105211 jurisdiction/ certificate of inheritance/ Addis Ababa City court

የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች አስቀድመው የወራሽነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት በቀረበ አቤቱታ ላይ ባሳለፉት ውሳኔ የሚነሳን ተቃውሞ አቤቱታ ተቀብለው ለማስተናገድ የሥረ ነገር ስልጣን ያላቸው ስለመሆኑ አዋጅ ቀ/361/1995 አንቀጽ41/ሸ/ አዋጅ 408/96 አንቀጽ 2/ንኡስ ቁ፣1

 

የሰ/መ/ቁ. 105211 ጥቅምት 1/2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካቾች፡- 1. አቶ እንዳለ ደንቦባ

 

2. አቶ ንጉሴ ደንቦባ

 

3. ወ/ሪት ውቢት ደንቦባ           ጠበቃ አብዮት አበበ ቀረቡ

 

4. ወ/ሮ ሽቶ ደንቦባ ተጠሪዎች፡- 1. ወ/ሮ አልማዝ ደንቦባ

2. ወ/ሮ ዘውዲቱ ደንቦባ

 

3. ወ/ሮ እታፈራሁ ደንቦባ              ጠበቃ ሰለሞን ስዩም ቀረቡ

 

4. አቶ ጌታቸው ደንቦባ

 

5. ወ/ሮ ወይንሐረግ ደንቦባ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ተወስኗል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

የሰበር አቤቱታው የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት የአሁን ተጠሪዎች ያቀረቡትን የመቃወም አቤቱታ ተቀብሎ የቀደመ ውሳኔውን በመሻሩ እና ይግባኝ ሰሚውና የሰበር  ችሎቱም


ውሳኔው ጉድለት የለበትም በማለት የቀረበላቸውን አቤቱታ ባለመቀበል መዝገቡ በመዝጋተቸው የሕግ ስህተት ተፈፅሟል በሚል ነው፡፡

 

የአሁን ተጠሪዎች ለስር ፍ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ባላንባራስ ደንቦባ ውፍዬ ህዳር 1996 ዓ.ም ኑዛዜ አድርገዋል ተብሎ ለፍ/ቤቱ ቀርቦ ፍ/ቤቱ ኑዛዜውን በማፅደቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን በኑዛዜው ላይ የተጠቀሱት ምስክሮች ኑዛዜው በተደረገበት ዕለት በቦታው ያልነበሩ ኑዛዜው ላይ የፈረሙት ኑዛዜው ከተደረገ በኋላ ቢሮዋቸው ድረስ በሄደላቸው መሰረት በመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ 881/3/ የተመለከተውን የሚያሟላ አይደለም፤ በኑዛዜው ተራ ቁጥር 5 የተመለከተው የንግድ ድርጅት ሟች ከባለቤታቸው ጋር ያፈሩት በመሆኑ የራሳቸው ብቻ ባልሆነ ንብረት ላይ ኑዛዜ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም፤ ለመቃወም አመልካቾች የተናዘዙትም ሊደርሳቸው ከሚገባው ድርሻ በታች ነው፤ ስለሆነም ኑዛዜው ፈራሽ ሊሆን ይገባል በማለት የመቃወም አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

 

የአሁን አመልካቾች ለአቤቱታው በሰጡት መልስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 358 መሰረት የሚቀርብ አቤቱታን ፍ/ቤቱ ተቀብሎ ለመወሰን ስልጣን የለውም የሚል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ በፍሬ ጉዳይም ኑዛዜው በአራት ምስክሮች ፊት የተደረገ በመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ 881 እና 882 የተመለከተውን የተከተለ ነው፤ ሟች በኑዛዜው የገለፁት ድርሻዬን በማለት ነው፤ ሊደርሰን ከሚገባው ድርሻ በታች ነው ለሚሉትም በህይወት የሌሉትን ወ/ሮ አለምፀሐይ ደንቦባን በመቀላቀል የንብረቱን ግምት በማካፈል በመሆኑ መቃወሚያው የሕግ መሰረት የለውም ብለዋል፡፡

 

የስር ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን በተመለከተ የኑዛዜውን ሰነድ መርምሮ የኑዛዜ ወራሽነት ውሳኔ የሰጠ ራሱ ፍ/ቤቱ በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 358 መሰረት በውሳኔው ላይ በዚያው መዝገብ ላይ የሚቀርበውን መቃወሚያ ተቀብሎ ለማየት ስልጣን አለው በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ በፍሬ ጉዳዩም የግራ ቀኙን ክርክር እና በኑዛዜው ላይ የተመለከቱ ምስክሮችን ቃል ከሰማ በኋላ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሁለቱ ኑዛዜው በማን እንደተፃፈ የት እንደተፃፈ አለማወቃቸውን ገልፀው ኑዛዜው ላይም የፈረሙት ሁሉም ምስክሮች በሌሉበት መሆኑን ተናዛዡ ሲፈርም ያላዩ መሆኑን ገለፀዋል፤ የቀሩት ሁለቱ ምስክሮች ደግሞ ኑዛዜው የት እንደተፃፈና ማን እንደፃፈው ያላዩ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን ተፅፎ የቀረበው ኑዛዜ በአራቱ ምስክሮች ፊት ተነቦ ተፈርሞ ነበር በማለት መስክረዋል፡፡ ስለሆነም ኑዛዜው የፍ/ብ/ህ/ቁ 881 ስር የሰፈረው ያሟላ ካለመሆኑም በላይ የምስክሮች ቃል ተመሳሳይ አይደለም በማለት ቀሪዎችን መከራከሪያዎች መመልከት ሳያስፈልግ አስቀድሞ የተሰጠው የኑዛዜ ወራሽነት  በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ  360/2/ መሰረት በመሻር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡


ይግባኙ የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኙን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 መሰረት የሰረዘ ሲሆን የከተማው የሰበር ችሎትም ውሳኔው መሰረታዊ ሊባል የሚችል የሕግ ስህተት ስላልተገኘበት ለሰበር አያስቀርብም ብሏል፡፡

 

አመልካቾች ለዚህ ፍ/ቤት መስከረም 13/2007 ዓ.ም የተፃፈ 4 ገፅ ዝርዝር የሰበር ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ይኽው ተመርመሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት የቀረበለትን የመቃወም አቤቱታ አከራክሮ የመወሰን የስረ ነገር ስልጣን ያለው መሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 361/1995 እና ከአዋጅ ቁጥር 408/1996 እንዲሁም በሰበር መ/ቁ 75560 ከተሰጠው የሕግ ትርጉም አንፃር ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ግራ ቀኙም በፅሁፍ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን የግራ ቀኙን ክርክር ከስር ፍ/ቤት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

 

አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 41/1//ሸ/ በአዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀፅ 2/1/ እንደተሻሻለው የወራሽነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት በሚቀርብ አቤቱታ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ተቃውሞ የቀረበበት ውሳኔ የተሰጠውም በሕጉ በተደረገው የዳኝነት ስልጣን መሰረት ነው፡፡ በሌላም በኩል የተቃውሞ አቤቱታው ያስከተለው የሕግ እና የፍሬ ነገር ክርክር ይዘት ሲታይ ከኑዛዜ ወራሽነት የምስክር ወረቀቱ የዘለለ እንድምታ የለውም፡፡

 

ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አስቀድመው የወራሽነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት በቀረበ አቤቱታ ላይ ባሳለፉት ውሳኔ የሚነሳን የተቃውሞ አቤቱታ ተቀብለው ለማስተናገድ የስረ ነገር ስልጣን የላቸውም ተብሎ የቀረበው መቃወሚያ ውድቅ በመደረጉ የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም፡፡

 

የሰ/መ/ቁ/ 75560 ሐምሌ 26/2004 ዓ.ም በዚህ ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ የባልና ሚስትነትን ማስረጃን የሚመለከት ሲሆን በእጃችን ካለው የወራሽነት ማስረጃ ጥያቄ ጋር አንድ ናቸው ወይም ተመሳሳይነት አላቸው የሚሰኝ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ የስረ ነገር ስልጣን ጥያቄን ለመወሰን መርህ የሆነው የክሱን ምክንያት ይዘት መመልከት ነው፡፡ ከይዘቱ ውጭ የሆኑ ሌሎች የማያመሳስሉ ሁኔታዎች መኖር ጉዳዮች በተመሳሳይ የስረ ነገር ስልጣን ስር ያርፋሉ የሚል መደምደሚያ ላይ አይደርስም፡፡ የባል ወይም የሚስትነት ማስረጃ የምስክር ወረቀት ለማግኘት በቀረበ አቤቱታ ላይ የተሰጠ ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 358 መሰረት ተቃውሞ ሲቀርብበት ተቃውሞውን ተከትሎ ፍ/ቤቶች የምስክር ወቀረቱን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ባለፈ ስለ ጋብቻ መኖር አለመኖር እና


በጋብቻ ውጤት ላይ ሁሉ እንድምታ ያለው ሌሎችን ሕጎች የሚነካ የፍሬ ነገር እና የሕግ ክርክር ይመለከታሉ፡፡ በአንፃሩ የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ የሚቀርብ የተቃውሞ አቤቱታ የማስረጃውን ትክክለኛነት እና ህጋዊነት ከማረጋገጥ ያለፈ እንድምታ የለውም፡፡

 

በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሚሰጠው ትርጉም አስገዳጅነት የሚኖረው ተመሳሳይ የሕግ ክርክር በቀረበባቸው ጉዳዮች ላይ ስለመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀፅ 2/1/ ድንጋጌ እና ከአስገዳጅ ውሳኔዎች ፅንስ ሃሳብ መረዳት የሚቻል ሲሆን በሰ/መ/ቁ. 75560 በተሰጠው ውሳኔ ላይ የቀረበው የሕግ ክርክር በእጃችን ካለው ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡

 

ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተው በስር ፍ/ቤቶች ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር መረዳት እንደሚቻለው ኑዛዜው በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 881 የተመለከተውን ፎርም ተከትሎ የተደረገ ባለመሆኑ አስቀድሞ የተሰጠው የኑዛዜ የወራሽነት ምስክር ወረቀት በመሻሩ የተፈፀሙ የሕግ ስህተት የለም፡፡ ስለሆነም ተከታዩ ተወስኗል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የአዲስ አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ 1038/2005 ግንቦት 28/2006 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሁም የአ/አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በመ/ቁ 22371 ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም እና የአ/አበባ ከተማ ሰበር ችሎት በመ/ቁ 22404 ነሐሴ 8/2006 ዓ.ም የሰጡት ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348/1/ መሰረት ፀንቷል፡፡

2.  ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ

 

 


 

 

ብ/ይ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት