94913 criminal law/ corporate criminal liability

አንድ ድርጅት ወንጀል እንዳደረገ የሚቆጠረው ከኃላፊዎች አንዱ ወይም ከሠራተኞች አንዱ ከድርጅቱ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የድርጅቱን ጥቅም በሕገ ወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ወይም የድርጅቱን ሕጋዊ ግዴታ በመጣስ ወይም በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት ወይም አነሳሽነት ወይም አባሪነት ወንጀል ሲፈጸም ብቻ ስለመሆኑ፣ የወ/ሕግ አንቀጽ 23 እና አንቀጽ 34/1/ ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 93/1ሀ/ እና 93/2/

 

የሰ//.94913

ህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማዉ ወሌ

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻዉ አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት - ዓ/ሕግ አቤል ገ/እግዚአብሔር - ቀረቡ

ተጠሪዎች፡-   1. ጆሳምቢን ትሬዲንግ ኃ/የግ/ማህበር       ከጠበቃ አለማየሁ ታደሰ ጋር - ቀረቡ 2. አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ አርጋዉ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለዉን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

ይህ የሰበር ጉዳይ ከጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ጋር በተያያዘ ተፈጸመ የተባለዉን የማጭበርበር ወንጀል የሚመለከት ክርክር መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ፡- የሥር ከሳሽ

/የአሁን አመልካች/ በምስራቅ ሻዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበዉ ክስ ተከሳሾች የጉምሩክ አዋጅ ቁ.622/2001 አንቀጽ 93 /1/ (ሀ) እና 93 /2/ በመፈተላለፍ ቻይና አገር የተመረቱን ዕቃዎች ከዉጭ አገር ለማስገባት የንግድ ፈቃድ አዉጥቶ፣ ዕቃዎቹ ሞጆ ደረቅ ወደብ ገብቶ ሲፈተሽ በዲክላራስዮን ቁጥር C-10951 በ20/12/2012 እ.አ.አ. እና ይህን በሚደግፍ ሰነድ ላይ ያልተሞለዉን መለያ ያለዉ ቬትናም አገር የተመረተ እና የጫማ ሳጥን በማስገባት ቀረጥ እና ታክስ ብር 3,328,524.38 መከፈል ያለበትን ብር 931,799.33 በመክፈል በልዩነት ብር 2,396,725.05 ሳይከፍል ዝቅተኛ ቀረጥና ታክስ በመክፈል ዕቃዉ ወደ አገር ወስጥ እንዲገባ ስላደረገ በማጭበርበር ወንጀል ተከሷል የሚል ነዉ፡፡

የሥር 2ኛ ተከሳሽ /የአሁን 2ኛ ተጠሪ/ ፍ/ቤት ቀርቦ ክሱ ተነቦለት በሰጠዉ ቃል በዚህ የወንጀል ድርጊት ምንም ዓይነት ተሰትፎ የለኝም ምክንያቱ በዲክላራስዮኑ ሰነድ ላይ ከተጠቀሱት ዕቃዎች ዉጭ የላከዉ ከዉጭ አገር ዕቃዎቹን የላከዉ ካመፓኒ የፈጸመዉ ስህተት ነዉ እንጂ የተከሳሽ ተሳትፎ የለም በማለት ገልጸል፡፡

ከዚህ በኃላ ፍ/ቤቱ የዐ/ሕግ ምስክሮችን በመስማት፣ 2ኛ ተከሳሽ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.142 /3/ መሰረት የሰጠዉን ቃል በማየት በሰጠዉ ዉሳኔ ተከሳሽ ከዉጭ የመጠዉን ዕቃዎች ያወቀዉ


በሞጆ ደረቅ ጣቢያ ሲፈተሸ እንደሆነ የዐ/ሕግ ምስክሮች ገልጸዋል፤ ዕቃዉ የመጣዉ ከተከሳሽ ጥያቄ ዉጭ በመሆኑ፣ ላኪዉ ካመፓኒ የራሱ ስህተት እንደሆነ እና ተከሳሹ በሰጠዉ ቃል የላኪዉ ካምፓኒ ስህተት እና ከእርሱ እዉቅና ዉጭ እንደሆነ በመግለጹ በወ/ሕ/ቁ.23 /2/ መሰረት ወንጀል ለመፈጸም የሐሰብ ክፍል ስላልተሟላ፣ ተከሳሽ ሊጠየቅ አይገባም በማለት በወ/ሕ/ቁ.149 /2/ መሰረት ነጻ ነዉ በማለት ወስኗል፡፡ የሥር ከሳሽ ይህን ዉሳኔ በመቃወም ይግባኙን ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ችሎት በማቅረቡ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ ተከሳሾች ይህን ለመፈጸም የሀሳብ ክፍል የለም በማለት ከክሱ ነጻ ነዉ በማለት የሰጠዉ ዉሳኔ የሚነቀፍ አይደለም፣ በዕቃዎቹ ላይ መከፈል ያለበትን ቀረጥና ታክስን በተመለከተ ዕቃዎቹ ላይ መከፈል ባለበት ላይ በተከፈለዉ መካከል በቅናሽ የሚፈለግ ክፍያ ካለ ተከሳሾች በመመሪያዉ መሰረት አስፈላጊዉን ክፍያ ከከፈሉ በኃላ ዕቃዎቹ እንዲለቀቁ በማለት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ ይህን ዉሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነዉ፡፡

አመልካች በ07/03/2006 ዓ.ም በተጻፈ አቤቱታ 1ኛ ተጠሪ በአዋጅ ቁ.622/2001 አንቀጽ 93 /1/ (ሀ) የተጠቀሱ የወንጀል ድርጊቶችን መፈጸሙ በአዋጁ አንቀጽ 93 /2/ በግልጽ የተደነገገ ሲሆን፣ ተጠሪ ድርጅት በመሆኑ የሐሳብ ክፍል እንዲያሟላ የሚጠበቅ ሳይሆን ተጠሪዉ በከፈለዉ ታክስ እና ቀረጥ መካከል በልዩነት ብር 2,396,725.05 ሳይከፍልበት ወደ አገር ዉስጥ አስገብቶ መገኘቱ ነዉ፡፡ ይህን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙ ተረጋግጧል፡፡ በዲክላራሲዮን ቁጥር C-10951 በቻይና አገር የተመረተዉን ዕቃ አቅራቢ ከሆነዉ ከSHEZHENE XINGCHEN በአደራ ተቀብሎ ተጠሪዎችን ወክሎ ተረክቦ የላካ ሆፕ ኢንተርናሽናል /HOPE INTERNATIONAL/ በአዋጁ አንቀጽ 2/23/ መሰረት ወኪልንም ስለሚጨምር አቅራቢ ያልሆነዉ ሆፕ ኢንተርናሽናል የጻፈዉን ደብድቤ በመውሰድ ተጠሪዎችን ነጻ መልቀቁ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነዉ፡፡ ሆፕ ኢንተርናሽናል ድርጅት የጻፈዉ ደብዳቤ በአዋጅ ቁ.334/1995 አንቀጽ 26 /1/ እና 27 /1/ መሰረት ስላልተረጋገጠ፣ የደብዳቤዉም ይዘት ሲታይ በልዩነት የታየዉን ገንዘብ ትተንልሃል የሚል ስለሆነ ከዘመናዊ ግብይት አንጽር ከንግድ መርህ ዉጭ ነዉ፤ ደብዳቤዉም የተጻፈዉ ተጠሪዎች ከተከሰሱ በኃላ ነዉ፡፡ ስለዚህ የስር ፍ/ቤቶች በሕግ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ያልሆነን መሰረት በማድረግ ተጠሪዎችን ከክስ ነጻ ማድረጋቸዉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት  ያለዉ በመሆኑ ተጠሪዎቹ ላይ የጥፋተኝነት ዉሳኔ እንዲሰጥ በማለት ተከራከረዋል፡፡

ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገቡን በመመርመር ፣ተጠሪዎች ይህን የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የሐሳብ ክፍል እንደአስፈላጊ ሁኔታ ተቆጥሮ የተሰጠዉን ዳኝነት አግባብነት፣ ለማየት ጉዳዩ ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡ በታዘዙት መሰረት መጋቢት 3 ቀን 2006 ዓ.ም የተጻፈ መልስ ቀርቧል፡፡ የመልሱም ይዘት፡ 1ኛ ተጠሪ ሆፕ ኢንተርናሽናል ቻይና አገር ከሚገኝ ዕቃዎችን ለመግዘት ይህ ድርጅት የዕቃዎቹን ከዋጋ ዝርዝር ጋር በላከዉ መሰረት የዉጭ ምንዛሬ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ሲፈቀድለት በዳሻን ባንክ በኩል አል.ሲ /letter of credit/ ከፍቶ  ግዥዉን


አከናዉኗል፡፡ ይህ ኩባንያ የዕቃዉን ዝርዝር እና የዋጋዉን መጠን በኮሚርሻል ኢንቮይስ በባንክ በኩል ለተጠሪዎች ልኮ ክፍያም በዳሽን ባንክ በኩል በኤል.ሲ አድቫይዝ ተፈጽሟል፡፡ ዕቃዎቹ በኢትዮጵያ መርከብ ተልከዉ ሞጆ ደረቅ ወደብ የደረሱ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ኤልሲ፣ ኮሚርሻል ኢንቮይስ፣ የዕቃዎች ዝርዝር ፓክንግ ሊስት፣ ቢል ኦፍ ሎድንግ፣ እና ሌሎች አስፈላጊ ዶክመንቶችን በአግባቡ ተልከዉለት በሰጠዉ ትዕዛዝና በከፈለዉ ዋጋ መጠን መሆናቸዉን አረጋግጦ ሰነዶቹ በሙሉ ትክክል ስለሆኑ ሰነዶቹን ከባንክ አዉጥቶ ለትራዚተር አስተላልፏል፡፡ በዚህ መሰረት ዲክላራሲዮን ተሞልቶ ተገቢዉ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎ ዕቃዎቹ በፍተሻ ሲታይ ቻይና አገር የሚገኘዉ አቅራቢ የአላላክ ስህተት በመፈጸሙ ዕቃዎቹ ጫማ መሆናቸዉ እና ብዛታቸዉ በሠነዱ በተገለጸዉ ልክ ቢሆንም ስሪታቸዉና አዲዳስ የሚል ቢራንድ ስም ስለተለጠፈባቸዉ በመሆኑ በቀረጥና ታክስ አከፋፈል ላይ ለብራንድ የሚከፈለዉ ቀረጥና ታክስ ልዩነት አምጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የአቅራቢዉ ስህተት መሆኑን ኩባንያዉ ገልጸል፡፡ በተጠሪዎች በኩል የተፈጸመ ሕገ ወጥ ድርጊት የለም፤ በተጠሪዎች እዉቅና ወይም ቸልተኝነት የተፈጸመ ነገር የለም፡፡ በጉምሩክ አዋጅ ቁ.622/2001 መሰረት የፈጸምነው የወንጀል ድርጊት  የለም፡፡ ወንጀል ለመፈጸማችን የሐሳብ ከፍል የተሟላ ነገር የለም፡፡ የሥር ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት በልዩነት የታየዉን ቀረጥና ታክስ እንዲከፈል ስላደረገ የመንግስት ጥቅም ያስጠበቀ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስላልሆነ እንዲጻናልን በማለት በዝርዝር ክርክራቸዉን አቅርበዋል፡፡ አመልካች በ23/07/2006 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ አቤቱታዉን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ከላይ የተመለከተ ሲሆን፣ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታዉ መነሻ ከሆነዉ ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እና መዝገቡ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር  እንደሚከተለዉ ተመርምሯል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነዉ አመልካች ባቀረበዉ ክርክር ተጠሪዎች ከዉጭ አገር ለማስገባት ፈቃድ ከወሰዱት ዕቃዎች ዉጭ ሌላ አገር የተመረተ ዕቃዎች በማስገባት ሊከፈል ከሚገባ ቀረጥ እና ታክስ አናስተኛ በመክፈል የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ሲሆን፣ ተጠሪዎች በበኩላቸዉ የፈጸምናዉ የወንጀል ድርጊት የለም፣ ዕቃዎቹን ከዉጭ አገር የላከዉ ኩባንያ የፈጸመዉ ስህተት ስለሆነ ሊንጠየቅ አይገባም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ከግራ ቀኙ ክርክር መገንዘብ እንደሚቻለዉ 1ኛ ተጠሪ በ2ኛ ተጠሪ ሥራ አስኪያጅነት በቻይና አገር የተመረተ የእስፖርት ጫማዎችን ወይም ዕቃዎችን ወደ አገር ዉስጥ ለማስገባት ፈቃድ የወሰዳ ሲሆን፣ እነዚህ ዕቃዎች ከዉጭ አገር ወደ አገር ዉስጥ ገብቶ ሞጆ ደረቀ ወደብ ከደረሳ በኃላ በተደረገ ፍተሻ ቻይና አገር የተመረተ ሳይሆን መለያ ያለዉ ቬትናም አገር የተመረቱ ዕቃዎች እንደሆኑ፣ በዚህ ምክንያት ለመንግስት መከፈል ካለበት ቀረጥና ታክስ ዉስጥ በልዩነት ብር  2,396,725.05


ሳይከፍልበት ወደ አገር ዉስጥ እንደገቡ ግራ ቀኙ ያልተካካዱ ከመሆኑም በላይ በማስረጃም ተረጋግጧል፡፡ የአመልካች ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል ይህ ድርጊት መደረጉን በዲክላራሲዮን ላይ ከተገለጹት ዕቃዎች ዉጭ ወደ አገር ዉስጥ መግባታቸዉን አረጋግጠዋል፡፡ አመልካች ያቀረባቸዉ የሰነድም ሆነ የሰዉ ምስክሮች 1ኛ ተጠሪ ወደ አገር ዉስጥ እንዲያስገባ ከተፈቀደለት ዕቃዎች ዉጭ ሌሎች ዕቃዎችን ወደ አገር ዉስጥ በእሱ ምክንያት እንደገባ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካች በተጠሪዎች ምክንያት ወደ  አገር እንዲገባ ከተፈቀዱ ዕቃዎች ዉጭ ወደ አገር ዉስጥ ገብቶ መገኘታቸዉ እና በዚህ ምክንያት መከፈል ከነበረበት ቀረጥና ታክስ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉ ገንዘብ በልዩነት መገኘቱን የማስረዳት ሸክሙን መወጣቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ነገር ግን የሥር ፍ/ቤቶች እንዳረጋገጡት በተጠሪዎች በኩል የቀረበዉ ማስረጃ ዕቃዎቹን ከዉጭ አገር የላከዉ ሆፕ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በኩል የተፈጠረ ስህተት መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ገልጸዋል፤ 2ኛ ተጠሪም በሰጠዉ ቃል ዲክላራሲዮን እና ሌሎች አግባብነት ያላቸዉ ሰነዶች በአግባቡ ተሞልቶ በባንክ በኩል ተገቢዉ ክፍያ ተፈጽሞ የተላካ ሲሆን፣ ከዉጭ አገር ዕቃዎቹን ወደ አገር ዉስጥ የላካዉ ኩባንያ በፈጠረዉ ስህተት በሰነዱ ላይ ያልተጠቀሱ ዕቃዎች ወደ አገር ዉስጥ ገብቶ ሞጆ ደረቅ ወደብ ሲፈተሽ እንዳወቀ እና አነስተኛ ቀረጥና ታክስ ለመክፈል ተብሎ ምንም ነገር እንዳላደረገ እና በዚህ ድርጊት ዉስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌለዉ ገልጻል፡፡ በጉምሩክ አዋጅ ቁ.622/2001 አንቀጽ 93 (1)(ሀ) እና 93 /2/ በመፈተላለፍ የማጭበርበር የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም እያወቁ የተፈጸመ ድርጊት መሆን እንዳለበት የሚያከራክር አይደለም፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 /2/ መሰረት አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለዉ ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሞልተዉ ሲገኙ ብቻ ነዉ በማለት ይደነግጋል፡፡ በዚህ አግባብ ሲታይ 2ኛ ተጠሪ ይህን የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም ምንም ዓይነት ሚና እንዳልነበረዉ እና ድርጊቱን ለመፈጸም ሐሳብ እንዳልነበረዉ የቀረበዉ ማስረጃ እንደሚያረጋግጥ የሥር ፍ/ቤቶች አረጋግጧል፡፡ 2ኛ ተጠሪ ይህን የወንጀል ድርጊት አዉቆ መፈጸም ይቅርና ያልተጠየቁ ዕቃዎች ወደ አገር ዉስጥ መግባታቸዉን ያወቀዉ ሞጆ ደረቅ ወደብ እንደሆነ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ነዉ፡፡ 2ኛ ተጠሪ በዚህ ድርጊት ምክንያት የወንጀል ተጠያቂነት አለበት ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡

 

በሌላ በኩል 1ኛ ተጠሪን በተመለከተ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 (3) የሕግ ሰዉነት የተሰጠዉ ድርጅት በዚህ ሕግ በአንቀጽ 34 በተደነገጉ ሁኔታዎች መሰረት በወንጀል ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል፡፡ በአንቀጽ 34 (1) መሰረት አንድ ድርጅት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣዉም ከኃላፊዎቹ ወይም ከሠራተኛቹ አንዱ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ


የድርጅቱን ጥቅም በሕገ ወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ፣ ወይም የድርጅቱን ሕጋዊ ግዴታ በመጣስ፣ ወይም ድርጅቱን በመሳሪየነት ያለአግባብ በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ወንጀል ሲያደርግ ነዉ በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህ አግባብ አሁን የተያዘዉ ጉዳይ ሲታይ 1ኛ ተጠሪ ባቀረበዉ ማስረጃ የድርጅቱ ኃላፊ ወይም ሰራተኛ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ድርጅቱን ተገን በማድረግ ወንጀሉን ያልፈጸመ መሆኑን ባቀረበዉ ማስረጃ ያረጋገጠ መሆኑን የሥር ፍ/ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነዉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ድንጋጌ አግባብ 1ኛ ተጠሪ የተጠቀሰዉን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን በማረጋገጡ፣ የሥር ፍ/ቤቶች 1ኛ ተጠሪን ከክሱ ነፃ እንዲወጣ የሰጡት ዉሳኔ የህግና የማስረጃ ድጋፍ ያለዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ ተጠሪዎች በዚህ የወንጀል ድርጊት ዉስጥ ምንም ተሳትፎ እንደሌላቸዉ በመከላከያ ማሰረጃ በማረጋገጥ እና በመከላከላቸዉ ከክሱ ነጻ እንዲወጡ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ዉሳኔ ከዉጤት አንጻር መሰረታዊ የሕግ ሰህተት የሌለዉ በመሆኑ የሚከተለዉ ተወስኗል፡፡

 

 ዉ ሳ ኔ

1. የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.33613 በ02/08/2005 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት የምስራቅ ችሎት በመ.ቁ.161271 በ16/12/2005 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ ከዉጤት አንጻር መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለዉ በመሆኑ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.195 /2/ /ለ/፣/ 2/ መሰረት ጸንቷል፡፡

2.  የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤት ይድረስ ብለናል፡፡

መዝገቡ ዉሳኔ ስላገኘ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

የ/ማ