113464 criminal procedure/ criminal law/ participation in crime/ standard of proof

በወንጀል ጉዳይ ከአንድ በላይ ሰዎች የተከሰሱ እንደሆነ የእያንዳንዱ ተከሳሽ ሚና እና ተሳትፎ ደረጃው በቂና አሳማኝ በሆነ ሁኔታ በከሳሽ ወገን በኩል በሚቀርበው ማስረጃ ነጥሮ ሊወጣ የሚገባ ስለመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32፣40 የወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 141 ተያያዥነት የሌላቸው ፍሬ ነገሮችን መሰረት ተደርጎና የአንድን ነገር መኖር ያለመኖር ሣይረጋገጥ ለአካባቢ ማስረጃ ክብደት መስጠት የማስረጃው አይነት የምዘና መርህን መሰረት ያደረገ ነው ለማለት የሚቻል ስላለመሆኑ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.173(1)

 

የሰ/መ/ቁጥር 113464

 

ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

 

 

አመልካች፡- 1. እናት ሁናቸው

 

2. ባለው እንደወቅቱ

 

3. ሃብታሙ ሁነኛው       የቀረበ የለም

 

4. በልስቲ ሁነኛው

 

 

 

ተጠሪ፡- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካቾች እና ስንሻው አለሙ በተባለው ግለሰብ ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱም ይዘት፡- ተከሳሾች በ1996 ዓ/ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ወንጀል አንቀፅ 32(1(ሀ)) እና 671(2) ስር የተደነገገውን መተላለፍ የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት አስበው ጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ/ም ከምሽቱ በግምት 4፡00 እስከ 6፡00 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ጎዛመን ወረዳ ማይ አንገታም ቀበሌ ከአሁኗ 1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ውስጥ     አቶ


ውባለም ግዛቸው ይባል የነበረውን በአሰቃቂ ሁኔታ ደብድበው ገለው እሬሳውን ከሻይ ቤት ራቅ አድርገው ጥለውት ይዞት የነበደርን ባለሰደፍ ክላሽ ጠመንጃ የወሰዱበት መሆኑን ዘርዝሮ ተከሳሾች ከባድ የውንብድና ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡ የአሁኑ አመልካቾችም ሆነ የሥር 1ኛ ተከሳሽ የነበረው አቶ ስንሻው አለሙ ፍርድ ቤት ቀርበው የአቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ተነቦላቸው እንዲረዱት ከተደረገ በሁዋላ እምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን ክደው በመከራከራቸው አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን አራት ምስክሮቸ ቆጥሮ ሶስቱን ፍርድ ቤት አስቀርቦ አስምቷል፡፡ ከዚህም በሁዋላ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የማጣሪያ ምስክሮችን መስማት አስፈላጊ ነው ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶ የ1ኛ አመልካች ጎረቤት ናቸው የተባሉትን ግለሰብ የምስክርነት ቃል በመቀበልና የፖሊስ የምርምራ መዝገብ ሁሉ አስቀርቦ አይቶ አመልካቾች እንዲከላከሉ ተደርጎ የመከላከያ ማስረጃዎች ቀርበው ተሰምተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ማስረጃዎች መርምሮ 1ኛ ተከሳሽ የነበረው አቶ ስንሻው አለሙ በመከላከያ ማስረጃዎቹ የአቃቤ ሕግን ማስረጃዎችን አስተባብሎአል በማለት ከክሱ በነጻ ያሰናበተ ሲሆን የአሁኑን አመልካቾች ግን  በመከላከያ ማስረጃዎቻቸው የአቃቤ ሕግ ማስጃዎችን አላስተባበሉም በማለት በአቃቤ በኩል ተጠቅሶ በቀረበባቸው ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ በማድረግ እና የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበል የቅጣት አወሳሰኑን ከተሻሻለው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 አንፃር በማየት የወንጀሉ ደረጃ በእርከን 38 ስር እንደሚወድቅ ከለየና ለሁሉም አመልካቾች ሁለት ሁለት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ ወደ እርከን 36 አውርዶ በዚሁ እርከን ስር አመልካቾች እያንዳንዳቸውን በ18 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ በመወሰን በስር 1ኛ ተከሳሽ እጅ ተያዘ ተብሎ በኢግዚቢትነት የተያዘው የጦር መሳሪያም የዚሁ ሰው መሆኑ ተረጋግጦ እንዲመለስላቸው በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

በዚሀ ውሳኔ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ ከዚህም በኋላ የሰበር ኤቱታቸውን  ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱ በአመልካቾች ላይ የተሰጠውን የጥፋተኝት ውሳኔ አፅንቶ የቅጣት ውሳኔውን ብቻ ከመመሪያ ቁጥር 1/2002 አንጻር መታየት እንደነበረበት በምክንያትነት ይዞ አመልካቾች በስር ፍርድ ቤት በተያዘላቸው ሁለት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች በእያንዳንዱ ሶስት ሶስት እርከን መቀነስ እንዳለበትና በዚህም ስሌት መሰረት ቅጣቱ ወደ እርከን 32 እንደሚወርድ ገልፆ በዚሁ እርከን ለፍርድ ቤቱ በተተወው ፍቅድ ስልጣን መሰረት እያንዳንዳቸው በአስራ አራት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ በማለት ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

አመልካቾች ሚያዚያ 29 ቀን 2007 ዓ/ም በጻፉት ሶስት ገፅ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ የሰበር አቤቱታው መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካቾች ጥፋተኛ ተብለን እንድንቀጣ የተወሰነው አቃቤ ሕግ


ምስክሮች በአይን ባላዩትና የስሚ ስሚ ምስክርነት ነው፣ በመከለካከያ ማስረጃዎችም የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል አሰተባብለናል በማለት ዘርዝረው የበታች ፍርድ ቤቶች የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ እንዲሻር ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ የሚገባው መሆኑ ታምኖበት ተጠሪን ያስቀርባል ተብሎ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ተጠሪ ቀርቦ በቁጥር ወየሂ/4173/መ/ቁ95/908 በቀን 21/01/2008 ዓ/ም በተፃፈ አራት ገፅ ማመልከቻ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የተሰጠው በሚታመን የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል መሆኑን ዘርዝሮና ውሳኔው ተገቢነት ያለው መሆኑን በመግልፅ ውሳኔው ሊጺና የሚገባው መሆኑን ጠቅሶ የጹሑፍ መልሱን ሰጥቷል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ተብሎ ሲታዘዝ ከተያዘው ጭብጥ ፣ ከድርጊቱ አፈፃጸም ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ የተያዘው  ጭብጥ አመልካቾች ጥፋተኛ ተብለው በስር ፍርድ ቤቶች የመቀጣታቸውን አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ነው፡፡

 

አመልካቾች ጥፋተኛ የተባሉት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 671 (2) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ከባድ የውንብድና ወንጀል ፈጽመዋል፣ ውባለም ግዛች ይባል የነበርን ግለሰብ ደብድበው ገድለው ሬሳውን ከሻይ ቤት ራቅ አድርገው ጥለው ይዞት የነበረውን ባለሰደፍ ክላሽ ጠመንጃ ወስደዋል በሚል ምክንያት ሲሆን አመልካቾች ድርጊቱን መፈጻማቸውን ክደው ተከራክረውም አቃቤ ሕግ ሶስት የሰው ምስክሮችን አሰምቷል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም ለትክክለኛ ፍትህ ሲል ማጣሪያ ምስከሮችን ከመስማቱም በላይ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ሁሉ አስቀርቦ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ የሕግ ማስረጃዎች ታይተውም አቃቤ ሕግ እንደክሱ አስረድቷል የሚል እምነት የበታች ፍርድ ቤቶች ደርሰዋል፡፡ ለጉዳዩ በማስረጃነት የተሰሙት ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል ይዘትም የሚከለተው መሆኑን የስር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ ያሳያል፡፡

 

አቶ ታዬ ብርሃን የተባል የአቃቤ 1ኛ ምስክር በሰጠው የምስክርነት ቃል በክሱ በተገለፀው ቀንና ቦታ ማታ ተከሳሾችና ሟች ሻይ ቤት ከምስክሩ ጋር ገብተው እንደነበር፣ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት እንተኛ ተባብለው ይኼው ምስክርና አሊ የተባለው የአቃቤ ሕግ ምስክር ለሽንት ወጥተው ወደ አሁኗ 1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ሲመለሱ የኩራዝ መብራት ጠብቶ የሽመልና የብርጭቆ ኳኳታ ድምጽ  ሰምተው አሊ የተባለው ምስክር ምንድን ነው ሲል ምን ሰማህ ብሎ የስር 1ኛ ተከሳሽ የነበረው አቶ  ስንሻው አመራ መሳሪያ ሲያቀባብል ደንግጠው በመሮጥ ይኼው ምስክሩና አሊ የተባለው ምስክር ተበታትነው ከውጭ አድረው ከዚያ በነጋታው ውባለም ሞተ ተብለው ምስክሩ ከሟች ጋር የጋብቻ ዝድምና እንዳለው፣ ከበረሃው በእዛው እለት ድርጊቱ ተፈጸመ ወደ ተባለበት ሐሙሲት ከተማ ምስክሩ ሊሄድ


የቻለውም ሟች ዱቁት ይሰጣችኃል ተብሎ መሆኑንና በዚህ ምክንያት ድርጊቱ ሲፈፀም ማየቱን እንዲሁም ከ1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ የገቡ መሆኑን ገልጾ መስክሯል፡፡

 

አቶ አሊ መኮንን የተባለው የአቃቤ ሕግ ምስክር በበኩሉ እንደ አቶ ታዬ ብርሃን በተመሳሳይ መመስከሩን ፍርድ ቤቱ ገልፆ የምስክርነቱን ቃል ዝርዝሩን በውሳኔው ላይ አላሰፈረውም፡፡ ቄስ ማማሩ ደመወዝ የተባለው የአቃቤ ሕግ ሶስተኛ ምስክር ደግሞ በክሱ በተገለጸው ቀን በነጋታው ጥዋት ከአገራቸው ወደ ሃሙሲት ከተማ ሞባይል ካርድ ሊሞሉ መጥተው ሳለ ሟች ሞተ ተብሎ ፖሊስ እንደአሰጠራቸው፣ የሟች አስክሬን ከወደቀበት ቦታ ሂደው ሲመለከቱም የሟችን መታወቂያ፣ዱላ፣ ሽመልም ያገኙ መሆኑን፣ ከአሁኗ 1ኛ አመልካች ቤት እስከ ሟች አስክሬን የደም ነጠብጣብ መመልከታቸውን እንዲሁም አልኮል የተቀባ የቁስል ማሸጊያ/ፋሻ/ ማግኘታቸውን፣ የአሁኑ  4ኛ አመልካች በስለት ተቆርጦ ታሽጎ ማየቱንና የሟችን አስክሬን ወደ አገሩ መውሰዳቸውን እንዲሁም ምስክሩም ራሱ ተጠርጥሮ ታስሮ እንደነበር፣ ነገር ግን ድርጊቱን እንዳልፈፀሙ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ማን ነው የሚለውን ያጣራ መሆኑንና ከሟች ጋር በገንዘብ ተጣልተው በሽማግሌ የታረቁ መሆኑን፣ የሙሉ ቢተው ሚስት አቃቤ ሕግ በክሱ በገለፀው እለት አህያ ከውጭ ታስሮ ነበር፣ ድምፅ የአህያው ሳይሆን ሰው ሲያጓጉርና ሲንፈራገጥ ሰማሁ በማለት ለአለኽን ሚስት ተናግራ አለኽኝ ደግሞ ለምስክሩ የነገራቸው መሆኑን፣ አቃቤ ሕግ በክሱ በገለጸው እለት ሟች መሳሪያ ይዞ ከሟች አበጀ መንግስቴ ያስፈጨውን ዱቄት ከፋንታ ምስጋናው ማስቀመጡን መስማቱን፣ ሟች ልደር ብሏት ወንድ የለም ብዬ መልሼዋለሁ ብላ የነገረቻቸው መሆኑንና የሟችን አስክሬን መጀመሪያ ያገኘው ልጃለም ስንታየሁ ነው በማለት መስክሯል፡፡ ከዚኅም በኃላ ፍርድ ቤቱ የአሁኗ አመልካች ጎረቤት ሰው ሲያጓጉር   ሰምቻለሁ ብላ ተናግራለች ተብሎ በሶስተኛ የአቃቤ ሕግ ምስክር በመገለፁ ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ያመች ዘንድ ምስክሯ ቀርባ እንድትሰማ ትዕዛዝ ሰጥቶ ምስክሯ ቀርባ የተሰማች ሲሆነን ምስክሯ በሰጠችው የምስክርነት ቃልም የአሁኗ 1ኛ አመልካች ጎረቤታቸው መሆናቸውን ገልፀው ጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ/ም ምሽት የሰሙት ድምጽ የለም፣ አህያም ከውጭ አልታሰረም በማለት የመሰከረችና ምስክርነቱ በዚሁ ያበቃ ሲሆን የሥር ፍርድ ቤት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በማየት ድምጽ መሰማቱን፣ አህያ መስሎኝ ነው እንጂ በማለት መገለጹን አገንዝቦ አልፎታል፡፡ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ መዝገቡን በመመርመር ዱቄት 1ኛ እና 2ኛ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲያመጡ ላካቸው የተባለውን ስንሻው ጎሹ የተባለውን ግለሰብ ቀርቦ እንዲሰማ ትዕዛዝ ሰጥቶ የክፍሉ ፖሊስ ሰንሻው ጎሹ የተባለ ግለሰብ እንደሌለና ሊያገኘው ያለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ በመግለፁ ምክንያት ይኼው ግለሰብ በተጨማሪ ማስረጃነት ሳይሰማ ታልፎአል፡፡

 

በመሰረቱ አንድ ሰው ወንጀል አደረገ የሚባለው ሕገወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ የተደነገገን ድርጊት ፈጽሞ በተገኘ ጊዜ መሆኑ እና አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለውም ወንጀሉን የሚቋቁሙት ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑ በወ.ሕ.አ. 23  (1)


እና (2) ስር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን ማንም ሰው በዋና ወንጀል አድራጊነት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣው በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር ወንጀሉን ያደረገ በሆነ ጊዜ ወይም ወንጀሉን እርሱ በቀጥታ ባያደርገውም እንኳን በመላ አሳቡና አድራጎቱ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ድርጊቱን የራሱ ያደረገ በሆነ ጊዜ ስለመሆኑም በወ.ሕ.አ. 32(1) ስር ተደንግጎአል፡፡ በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ የክስ ማመልከቻ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል እንዲሁም የወንጀሉ መሰረታዊ ነገርና ሁኔታዎች የተገለጹበት ሊሆን እንደሚገባ እና ስለ ወንጀሉና ስለሁኔታው የሚሰጠው ዝርዝር መግለጫ ተከሳሹ ፈጸመ የተባለውን ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን እንደሚገባው በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 111 እና 112 ድንጋጌዎች ላይ የተደነገገውም ከሳሹን ወገን በወ.ሕ.አ. 23(2) ስር የተመለከቱት የወንጀል መማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸውን ለማስረዳት እንዲያስችለው መሆኑን ከድንጋጌዎቹ ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር ከሳሽ ወገን በክሱ መሰረት የማስረዳት ግዴታ ተወጥቶአል ሊባል የሚችለው ቀደም ሲል በተጠቀሱት የወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 111 እና 112 ድንጋጌዎች መሰረት አዘጋጅቶ ባቀረበው የክስ ማመልከቻ መሰረት ተከሳሹ ወንጀል መፈጸሙን ማስረዳት በቻለ ጊዜ ነው፡፡ ክሱ የቀረበለት ፍ/ቤትም ተከሳሹ መከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ክሱን እንዲከላከል በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 142 መሰረት ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚችለው ከሳሽ ወገን ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያደርገው መሆኑን ሲያረጋግጥ ስለመሆኑ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 141 ስር በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ከአንድ በላይ ሰዎች በተከሰሱበት የወንጀል ጉዳይም የእያንዳንዱ ተከሳሽ ሚና እና የተሳትፎ ደረጃው በቂና አሳማኝ በሆነ ሁኔታ በከሳሽ ወገን በኩል በሚቀርበው ማስረጃ ነጥሮ ሊወጣ የሚገባ መሆኑን ስለመወንጀል አፈፃጸም ተካፋይ መሆን የሚመለከቱ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች በተለይም አንቀፅ 32 እና 40 እና የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 141 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የሚያስገነዝቡን ጉዳይን ነው፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ በዐ/ሕግ በኩል በቀረበው የአካባቢ ማስረጃ የተረጋገጡት መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች ሟች ከ1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ገብተው እንደነበርና በሻይ ቤቱ ከሟች ጋር ነበርን ያሉት 1ኛ እና 2ኛ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ከሻይ ቤቱ ለሽንት ወጥተው ሲመለሱ በቤቱ የነበረው የኩራዝ መብራት ጠፍቶ የሽመልና የብርጭቆ ኳኳታ ሰምተው ምንድነው የሚለውን ጥያቄ 2ኛ የአቃቤ ሕግ ምስከር ሲያቀርብ በስር 1ኛ ተከሳሽ ተከሳሽ የነበረውና በመከላከያ ምስክሮች የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል አስተባብሎአል ተብሎ በነጻ የተሰናበተው አቶ ስንሻው አመራ የጦር መሳሪያ ሲያቀባብሉ 1ኛ እና 2ኛ ምስክሮች ደንግጠው የራሳቸውን ሕይወት ለማትረፍ ተበታነው ሸሽተው አድረው በበነጋው ሟች ሞተ ተብሎ እንደተነገራቸውና የሟች አስክሬንም ከአሁኗ 1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ራቅ ብሎ ተጥሎ መገኘቱን ነው፡፡

 

በመሰረቱ እነዚህ ፍሬ ነገሮች ደግሞ ብቻቸውን በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 141 ስር በግልጽ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ዐ/ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያደርግ    ነው


ለማለት የሚያስችሉ አይደሉም፡፡ ዐ/ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ሟቹ በአመልካቾቹ ተገድሏል ለማለት የማያስደፍር ስለመሆኑ የምስክሮች ዝርዝር የምስከርነት ቃሉ አያሳይም፡ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች በተለይ 1ኛ እና 2ኛ ምስክሮች ሟችን ከእነማን ጋር እንደነበር ከማየታቸው ውጪ አመልካቾቹ በወንጀሉ ድርጊት የነበራቸውን ሚና፣ ተሳትፎና ደረጃውን ገልጸው የመሰከሩ አይደሉም፡፡ አመልካቾች በጊዜና በቦታው ነበሩ ስለተባለ ብቻ ግን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚያስችል የወንጀል ጉዳይ ማስረጃ ምዘና መርህ የለም፡፡ እያንዳንዱ አመልካች በወንጀሉ የነበረው ተሳትፎና ደረጃው በቂ በሆነ ሁኔታ መረጋገጥ ያለበት ሲሆን ይህ ካልሆን ግንሞ ፍ/ቤቱ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 141 መሰረት ተከሳሽን ማሰናበት የግድ የሚል እንጂ ተከሳሹ የመከላከያ  ማስረጃ  እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠት የሕግ መሰረት አይኖረውም፡፡ ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካቾች በሟች ሕይወት ማለፍ የነበራቸው ተሳትፎ ተለይቶ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ከሟቹ ጋር ነበሩ ስለተባሉ ብቻ ድርጊቱን እንደፈጸሙ በአቃቤ ሕግ ምስክሮች ተረጋግጦባቸዋል ተብሎና በመጨረሻም የዐ/ሕግን ማስረጃ አላስተባበለም በማለት በአመልካቾች ላይ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መስጠታቸው ከላይ የተመለከቱትን መሰረታዊ የሆኑ የወንጀል ሕግ እና የወንጀል ስነስርዓት ሕግ ድንጋጌዎችን የጣሰ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የተጠሪ ምስክሮች በወቅቱ  ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ /circumstantial Evidence/ የሠጡ ናቸው ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች  የተገለጸው የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ ስለ አከባቢ ማስረጃ ምዘና መርህ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ ለአንድ የአከባቢ ማስረጃ ክብደት ለመስጠት ማስረጃው ጠንከራ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የአከባቢ ማስረጃ ስለጉዳዩ በቀጥታ የማይነግረን በመሆኑ የተወሰኑ ፍሬ ነገሮች መኖራቸው ወይም ያለመኖራቸው ሲረጋገጥ ወደ አንድ ድምዳሜ የምንደርስበት የማስረጃ አይነት ነው፡፡ ስለመሆኑም ፍሬ ጉዳዮቹ ተያያዥነት ያላቸውና ጠንከራ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ተያያዥነት የሌላቸው ፍሬ ነገሮች መሰረት ተደርጎና የአንድን ፍሬ ነገር መኖር ያለመኖር ሳይረጋገጥ ለአከባቢ ማስረጃ ክብደት መስጠት የማስረጃው አይነት የምዘና መርህን መሰረት ያደረገ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡ በአገራችን የህግ ሥርዓት ምስክሩ ስለአጠቃላይ ሁኔታዎች በአይኑ የታዘበውን በጆሮው የሰማውንና የሚያውቀውን ፍሬ ጉዳይ ሊስመሰክር እንደሚችልና የምስክሩም ቃል ህጋዊ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 137 ንዑስ አንቀፅ 1 ድንጋጌ ይዘት መንፈስና ዓላማ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግን የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ቃል የአከባቢ ማስረጃ ከሚመዝንበት እና የስሚ ስሚ ማስረጃውም ለጉዳዩ በማስረጃነት ከሚሰድበት አግባብ ወጪ የመሰከሩ ናቸው ከሚባል በስተቀር በቂና አሳማኝ በሆነ ሁኔታ የአመልካቾችን የወንጀሉን ተሳታፊነት ያረጋገጡ ናቸው ተብሎ የሚወሰዱ ሁነው አልተገኘም፡፡ በስር ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ የነበረው ግለሰብ በ1ኛ እና 2ኛ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ሟች ሞተ በተባለበት ሻይ ቤት በመሳሪያ ያስፈራራቸው ስለመሆኑ የተነገረ ቢሆንም ይህ ግለሰብ ከወንጀሉ ነፃ ከመውጣቱም በላይ ከሟች ተወሰደ የተባለው


መሳሪያም በኢግዚቪትነት የተያዘ ስለመሆኑ ያለመረጋገጡም የአመልካቾችን የወንጀል ተሳታፊነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተው ሁኖ አግኝተናል፡፡ አቃቤ ሕግ በዚህ ሰበር ችሎት አመልካቾች ተጠያቂነት የለባቸውም ተብሎ ቢወሰን በወንጀል ፍትህ ስርዓቱ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተዕጽኖ ገልፆ መከራከሩ አመልካቾች በወንጀሉ የነበራቸውን ተሳትፎና በወንጀል ጉዳይ ማስረጃ የሚመዘንበትን መርህ መሰረት ያላደረገና የሕግ መሰረት የሌለው በመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡

 

ሲጠቃለል ከሳሽ ዐ/ሕግ በአመልካቹ ላይ ባቀረበው የግፍ ግድያ የወንጀል ክስ መሰረት ለማስረዳት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ባልወጣበት ሁኔታ ክሱን የተመለከተው የዞን አንድ ከ/ፍ/ቤት ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ የሰጠው ትዕዛዝም ሆነ በመጨረሻ የሰጠውና በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት በትዕዛዝ የፀናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ በአብላጫ ድምጽ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.    በምስራቅ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት  በመ.ቁ. 0206782 ጥር 26  እና የካቲት

06 ቀን 2006 ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ./ቁጥር

09870 መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ/ም የፀናውና በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት 39613 በ12/06/2007 ዓ.ም. የተሻሻለው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 195(2)(ለ)(1) መሰረት በድምጽ ብልጫ ተሽሮአል፡፡

2. ተጠሪ ባቀረበው ማስረጃ አመልካቾች ወንጀሉን ማድረጋቸውን  ያላስረዳ  እና በሕግ የተጣለበትን የማስረዳት ግዴታ ያልተወጣ በመሆኑ አመልካቾች ከተከሰሱበት የከባድ ውንብድና የወንጀል ክስ በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል በማለት ወስነናል፡፡

3. በአመልካቾች ላይ ተጥሎ የነበረው የአስራ አራት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት የተሻረ በመሆኑ የሚፈለጉበት ሌላ ጉዳይ አለመኖሩን አረጋግጦ አመልካቾችን ዛሬውኑ ከእስር እንዲለቃቸው ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይተላለፍ፡፡ ይፃፍ፡፡

4. እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች እና ለአውሲረሱ ማረሚያ ቤት ይላክ፡፡ ለአመልካቹም በዚያው በኩል ይድረስ፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቶአል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት


 

 

 የ ልዩነት ሐሳ ብ

 

ሰሜ በ5ኛ ላይ የተጠቀሰው ዳኛ የአብላጫ ድምጽ ከሰጠው ውሳኔ እንደሚከተለው በመለየት ሐሳቤን አስቀምጣለሁ፡፡ ከዚህ መዝገብ ውስጥ መረዳት እንደሚቻለው ተጠሪ ያቀረበው ክስ የስር 1ኛ ተከሳሽ እና የአሁን አመልካቾች የወ/ህ/ቁ.32/1፣ሀ/ እና 671(2) በመተላለፍ ጥቅምት 22 ቀን

2004 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት እስከ 6፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ የግል ተበዳይ ዉባለም ግዛቸው የሚባለውን በአሰቃቂ ሁኔታ ደብድበው ገድለው እሬሳውን ጥለው ይዞት የነበረውን ጠመንጃ የወሰዱ በመሆኑ ከባድ የውንበድና ወንጀል ፈጽመዋል ተከሷል፡፡ አመልካቾች ፍ/ቤት ቀርበው በሰጡት የእምነት ክህደት ቃላቸው ወንጀሉን አልፈጸምንም በማለት  ክደው ተከራክረዋል፡፡ ከዚህ በኃላ ፍ/ቤቶች የግራ ቀኝ የሰው ምስክሮች በመስማት ተጨማሪ የሰው ማስረጃ መስማት፣ የፖሊስ ማስረጃ በማስቀረብ በማየት በሰጡት ውሳኔ የስር 1ኛ ተከሳሽ አቶ ስንሻው አለሙ ከክሱ በነጻ በማሰናበት፣ የአሁን አመልካቾችን በተከሰሱበት ወንጀል  ጥፋተኛ ናቸው በማለት የእስራት ቅጣት የወሰኑ መወሰናቸውን መገንዘብ  ይቻላል፡፡ አመልካቾችን ወንጀሉን አልፈጸምንም፣ በመከላከያ ምስክሮቻችን ተከላክለናል፣ የስር ፍ/ቤት የጥፋተኝነትም ሆነ የእስራት ውሳኔ ተሽሮ በነጻ እንዲንሰናበት የሚል አቤቱታ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል፡፡ ተጠሪ በበኩሉ አመልካቾች የተከሰሱበተን ወንጀል ስለመፈጸማቸው የዐ/ህግ ምስክሮች በሚገባ ስላረጋገጡ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ እንዲጸናልን በማለት መልስ አቅርበዋል፡፡

 

የግራ ቀኙ ክርክር የስር ፍ/ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ ካረጋገጡት ነገሮች አንጻር ማይት አስፈላጊ ነው፡፡ የዐ/ህግ 1ኛ እና 2ኛ ምስክሮች የወንጀል ድረጊቱ ተፈጸመ በተባለ ቀን ምሽት በሟች ጋር 1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደነበሩ፣ ሟችን እዛው ትተው ለሽንት ወጥተው ስመለሱ የሻይ ቤቱ መብራት ጠፍቶ የሻይ ብርጭቆና የአረቄ መለኪከ ኳኳ የሚል ድምጽ እንደሰሙ፣ ዓሊ የተባለው ምስክር ምንደነው ብሎ ሲጠይቅ የስር 1ኛ ተከሳሽ ምን ሰማህ በማለት መሳሪያ ሲያቀባብል ለህይወታቸው ፈርተው ሸሽተው እንደሄዱ መስክሯል፡፡ 3ኛ ምስክር ደግሞ በሰጠው ቃል ጠዋት ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ ሟች ወድቆ ሞቶ እንደገኘ ሟች ከወደቀበት እስከ ከ1ኛ አመልካች ቤት የደም ነጠብጣብ መኖሩን መስክሯል፡፡

 

ስለዚህ እነዚህ የዐ/ህግ ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል ሲታይ የአከባቢ ማስረጃ ይሁኑ እንጂ ከሟች ጋር የ1ኛ አመልካች ሻይ ቤት እንደነበሩ እና ሌሎች አመልካቾች እዛው እንደነበሩ ሟችን ሻይ ቤቱ ውስጥ ትተው ለሽንት ወጥቶ ስመለሱ የሻይ ቤቱ መብራት ጠፍቶ የሻይ ብርጨቆ እና የአርቄ መለኪያ ኳኳታ ድምጽ እንደሰሙ እና 1ኛ ተከሳሽ ወደ ቤት


እንዳይገቡ አድርጓቸው ለሕይወታቸው ሲሉ ሸሽቶ ከቦታው መሄዳቸው ሲታይ ሟች ከዚህ ሻይ ቤት እንደነበር ያመለክታል፡፡ ሟች በዚህ ሻይ ቤት ውስጥ ከምስክሮች ጋር  እንደነበረ በመረጋገጡ፣ ሟች ከምስክሮቹ ጋር አብሮ ወጥቶ መሄዱ እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ ምስክሮቹ ከሄዱ በኋላ እንኳን ወጥቶ መሄዱ እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ ሟች በ1ኛ አመልካች ሻይ ቤት እያለ የተገደለ መሆኑን ያመልክታል፡፡ በዚህ ሻይ ቤት ውስጥ በዛን ሰዓት ከአመልካቾች በቀር ሌላ ሰው መኖሩን የሚያረጋግጥ ነገር የለም፡፡ አመልካቾች በ1ኛ አመልካች ሻይ ቤት ውስጥ እያሉ ሟችም እዚያው ሻይ ቤት ውሳጥ እያለ የግዱያ ወንጀል የተፈጸመበት በመሆኑ አመልካቾች ውጭ ሌላ ሰው ይህን የግድያ ወንጀል ፈጸሟል ለማለት የሚያስችል ነገር የለም፡፡ ከዚህም በላይ የስር ፍ/ቤቶች የፖሊስ ምርምራ መዝገብ ማስቀረበ ያዩ መሆናቸውን መዝገቡን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ እነዚህ የዐ/ህግ ምስክሮች የአከባቢ ምስክሮች ቢሆኑም አመልካቾቹ ሟች ዉባለም ግዛቸው የሚባለውን ሰው ገድለው ይዞ የነበረውን ጠመንጃ መውሰዳቸውን ለማስረዳት በቂ ማስረጃ (sufficient evidence) ሊሆን የማይችሉበት ምንም ተጨባጭ ምክንያት የለም፡፡ ይህ በመሆኑ የስር ፍ/ቤት አመልካቾች በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.142(1) መሰረት መከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው እንዲከላከሉ ብይን መስጠታቸውን በአግባቡ ነው፡፡

 

በመቀጠል መታየት ያለበት ጉዳይ አመልካቾች ባቀረቡት የሰው ምስክሮች የዐ/ህግ ምስክሮች የሰጡትን የምስክርነት ቃል ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል ወይ? የሚለውን ነጥብ መልስ ማግኘት ያለበት ነገር ነው፡፡ አመልካቾች መከላከያ ምስክሮቻችው ቃል ሲታይ 1ኛ አመልካች ቤት መጥተው ቆይተው የሄዱ ጊዜ፣ እሮንድ መጠበቃቸው፣ ሌሎች ተከሳሾች 1ኛ አመልካች ቤት ስለመግባታቸው ጋር ተያይዞ የሰጡት ቃል የዐ/ህግ ምስክሮችን ጥርጣሪ ውስጥ አስገብቷል ለማለት የሚያስችል አይደለም፡፡ የመከላከያ ምስክሮች በተጠቀሰው ምሽት 1ኛ አመልካች ቤት ሻይ ወይም አረቄ ለመጠጣት ሟች እና የዐ/ህግ ምስክሮች በእርግጠኝነት አለመምጣታቸውን ያመሰከሱት ነገር የለም፡፡ እነዚህ ምስክሮች በእርግጠኝነት ሟች እና የዐ/ህግ ምስክሮች አለማምጣታቸውን ካላረጋገጡ ደግሞ የዐ/ህግ ምስክሮች የሰጡትን ቃል ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱበት አቅም አይኖራቸውም፡፡ ይህ በመሆኑን የስር ፍ/ቤቶች አመልካቾች  የዐ/ህግ ምስክሮችን የቀረቡት የመከላከያ ምስክሮች ጥርጣሬ ላይ በመጣል አመልካቾች ተከላክለዋል የሚያስብላቸው ነገር ባለመኖሩ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠታቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በአዋጅ 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረት ሲታይ የስር ፍ/ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጡትን እውነታ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት መቀበል ይገበዋል፡፡ በመሆኑም የምስራቅ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት እና አማራ ብ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት እና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለውም እላለ፡፡


ቅጣትን በተመለከተ የአማራ ብ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው የጽኑ እስራት ቅጣት ሊጸና ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ሊጸና ይገባል እንጂ አመልካቾች ነጻ እንዲሰናበቱ የሚያበቃቸው ምክንያት የለም በማለት የልዩነት ሐሰቤን አስቀምጣለሁ፡፡

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

ሃ/ወ