112575 jurisdiction/ adoption/ certificate of inheritance/ Addis Ababa city court

አዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት የጉዲፈቻ ስምምነትን ማስረጃን ተመልክቶ የወራሽነት ማስረጃን የመስጠት ስልጣን ያለው ስለመሆኑ አዋጅ ቁ. 361/1995 አንቀፅ 41(ሸ)

 

የሰ/መ/ቁ.112575 30/06/2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሠለ

አመልካች፡- አቶ አፈወርቅ መኩሪያ - አልቀረቡም

 

ተጠሪ፡- ወ/ሮ ማዳሊና ፍራንሲኔቲ ጠበቃ ኤልያና ጥላሁን መዝገቡን መርምረን ተከታዮን ፍርድ ሰጥተናል ፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዮ የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰረዝ የቀረበ አቤቱታን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ የመጀ/ደ/ፍ/ቤት ነው፡፡ ተጠሪ ቀደም ሲል ከዚህ ፍ/ቤት የወሰዱት የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰረዝ አመልካች ያቀረቡት የመቃወሚያ አቤቱታ ይዘት የመቃ/ተጠሪ/የአሁኗ ተጠሪ/ የሟች ወ/ሮ ፈንታዮ መተኪያ ልጅ ሳይሆኑ በተፈጥሮ ሟች እንደወለዱዋቸው ልጅ ነኝ ብለው የወሰድት የወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝልኝ የሚል ሲሆን ተጠሪ በበኩላቸው ባቀረቡት የመጀ/ደ/መቃወሚያ ፍ/ቤቱ የልጅነትን ክርክር ጭብጥ ይዞ ለማየት ስልጣን የለውም፣የመቃ/አመልካች የሟች ልጅ /ተወላጅ/ ሳይሆኑ ያቀረቡት መቃወሚያ አቤቱታ ላይ መብት ወይም ጥቅም የላቸውም ፣የመቃ/አመልካች ወላጅ እናት ወ/ሮ አፀደ ንዋይ የሞቱት  ከ 30 ዓመት በፊት ስለሆነ አቤቱታው በይርጋ ቀሪ ነው በማለት መቃወሚያ እና በአማራጭም መልስ ማቅረባቸው ከስር ፍ/ቤት ውሣኔ ላይ ተመልክቷል፡፡

 

ፍ/ቤቱ የቀረበውን የመጀመሪያ መቃወሚያ መርምሮ የመቃ/አመልካች እንደሚሉት እና በመቃ/ተጠሪም የግራ ቀኙን የልጅነት ክርክርን ፍ/ቤቱ ጭብጥ ይዞ ሲመረምረው በተገቢው ፍ/ቤት አጠናቀው እና ማስረጃ ይዘው እስከ ቀረቡ የወራሽነት ክርክሩ መዝገብ ለጊዜው ተዘግቶ ይቆይ በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡ ሌሎች መቃወሚያዎች ላይ መቃወሚያዎቹን ባለመቀበል በብይን አልፋል፡፡  ተጠሪ  በዚህ  ብይን  ላይ ቅሬታቸውን  ለአዲስ  አበባ ከተማ  ይግባኝ  ሰሚ ፍ/ቤት


አቅርበው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.337 መሠረት ይግባኙ የተሰረዘ ሲሆን የሰበር አበቱታ ለይ/ሰሚው ፍ/ቤት አቅርበው ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ የስር ፍ/ቤትን ብይን በመሻር አመልካች /የስር የመቃ/ተጠሪ/ የሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ የጉዲፍቻ ልጅ መሆን አለመሆኑን የቀረበውን ማስረጀ እና እንዲቀርብ የተጠየቀውን ማስረጃ በማስቀረብ መርምሮ የመሰለውን እንዲወሰን ለስር ፍ/ቤት በመመለስ ወስኗል፡፡

 

አመልካች በዚህ ውሣኔ ላይ ቅሬታቸውን በመዘርዘር የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍ/ቤት ተጠሪ የሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ የጉዲፈቻ ልጅ መሆን አለመሆናቸውን የማጣራት የሥር ነገር የዳኝነት ሥልጣን አለው ሲል ጉዳዮ ተጣርቶ እንዲወሰን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.343/1/ መሠረት የመለሰበትን አግባብ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ቁ.361/1996 አንቀፅ 41 መሠረት ለመመርመር ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡አመልካችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

 

የጉዳዮ አመጣጥ ከዚህ በላይ አጠር ተደርጐ የተመዘገበዉ ሲሆን እኛም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው የስር ፍ/ቤት ውሣኔ እና አግባብነት ካለው የህግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ መርምረናል ፡፡

 

እንደመረመርነውም አመልካች ከስር ፍ/ቤት ጀምረው የሚከራከሩት ተጠሪ የሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ የጉዲፈቻ ልጅ አይደለም በማለት ሳይሆን ተጠሪ ከሟች በተፈጥሮ የተወለዱ ልጅ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ልጅነኝ ብለው የወሰዱት የወራሽነት ማስረጃ ሊሰረዝ ይገባል በማለት ነው ተጠሪ በበኩላቸው የሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ የጉዲፈቻ ልጅ መሆናቸውንና ለዚህም ማስረጃ ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡

 

ጉዳዮን በመጀመሪያ የተመለተው የአዲሰ አበባ ከተማ የመጀ/ደ/ፍ/ቤት ከግራ ቀኙ ከርክር አንፃር ተጠሪ ከሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ በተፈጥሮ የተወለዱ መሆኑን ገልፀው ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት የወራሽነት ማስረጃ ወስደዋል ወይስ አልወለዱም የሚለውን ጭብጥ ለማጣራት ተጠሪ የወራሽነት ማስረጃ ወስደዋል የተባለበትን መዝገብ አሰቀርቦ አልተመለከተምደ ግራ ቀኙንም በዚህ ነጥብ ላይ አላከራከረም ፡፡

 

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 በአንቀጽ 182 የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደተጠበቀው ሆነው የጉዲፈቻ ልጅ በማናቸውም ረገድ ቢሆን እንደጉዲፈቻ አድራጊው ልጅ የሚቆጠር መሆኑን ደንግጓል፡፡ የጉዲፈቻ ስምምነት በጉዲፈቻ አድራጊውና በልጁ አሳዳሪ መካከል የሚደረግ መሆኑ በዚሁ ሕግ አንቀፅ 190 የተመለከተ ሲሆን የጉዲፈቻ ስምምነትን  አስመልክቶ


ስለ ፍ/ቤት ስልጣን በአንቀጽ 194 ተደንግጓል፡፡ የጉዲፈቻ ስምምነትን በተመለከተ የፍ/ቤት ሚና ስምመነቱን ከማፅደቁ በፊት በዚህ አንቀፅ ከንዑስ አንቀፅ 2 እስከ 4 የተመለከቱ መመዘኛዎችን የማጣራትና የማረጋገጥ መሆኑን ከድንጋጌው መረዳት ይቻላል፡፡ የጉዲፈቻ ስምምነቱ የሚሰረዝበትን የሕግ አግባብ በተመለከተም በአንቀፅ 196 ተመልክቷል ፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ የተጠሪ አጥብቀው የሚከራከሩት የሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ የጉዲፈቻ ልጅ ስለመሆናቸው ማስረጃ ያላቸው መሆኑ እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.145 መሠት በፍ/ቤቱ ትህዛዙ ማስረጃ እንዲቀርብላቸው ነው፡፡ ተጠሪ ባቀረቡት እና እንዲቀርብ የጠየቁ ማስረጃ እንዲቀርብ አድርጐ የሟች ወ/ሮ ፋንታዬ መተኪያ የጉዲፈቻ ልጅ መሆን አለመሆናቸውን ማስረጃን በመመርመር ወራሽ ናቸው ወይም ወራሽ አይደሉም ብሎ ውሣኔ መስጠት፣የተፈጥሮ ልጅነት ከሚረጋገጥበት በህጉ ከተመለከተው ስርዓት የተለየ ነው ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶችን የዳኝነት ሥልጣንን የደነገገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁ.361/1995 አንቀጽ 41/ሸ/ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት የወራሽነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታን ለማየት የዳኝነት ሥለጣን ያላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የቤተሰብ ሕግ በተመለከተው መሠረት የተደረገ የጉዲፈቻ ስምምነት ማስረጃን ተመልክቶ ወራሽነት ማስረጃን በስተት የአ/ከተማ ፍ/ቤት ስልጣን ሆኖ እያለ ክርክሩ የጀመረበት የአ.አ.ከተማ የመጀ/ደ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን የክርክር ይዘት በውል ባለማጤን የልጅነት ክርክርን ለማየት ስልጣን የለኝም በተገቢው ፍ/ቤት ተጣርቶ ይቅረብ ብሎ የሰጠው ብይን ተገቢ አለመሆኑን እና  የተጠሪን የጉዲፈቻ ልጅ ማስረጃን ተመልክቶ የመሰለውን እንዲወሰን የአ.አ.ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሣኔ የሚነቀፍ ሆኖ አላገኘነውም ፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. የአ.አ. ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.22960 በቀን 30/07/2007 ዓ.ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.348/1/ መሠረት ፀንቷል ፡፡

2. በዚህ ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ላደረጉት ክርክር ያወጡትን ወጭ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል ፡፡

3.  መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ይመለስ ፡፡


 

 

መ/ተ