኙ በዚህ ችሎት ለደረሰባቸው ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

5.  በዚህ መዝገብ ላይ የተሰጠ ዕግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡

6.  የሥር ፍ/ቤት መዝገብ እንደመጣ ይመለስ ብለናል፡፡

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 የ ል ዩነ ት ሀ ሳብ

 

ህጻኗ የቀኝ እጅ የነርቭ መስነፍ ጉዳት የደረሰባት መሆኑ፤ ጉዳቱም የደረሰው በወሊድ ጊዜ መሆኑ እና የደረሰውም የስር 2ኛ ተከሳሽ ፎርሴፕስ (forceps) በተባለ የማወለጃ መሳሪያ ተጠቅመው የህፃኗን እናት ባዋለዱበት ጊዜ መሆኑ የልተካዱ እና የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች ናቸው፡፡ ተጠሪዋ ካሰሟቸው ምስክሮች መካከል ከፊሎቹ በማወለድ የህክምና ሙያ ልዩ ዕውቀት ያላቸው የህክምና ባለሙያዎቸ ናቸው፡፡ ጉዳቱ የደረሰው በአመልካች ሆስፒታል ውስጥ ይሰሩ የነበሩት የስር 2ኛ ተከሳሽ የማዋለድ ተግባሩን ባከናወኑበት ጊዜ ሆን ብለው ወይም በቸልተኝነት የሙያ ግድፈት ወይም ጥፋት በመፈጸማቸው ምክንያት ስለመሆኑ ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል    አንዳቸውም


አረጋግጠው ያልመሰከሩ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ በግልጽ ያመለክታል፡፡ የባለሙያዎች የምስክርነት ቃል ይዘት የማዋለድ ተግባሩ በፎርሴፕስ መሳሪያ በሚከናወንበት ጊዜ በሚወለዱት ህጻናት ላይ አሁን መከሰቱ የተረጋገጠው ዓይነት ጉዳት ሊደርስ የሚችል መሆኑን የሚያስገነዝብ ከመሆኑ በቀር የስር 2ኛ ተከሳሽ የማዋለድ ተግባሩን በፎርሴፕስ ባከናወኑበት ጊዜ አሁን የተከሰተው ጉዳት እንዳይከሰት ማድረግ ይችሉ የነበረ ስለመሆኑ ወይም በሌላ አነጋገር ጉዳቱ የተከሰተው በሙያ ግድፈት ምክንያት ስለመሆኑ የሚያመለክት አይደለም፡፡ በፎርሴፕስ መሳሪያ ማዋለድ ያልተፈቀደ ተግባር ሰለመሆኑም አልተገለጸም፡፡

 

በባለሙያዎች የተሰጠው ምስክርነት የማዋለጃ ስርዓቱን ወይም መሳሪያውን የመምረጥ እና የመወሰን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ለአዋላጅ ሐኪሙ የተተወ መሆኑን እና የስር 2ኛ ተከሳሽ የተመሰከረላቸው ብቁ ባለሙያ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ በርግጥ ምስክከሮቹ አዋላጅ ሒኪሙ በዘርፉ ከሚታወቁት የማዋለድ ስርዓቶች ወይም ዘዴዎች መካከል አንዱን ወይም ሌላኛውን የመረጠበትን ምክንያት በሕክምና ካርዱ ላይ ከተቻለ በማዋለዱ ሂደት የሁኔታዎች አጣዳፊነት ካላስቻለውም የማዋለዱ ተግባር ከተጠናቀቀ በኃላ መመዝገብ እንደሚገባው የሙያው ስነ ምግባር የሚያዝ መሆኑን ሐኪሙ እንደኛውን ወይም ሌላኛውን የማዋለድ ዘዴ የተጠቀመባቸውን ነባራዊ ሁኔታዎች መገንዘብ እና ተገቢ ስለመሆን አለመሆኑ ሙያዊ አስያየት መስጠት የሚቻለው ከዚህ ዓይነቱ ምዝገባ መሆኑን እና በተያዘው ጉዳይ ግን ሐኪሙ ምዝገባውን ስላላከናወኑ በፎርሴፕስ የማዋለጃ መሳሪያ መጠቀማቸው ስህተት ነበር ወይስ አልነበረም የሚል አስተያየት ለመስጠት የማይችሉ መሆናቸውን ገልጸው መስክረዋል፡፡ የስር 2ኛ ተከሳሽ ምዘገባውን አላከናወኑም መባሉ በህጻኗ ላይ መድረሱ ከተረጋገጠው ጉዳት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ ዓይነቱ የመመዝገብ ሁኔታ የመንግስት ትላልቅ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ያልተለመደ እና የማይተገበር መሆኑን  እና  እራሳቸውም ቢሆኑ በሙያው ላይ በቆዩባቸው በበርካታ ዓመታት የሙያው ስነ ምግባር የሚጠይቀው ነው ያሉትን መረጃዎችን መዝግቦ የመያዝ ሁኔታ ተግባራዊ አድርገው የማያውቁ መሆኑን ጭምር እነዚሁ የተጠሪ ምስክሮች ገልጸዋል፡፡ በመሠረቱ የአንድን ሙያ ስነ ምግባር በሙያው ላይ የተሰማራ አንድ ሰው ሙያውን በቀሰመበት ቆይታ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ይህ በትምህርት ቆይታ የተገኘ ነው የሚባለው የሙያ ስነ ምግባር የፍትሐብሔር ኃላፊነትን ለማስከተል በሚያስችል ሁኔታ ተጥሶአል ለማለት የሚቻለው በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2031 (1) አነጋገር መሰረት የሙያ ስራው የሚመራበት ደንብ ወይም በፍትሕብሔር ሕግ ቁጥር 2647 (1) አነጋገር መሠረት የሙያው የኪነ ጥበብ ደንብ መሆኑ ሲረጋገጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ በተያዘው ጉዳይ የመመዝገቡ ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ ያልተለመደ እና የማይተገበር መሆኑ በተጠሪዋ ምስክሮች የተገለጸ እስከሆነ ድረስ የምዝገባው ሁኔታ የሙያ ስራው የሚመራበት ደንብ ወይም የሙያው የኪነ ጥበብ ደንብ ነው


ከሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በመሆኑም ውሳኔው ተሸሮ አንድ አዋላጅ ሐኪም በዘርፉ ከተፈቀዱት የማዋለድ ስርዓቶች ወይም ዘዴዎች መካከል አንዱን ወይም ሌላኛውን የመረጠበትን እና የተጠቀመበትን ምክንያት መዝገቦ የማስቀመጡ ጉዳይ በሚመለከተው የመንግስት አካል ታውቆ እና ተረጋግጦ የሙያ ስራው የሚመራበት ደንብ ነው በሚያሰኝ ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ ዕውቅና እና ተቀባይነትን አግኝቶ በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች እየተተገበረ መሆን አለመሆኑ ወደ ስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመልሶ ተጨማሪ ማጣራት ሊደረግበት ይገባ ነበር በማለት ስሜ በተራ ቁጥር ሶስት የተመለከተውን ዳኛ የልዩነት ሀሳቤን አስፍሬአለሁ፡፡

 

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ፡፡