108251 extracontractual liability/ damage assessment/ equity

የካሳን መጠን በርትዕ ለመወሰን የሚያስገድድ ሁኔታ በገጠመ ጊዜ መጠኑን ለመወሰን የጉዳት ካሳው መጠን ከጉዳቱ ተመጣጣኝ ይሆን ዘንድ ሚዛን ላይ ሊቀመጡ የሚገባቸው መለኪያዎች ሊኖሩ የሚገባ ስለመሆኑ፣ የፍ/ሕ/ቁ.2102 እና 2153

 

የሰ/መ/ቁ. 108251 ቀን ጥር 5/2008ዓ.ም

ዳኞች፡-  ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ

አመልካች፡- የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የጎዴ ደናን መንገድ ፕሮጀክት

 

-ነ/ፈ አብርሃም አሰፋ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- አቶ አመካክ ከሊፋ                       -አልቀረቡም፡፡

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

የሰበር አቤቱታ የቀረበው የሸበሌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. M/S/Sh – 60/2006 ግንቦት 26 ቀን 2007ዓ.ም እንዲሁም የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 05-1-185/06 ህዳር 5ቀን 2007ዓ.ም ያሳለፉትን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡

 

የአሁን ተጠሪ በዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ አመልካች ድርጅት በቆፈረው የውሃ መሄጃ ጉድጓድ ልጃቸው መሃመድ አመካክ ከሊፋ ህዳር 12/2006ዓ.ም ጉድጓዱ ውሃ  ሞልቶ በቸልተኝነት ሳይሸፈን በመቅረቱ ምክንያት ገብቶ ስለሞተ ለደረሰባቸው ጉዳት አመልካች ሃላፊ እንዲባልና ልጁ የ4ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ ከትምህርት ሰዓት በኋላ በአህያ ውሃ እየቀዳ ለሰፈር ነዋሪዎች በበርሚል 25ብር በመሸጥ በቀን የስምንት በርሚል ብር 200.00 በወር ብር 6000.00 ለቤተሰቡ ገቢ በማስገባት ደረጃ ስለነበር ትምህርቱን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ታስቦ በጠቅላላ ብር 564,000.00፤ እንዲሁም የሞራል ካሳ ብር 1,000.00 እና የቀብር ማስፈጸሚያ ብር 25,000.00 እንዲከፈላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡


የአሁኑ አመልካች ለክሱ መቃወሚያ እና በሃላፊነት ሆነ በጉዳቱ መጠን ላይ የበኩሉን ክርክር አቅርበዋል፡፡

 

የስር ፍ/ቤት ክርክሩን እና ማስጃዎችን ሰምቶ አመልካች ለጉዳቱ ሀላፊነት አለበት በማለት ካሳውን በርትዕ አስተያየት በመወሰን ብር 500,000.00 /አምስት መቶ ሺህ/ እንዲከፈል ፈርዷል፡፡ ይግባኙ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ አመልካች የስር ፍ/ቤት ጉዳዩን ተቀብሎ ለማከራከር ስልጣን የለውም በማለት የሚያቀርቡትን መከራከሪያ በተመለከተ አስቀድሞ የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ክሱን የስር ፍ/ቤት ተመልክቶ እንዲወስን በመለሰለት መሰረት ታይቶ የተወሰነ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ለጉዳቱ ሃላፊ መደረጉ በአግባቡ መሆኑን፣ እንዲሁም የካሳውን መጠን በተመለከተ የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ /የጎዴ አካባቢ/ በሙሉ ልጆቹን ውሃ በአህያ እያስቀዳ የሚያሰራቸውና የኑሮ መሰረታቸው ስለመሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ፍርዱ እንዲጸና ወስኗል፡፡

 

የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን በመቃወም ነው፡፡ አመልካች ታህሳስ 21,2007ዓ.ም ያቀረቡት የሰበር ማመልከቻ ተመርምሮ ሟች የ8 ዓመት ልጅ የነበረ ከመሆኑ አኳያ ውሃ በመሸጥ በየወሩ ያለማቋረጥ ብር 6000 ያስገኝ ነበር ተብሎ በስር ፍ/ቤቶች በእርግጠኝነት ተቀባይነት ማግኘቱ ከህግም ሆነ ከልማዳዊ አሰራር አንጻር ተገናዝቦ የተሰጠ መሆን አለሞኑን ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ግራቀኙ ክርክራቸውን በጽሑፍ እንዲለዋወጡ ትእዛዝ የተሰጠ ቢሆንም ተጠሪ መጥሪያ ደርሷቸው እንዳልቀረቡ አመልካች በቃለ መሃላ የተደገፈ አቤቱታ ስላቀረቡ በጽሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፎ መዝገቡ ለምርመራ ቀጠሮ ይዟል፡፡

 

ከላይ ባጭሩ የገለጽነው የጉዳዩን አመጣጥ ሲሆን ቅሬታ ያስነሳውን ውሳኔ ከተያዘው ጭብጥ እና ከህጉ ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

 

አመልካች የስር ፍ/ቤት በህግ ከተሰጠው በገንዘብ መጠን የተወሰነ የዳኝነት ስልጣን በላይ ተመልክቶ የሰጠው ውሳኔ በመሆኑ ስልጣን በሌለው ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ እንዳልተሰጠ እንዲቆጠር በሰበር ቅሬታቸው ያመለከቱ ቢሆንም በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ እንደተመለከተው ይኸው መከራከሪያቸው ታልፎ ጉዳዩ በስር ፍ/ቤት ታይቶ እንዲወሰን ሲመለስ በወቅቱ ጉዳዩን በሰበር አቅርበው እንዲታረም ያላደረጉ በመሆኑ ቅሬታው ክርክሩ አሁን በደረሰበት ደረጃ የሚቀርብ አይደለም ብለናል፡፡

 

ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተ የስር ፍ/ቤት የካሳውን መጠን በርትዕ የወሰነ ሲሆን አመልካች የካሳው መጠን እጅግ የተጋነነ እና ካሳው ከደረሰው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት በህጉ


ከተደነገገው ውጭ የተወሰነ መሆኑን በመጥቀስ ውሳኔው መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው እንዲባል ጠይቀዋል፡፡

 

በመሰረቱ ጉዳት መድረሱ ምክንያታዊ የሆነ እርግጠኝነት ሲኖር እና የካሳውን መጠን ለመወሰን አስቸጋሪ ሲሆን ዳኞች በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2102 መሰረት የካሳውን መጠን በርትዕ እንዲወስኑ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ተጎጂው የ4ኛ ክፍል ተማሪ የነበረና እንደ አካባቢው ህጻናት ውሃ በአሕያ በመቅዳት ቤተሰቡን ይረዳ እንደነበር ቢታወቅም በህጻኑ ሞት ምክንያት የቀረው ጥቅም መጠን በትክክል ለማስላት ስለሚያዳግት በርትዕ መወሰን ተገቢ ይሆናል፡፡ ነገር ግን  የካሳ መጠኑ ያላግባብ እንዳይጋነንም ሆነ ያላግባብ እንዳይቀንስ በተቻለ መጠን የጉዳት ካሳው መጠን ከደረሰው ወይም ወደፊት ሊደርስ ከሚችለው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ውሳኔ መስጠት ይገባል፡፡ ስለሆነም በርትዕ በሚወሰንበት ጊዜም ቢሆን የጉዳት ካሳው መጠን ከጉዳቱ ተመጣጣኝ ይሆን ዘንድ ሚዛን ላይ ሊቀመጡ የሚገባቸው መለኪያዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2153 እንደተደነገገው ዳኞች ሊገምቱት የሚገባቸውን የነገሩን አጋጣሚ ሁኔታ በአግባቡ በመያዝ፣ ሊገምቱ የሚገባቸውን ትክክለኛውን መንገድ በመያዝ፤ ከአእምሮ ግምት ውጭ ያልሆነ፤ ከዝንባሌ የጸዳ ውሳኔ እንዲሰጡ ይጠበቃል፡፡

 

የካሳውን መጠን በርትዕ ለመወሰን የሚያስገድድ ሁኔታ በገጠመ ጊዜ መጠኑን ለመወሰን ከግምት ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ሁኔታዎች ወይም መለኪያዎች ካልተመለከቱ የሚሰጠው ውሳኔ ስሜትን መሰረት የሚያደርግ እና የሕጉን አላማ የሚስት በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በተያዘውም ጉዳይ የካሳው መጠን የተሰላበት ሁኔታ እና ለስሌቱ ግምት ውስጥ የገቡ ሁኔታዎች (መለኪያዎች) በግልጽ ሳይመለከቱ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል፡፡ ተከታዩንም ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1ኛ. የሸበሌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. m/s/sh/60/2006 ግንቦት 26/2006ዓ.ም ያሳለፈው እና በሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 05-1-185/06 ህዳር 5/2007ዓ.ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

 

2ኛ. አመልካች ለጉዳቱ ሃላፊ ነው መባሉ በአግባቡ በመሆኑ ይኸው የውሳኔ ክፍል ጸንቷል፡፡


 

 

3ኛ. የካሳውን መጠን በተመለከተ በርትዕ መወሰኑ የሚነቀፍ ባይሆንም መጠኑን ለመወሰን ያስቻለው ሁኔታ ወይም መለኪያዎች ባልተመለከቱበት እና ይህ ነው የሚባል መነሻ ምክንያት ሳይሰጥ አመልካች ለተጠሪ ብር 500,000.00 /አምስት መቶ ሺህ/ እንዲከፍል የተሰጠው ውሳኔ ህጉን የተከተለ ባለመሆኑ ተሽሯል፡፡

 

4ኛ. የከፍተኛው ፍ/ቤት መዝገቡን በማንቀሳቀስ የካሳውን መጠን በህጉ አግባብ እንዲወሰን ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሕ/ቁ. 343(1) መሰረት መልሰናል፡፡

 

5ኛ. ጉዳዩ በሰበር ሲታይ ስላስከተለው ወጪ አመልካች የራሱን ይቻል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

መ/ይ