92991 jurisdiction/ investment

ካሳ አነሰኝ ወይም ተከለከልሁ ካልሆነ በቀር በኢንቨስትመንት የሚቀርቡ የሕግም ሆነ የፍሬ ነገር ክርክር ይግባኞች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ፍርድ ቤት ስለመሆኑ፣ አዋጅ ቁጥር 138 አንቀጽ 6/5/

 

 

የሰ/መ/ቁ. 92991

 

ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- አቶ ተፈራ ተሰማ አልቀረቡም፡፡

 

ተጠሪ፡- የአርሲ ዞን አስተደደር ጽ/ቤት አልቀረቡም፡፡ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የኢንቨስትመንት ውልን መሠረት አድርጐ ለአመልካች ተሠጥቶ የነበረ የገጠር መሬትን የሚመለከት ሲሆን ተጠሪ ውሉን አፍርሶ መሬቱ እንዲለቀቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ለክሱ ምክንያት በማድረግ አመልካች ለአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀጥታ ክስ አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም በተጠሪ የቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በመቀበል ጉዳዩ የኢንቨስትመንት ጉዳዩችን አይቶ ውሳኔ ለመስጠት የተቋቋመው የኢንቨስትመንት ኮሚቴ ስልጣን መሆኑን በመጥቀስ መዝገቡን ዘግቷል፡፡

 

ይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ችሎቶችም ውሳኔው ጉድለት የለበትም እንዲሁም የህግ ስህተት አልተፈፀመበትም በማለት አሰናብተዋል፡፡

 

የሰበር አቤቱታው ለዚህ ፍ/ቤት የቀረበው ይህን በመቃወም ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች በሊዝ የወሰደውን መሬት በማልማት የተለያዩ አትክልት አይነቶች እያመረተ መሆኑን በሚከራከርበት ሁኔታና የአርሲ ዞን አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚቴ ከአዋጅ ውጭ መሬቱን የነጠቀው መሆኑን እየተከራከረ የሥር ፍ/ቤቶች ጉዳዩ በዳኝነት አካል የሚታዮ አይደለም በማለት የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ የማድረጋቸው አግባብነት የኦሮሚያ ክልል  ኢንቨስትመንት አስተዳደር እንደገና ለመወሰን ከወጣው አዋጅ ቁጥር 115/1998 አንፃር ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ግራ ቀኙም ክርክራቸውን በፅሑፍ አቅርበዋል፡፡


በበኩላቸን ቅሬታ ያነሳውን ውሳኔ ከግራ ቀኙ ክርክር እና ከህጉ ጋር በማያያዝ መርምረናል፡፡ እንደመረመርነው ጉዳዩ በፍርድ ሊታይ የሚችል መሆን አለመሆኑ እና የሥር ፍ/ቤት የሥረ ነገር ስልጣን የለኝም ማለቱ ህጉን የተከተለ መሆኑን መመልከት ይጠይቃል፡፡

 

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 37/1/ ማንኛውንም ሰው በፍ/ቤት ወይም የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው ሌላ አካል ጉዳዮን አቅርቦ ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 4 ሥር እንደተመለከተውም ፍርድ ቤቶች በሌላ ህግ በግልፅ ለሌላ አካል ከተሰጡ ጉዳዩች ውጭ አከከራክሮ የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን አላቸው ስለሆነም ፍ/ቤቶች ጉዳዩን ተቀብለው በማከራከር ውሳኔ መሰጠት የሚችሉት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በግለፅ ህግ ለሌላ እካል እስካልተወጣ ድረስ ነው፡፡ በህግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉት ጉዳዩች ላይ መደበኛ ፍ/ቤት የመዳኛት የስረ ነገር ሥልጣን ስለሌለው በህጉ መሠረት ሥልጣን ለተሰጠው የአስተዳደር አካል ቀርቦ በየደረጀው አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጥበትን ጉዳይ ፍ/ቤት አስተናግዶ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ የኢንቨስትመንት ኮሚቴው በሰጠው ውሳኔ ላይ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን በሚመልከት በኮሚሽኑና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ ድርሻ ባላቸው አካላት የሚወሰኑትን ጉዳዩች አስመልክቶ በሚቀርቡ ይግባኞች ላይ ውሳኔ የሚሰጠው የኢንቨስትመንት  ቦርዱ ስለመሆኑ እና ብርዱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ስለመሆኑ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንት አስተዳደርን እንደገና ለመወሰን የመጣውን አዋጅ ቁጥር 115/1998 ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 138/2000 አንቀጽ 6/5/ ይደነግጋል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ አንቀጽ 9/4/ ላይ እንደተመለከተውም ካሳ አነሠኝ ወይም ካሳ ተከሰከስኩ ወይም መሠረታዊ የህግ ሥህተት ተፈፀመብኝ በሚሉ ክርክሮች ላይ ካልሆነ በቀር በኢንቨስትመንት የሚቀርቡ የህግም ሆነ የፍሬ ነገር ክርክር ይግባኞች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሠጠው ቦርዱ ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡

 

ስለሆነም የቀጥታ ክስ የቀረበለት የከፍተኛው ፍ/ቤት የሥረ ነገር  ሥልጣንን አስመልክቶ የቀረበውን መቃወሚያ ተቀብሎ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 244/2/ሀ/ እና 245/2/ መሠረት ክሱ ተቀባይነት የለውም በማለት መወሰኑ እና ይግባኝ መባሉም ሆነ የሰበር ችሎቱ አቤቱታውን በመሰረዛቸው የተፈፀመ የህግ ስህተት የለም ብለናል፡፡ ተከታዩን ወስነናል፡፡


 

 

 ው ሳ ኔ

 

1ኛ የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 38932 ህዳር 14/2005 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 152805 ታህሳስ 23/2005 ዓ.ም እንዲሁም የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ.158804 ሰኔ 18/2005 ዓ.ም የሰጡት ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሠረት ፀንቷል፡፡

 

2ኛ ወጩና ኪሳራ ይቻቻሉ

 

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ወ/ከ