117065 criminal law/ tax law

ማንኛውም እቃ ወይም መጓጓዣ ሊወረስ በሚችል ወንጀል በተከሰሰ ሰው ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ ተጨማሪ ትእዛዝ መስጠት ሳያስፈልግ እቃው ወይም መጓጓዣው እንዲወረስ የሚደረግ ስለመሆኑ አዋጅ ቁ. 622/2001 አንቀፅ 104(1)

 

የሰ/መ/ቁ. 117065 የካተት 30 ቀን 2008ዓ/ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ  አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሹ ሺርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዓቃቤ ህግ ምህረቱ ቁምላቸው ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ሚፍታ ካሚል ቀርቧል፡፡

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ለክርክር መነሻ የሆነው የአሁኑ አመልካች በተጠሪ ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስ ነው፡፡ ክሱ የኮንትሮባንድ ወንጀል ሆኖ ክርክሩ የተጀመረው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ተጠሪ ከስር ክስ ሶስት ተከሳሾች ከነበሩት ጋር የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91/2/ የተደነገገውን በመተላለፍ በቀን 10/10/2006 ዓ.ም ከቀኑ 7፡15 አከባቢ ምንም ዓይነት የጉምሩክ ስነስርአት ያልተፈፀባቸው እና ጠቅላላ ቀረጥና ታክሳቸው ብር 15,425.23 /አስራ አምስት ሺህ አራት መቶ ሃያ አምስት ብር ከሃያ ሶስት ሳንቲም/ ለመንግስት ያልተከፈለባቸው መሆናቸውን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው የተለያዩ ንብረቶች በ1ኛው ተከሳሽ የአሁኑ ተጠሪ ረዳትነትና የመኪናው ባለቤትነት እና 2ኛ ተከሳሽ አሽከርካሪነት  ከጊዘን ወደ አሶሳ ለመሄድ በኮድ3-00277 ቤጉ በሆነ ሚኒባስ ጭነው በመጓጓዝ ላይ እያሉ ሸርቆሌ ፌዴራል ፖሊስ ካምፕ አካባቢ በፌዴራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር  በማዋላቸው የኮንትሮባንድ ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ክስ ቀርበውበታል፡፡ ከ2ኛ-4ኛ ተከሳሾች ባለመቅረባቸው በሌሉበት ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆኑን ከስር መዝገብ መረዳት ይቻላል፡፡  የአሁኑ ተጠሪ የቀረበውን የወንጀል ክስ በመካዱ ፍርድ ቤቱም የዐ/ህግ ምስክሮች በመስማት ከመረመረ በኋላ ተጠሪ እንዲከላከል ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ተጠሪ መከላከያ ምስክር ያቀረበ ቢሆንም ባለመከላከሉ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ካለ በኋላ ቅጣት በተመለከተም በሁለት ዓመት ፅኑ እስራት እና በብር 50,000 የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣና የእስራት ቅጣት በሁለት ዓመት የፈተና ጊዜ ገደብ እና በተከሳሾች እጅ የተያዘው የኮንትሮባንድ ወንጀል ንብረቶች ለመንግስት ገቢ እንዲደረጉ፡፡   በተጠሪ


ስም የተመዘገበውን ንብረት ኮድ 3-00277 ቤጉ ሚኒባስ መኪና ለባለ ንብረቱ እንዲመለስ በማለት ወስኗል ፡፡

 

አመልካች በዚሁ የእስራት ቅጣቱ በገደብ መለቀቁና መኪናው ይመለስ በማለት የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታው ቢያቀርብም በውሳኔ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታም የስር ፍርድ ቤቶች ቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስሕተት የተፈፀመበት ስለሆነ እንዲታረም በማለት የቀረበ ነው፡፡ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- የአሁኑ ተጠሪ የተሸከርካሪው ባለቤት እና በወቅቱ በተሸከርካሪው ላይ በረዳትነት ሲሰራ የኮንትሮባንድ እቃዎች ጭኖ በመያዙ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91/2/ የተከሰሰ እና በዚሁ አዋጅ ስር ጥፋተኛ የተባለ እንደመሆኑ በወንጀል የተፈፀመበትን ማጓጓዣ መወረስ እንዳለበት ህጉ በግልፅ ደንግጎ ይገኛል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ይህን የህግ ድንጋጌ በጥልቀጥት ሳይመለከት እና ከዚህ ተቀራኒ በሆነ መልኩ ማጓጓዣውን በተመለከተ ያለምንም ምክንያት ለባለንብረቱ ይመለስ በማለት የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው፡፡

 

በሌላ በኩል ይግባኝ ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት የተጠሪ ማጓጓዣ ላይ የተሰጠውን ትእዛዝ አግባብነት ከጉምሩክ ህግ አንፃር በጥልቀት መመርመር ሲገባው ተጠሪ በወቅቱ በመኪናው ላይ በረዳትነት ሲሰራ እንደነበረ የስር ፍርድ ቤት በማረጋገጥ የሰጠው ጥፋተኝነት ውሳኔ ባልተሸረበት እና የመከራከሪያ ነጥብ ያለሆነውን የአሁን ተጠሪ መኪናው ኮንትሮባንድ እቃ ሲጫን በቦታው አልነበረም በማለት የወ/መ/ስ/ስ/ህግን እና የሙግት ስነስረአት በሚቃረን መልኩ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ማፅናቱ የህግ ስህተት የተፈፀመ መሆኑን፤ እንዲሁም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 192፤196 እና 197 የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት የቅጣቱን አፈፃፀም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 196/2/ መሰረት መገደቡ መሰረታዊ የህግ ስህተት በማረም ተጠሪ ላይ የተጣለውን የቅጣት አፈፃፀም ገደብ እንዲያነሳልን እና የአሁኑ ተጠሪ የሆነውን ኮድ 3-00277 ቤጉ ተሸከርካሪ እንዲመለስ የተሰጠው ትእዛዝ ተሽሮ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91/2/ መሰረት ለመንግስት ውርስ እንዲሆን ትእዛዝ እንድሰጥላቸው አቤቱታቸውን አቅርቧል፡፡

 

የቀረበው የሰበር አቤቱታ በመመርመር ንብረትነቱ የተጠሪ ከሆነ ኮድ 3-00277 ቤጉ ሚኒባስ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተጭኖ በመገኘቱ በአዋጅ ቁ.622/2001/ አንቀጽ 91/2/ መሰረት ተጠሪ ጥፋተኛ መባሉ ተረጋግጦ እያለ ዕቃው የተጫነበት መኪና ለተጠሪ ይመለስ የመባሉን አግባብነት ከአዋጅ ቁ. 622/2001/ አንቀጽ 91/2/ እና 104 ድንጋጌ አንፃር ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሰረትም ተጠሪ መልስ እንዲሰጥበት በታዘዘው መሰረት በቀን 21/01/2008ዓ/ም የተፃፈ 2 ገጽ መልስ አቅርቧል፡፡   ይዘቱም ተጠሪ የስር ፍርድ ቤት    ቅጣቱ


የገደበው ህጉ በሚፈቅደው አግባብ ስለሆነ የህግ ስህተት የሚያነሳና ለክርክር  የሚቀርብ አይደለም፡፡ በወቅቱ ነዳጅ አልቆብናል አምጣልን ብለውን ከአሶሳ ይዠላቸው በሄድኩበት የእርዳታ ዘይቱ ጫነ መሆኑን በመገንዘብና ከፍተኛው የገንዘብ ቅጣት 50,000 የተቀጣሁ በመሆኑ በኢግዚቢትነት የተያዘው ተሸከርካሪ ለተከሳሽ ይመለስለት መባሉአግባብነት ያለውነው፡፡  ስለዚ የስር ፍርድ ቤቶች ወሳኔ በማፅናት የህግ ስህተት የለበትም ተብሎ በነፃ እንዲያሰናብተኝ በማለት መልሱን አቅርበዋል፡፡

 

አመልካች ጥቅምት 19 ቀን 2008ዓ/ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል ተጠሪ በጥፋተኝነት ውሳኔ ላይ ምንም ቅሬታ ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አላቀረበም:: የስር ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሳይሻር መኪናው ሲያዛ በቦታው አልነበርኩም የመከራከሪያ ነጥብ ተቀባይነት የለውም:: በሌላ በኩል 50,000 ብር ከፈልኩ በማለት ያቀረበው ጥፋተኛ በተባለበት አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91/2/ ስር በተነገገው መሰረት የተጣለበት የገንዘብ መቀጮ እንጂ የተያዘው መኪና ላማስለቀቅ የተከፈለ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብልን በማለት አቤቱታውን በማጠናከር የመልስ መልሱን በማቅረብ ተከራክሯል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ እንደተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነውም ታክስና ቀረጥ ሳይከፈለበት የኮንትሮባንድ ዕቃ ስታጓጉዝ የተያዘችው የተጠሪ መኪና ይመለስ በማለት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ከግምሩክ አዋጅ ህጉ አግባብነት ያለው መሆኑንና አለመሆኑን የሚለውን ጭብጥ መልስ ማግኘት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

 

በፍሬ ጉዳይ ማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት የኮንትሮባንድ ዕቃ ለመንግስት ሊከፈል የሚገባው ታክስ እና ቀረጥ ብር 15,425.23/አስራአምስት ሺህ አራት መቶ ሃያ አምስት ብር ከሃያ ሶስት ሳንቲም/ያልተከፈለበት ሲያጓጉዝ በተያዘበት ወቅት ተጠሪ የመኪነው በረዳትነት እንደነበረ እንዲሁም የመኪናው ባለቤት መሆኑን በማረጋገጥ በተከሰሰበት አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91/2/ የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት የፅኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ቅጣት የተወሰነበት መሆኑን ተረጋግጠዋል፡፡ በተጠሪ ላይ  የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ላይ በይግባኝ ቀርቦ የተለወጠ አይደለም፡፡ ተጠሪ ጥፋተኛ ከተባለና ለኮንትሮባንድ ዕቃ መጓጓዣ የዋለው የተጠሪ መኪና መሆኑን ከተረጋገጠ  መኪናው የማይወረስበት ሁኔታ አለ ወይ የሚለውን ከሕጉ አንፃር መታየት አለበት፡፡

 

አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91/2/ በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ/1/ ላይ በተመለከተው ሕገወጥ መንገድ  የተገኙ  እቃዎች  መሆናቸውን  እያወቀ  ወይም  ማወቅ  ሲገባው  እቃዎቹ ያጓጓዘ፤


ያከማቸ፤ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የገዛ ማንኛውም ሰው በቅን ልቦና ለወንወጀሉ ባዕድ የሆኑት ሰዎች መብት ሳይነካ ወንጀሉ የተፈፀመበት ዕቃና መሳሪያ እና የወንጀሉ ፍሬ እንደሚወረሱ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ተጠሪ የኮንትሮባንድ ዕቃ መሆኑን እያወቀ ያጓጓዘ በመሆኑ በመረጋገጥ ጥፋተኛ ስለተባለ በቅንልቦና ወይም ለወንጀሉ ባዕድ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ እንዲሁ በሆነበት ከጉምሩክ አዋጅ ቁ.622/2001 አንቀጽ 104/1/ ማንኛውንም እቃ ወይም ማጓጓዣ ሊወረስ በሚችል ወንጀል በተከሰሰ ሰው ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ ተጨማሪ ትእዛዝ መስጠት ሳይስፈልግ እቃው ወይም ማጓጓዣው እንዲወረስ ይደረጋል ሲል ተደንግጓል፡፡

 

የክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት ለማፅናት እንደምክንያት ያደረገው ተጠሪ ዕቃው ሲያዝ በቦታው አልነበረም ዕቃው ሲጫን አያውቅም የሚለውን በማሰረጃ የተረጋገጠው ረዳት ሆኖ ዕቃው የመኪናው ሽፌር የነበረው 2ኛ ተከሳሽ የኮንትሮባንድ ነው እንዳይጫን እየተባለ የጫነ መሆኑን በአመልካች ምስክሮችበመረጋገጥ በተጠሪ ላይ የጥፋተኘነት ከተሰጠበት ውሳኔ በሚቃረን እና የሰ/መ/ቁ.76976 ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው በመጥቀስ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡

 

ለዚህ ጉዳይ ተመሳሳይ በፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 64819 አስገዳጅ ትርጉም ሰጥተቦታል፡፡ በመሆኑ ይህ የህጉ መንፈስ መሰረት በማድረግ ተጠሪ የመኪናው ባለቤት ሆኖ በወንጀሉ ተሳተፊነት በማረጋገጥ የጥፋተኝነት ከተሰጠ ሌላ ተጨማሪ ትእዛዝ ሳያስፈልግ የኮንትሮባንድ ዕቃ ለመጓጓዣ የዋለው መኪና ምንም ህጋዊ ምክንያት በሌለው ለተጠሪ ይመለስ በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ትእዛዝ ከጉምሩክ አዋጁ አንቀጽ 91/2/ እና 104/1/ ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝተዋል ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የቤ/ጉ/ክ/መ/ ጠ/ፍ/ቤትበመ/ቁ.06590ሐምሌ 23 ቀን 2007ዓ/ም፤ የተሰጠ ውሳኔ እና የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.09092ግንቦት 28 ቀን 2007ዓ/ም የተጠሪ መኪና ይመለሰለት በማለት የተሰጠ ቅጣት ውሳኔ ክፍል ብቻ በወ/መ/ስ/ስ/ቁ.195/2/መ መሰረት ተሽሯል፡፡

2. በተጠሪ ላይ የሁለት ዓመት የፅኑ እስራት በመገደብ የተወሰነ ቅጣትና የገንዘብ መቀጮ ፀንተዋል፡፡

3. በተጠሪ ስመንብረቱ ተመዝግቦ የሚገኘው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-00277 ቤጉ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ለመንግስት በውርስ ገቢ እንዲደረግ በማለት ታዟል፡፡

 

 

መዘገቡ ተዘግተዋል፤ ወደ መዘገብ ይመለስ፡፡  የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡