108335 rural land/ Oromia region

በኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ መሰረት ይዞታን የመጠቀም መብት የሚተላለፈው በውርስ ሕግ መሰረት በይዞታው የመጠቀም መብት ላለው የቤተሰብ አባል ሲሆን በዚሁ አግባብ ቅድሚያ የውርስ መብት የሚሰጠው ከመሬቱ በሚያገኙት ገቢ ለሚተዳደሩ(ሌላ መተዳደሪያ)ገቢ ለሌላቸው ወራሾች ሥለመሆኑ የኦሮሚያ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ቁ. 130/1999 አንቀፅ 9(1)(2) አዋጁን ለማስፈፀም የወጣው ደንብ ቁጥር 151/2005 አንቀፅ 10(1)

 

የሰ/መ/ቁ.ጥር 108335

የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡-ተሻገር ገ/ሥላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብረሃ መሰለ

አመልካቾች፡-

 

1.  አቶ ዓለሙ ስሜ - ቀረቡ

2. ወ/ሮ ታደሱ ስሜ - የቀረበ የለም ተጠሪዎች፡-

1.  ወ/ሮ ብዙነሽ ስሜ - ቀረቡ

2.  ወ/ሮ ፀዳሉ ስሜ -  ቀረቡ

3.  አቶ ተሾመ ሽሜ

4.  ወ/ሮ ሰላማዊት ስሜ         ወኪል 1ኛ ተጠሪ ቀረቡ

5.  ወ/ሮ ወርቅነሽ ስሜ

6.  አቶ ብርሃኑ ስሜ           የቀረበ የለም

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ በገጠር የእርሻ ይዞታ ላይ የተነሳ የውርስ ይገባኛል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሾች የነበሩት የአሁኖቹ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉት ተጠሪዎች በደብረ ሊባኖስ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሳሽ በነበሩት የአሁኑ 1ኛ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ ነው፡፡የአሁኗ 2ኛ አመልካች በዋናው ክርክር ጊዜ በጉዳዩ በጣልቃ ገብነት የተከራከሩ ሲሆኑ የአሁኖቹ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች ደግሞ በጉዳዩ ላይ የወረዳ ፍርድ ቤቱ በ27/07/2006 ዓ.ም. ውሳኔ ከሰጠ በኃላ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 358 ድንጋጌ መሰረት ወደ ጉዳዩ የገቡ ናቸው፡፡

 

ፍርድ ቤቱ በከሳሾች እና በተከሳሽ፣እንደሁም በጣልቃ ገቧ የአሁኗ 2ኛ አመልካች መካከል የነበረውን ክርክር መርምሮ ክርክር ያስነሳውን የእርሻ መሬት፣ እንዲሁም የእንስሳት ግምት ብር 7,000 (ሰባት ሺህ) ከሳሾች እና ተከሳሽ እኩል ይካፈሉ በማለት በመዝገብ ቁጥር 12083 በ27/07/2006 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጥቶአል፡፡ከዚህ በኃላ የእርሻ ይዞታው እና የከብቶቹ ግምት በውርስ


ሊተላለፍ የሚገባው ለከሳሾች እና ለተከሳሹ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጭምር በመሆኑ ውሳኔው ሊሻሻል ይገባል በማለት የአሁኖቹ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 358 ድንጋጌ መሰረት በ24/10/2006 ዓ.ም. የተጻፈ የመቃወም አቤቱታ በማቅረባቸው መዝገቡ ተንቀሳቅሶ የስር ከሳሾች ውሳኔው መቃወሚያ አቅራቢዎቹ በጠየቁት አግባብ ቢሻሻል ተቃውሞ እንደሌላቸው በመግለጽ መልስ የሰጡ ሲሆን የስር ተከሳሽ  በበኩላቸው  በሰጡት መልስ መቃወሚያ አቅራቢዎቹ ከሟች ስሜ ደገፋ የሚወለዱ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ እና በደመወዝ የሚተዳደሩ በመሆናቸው እና የሟች የቤተሰብ አባል ከሳሽ ብቻ በመሆናቸው ጥያቄአቸው ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት የተከራከሩ መሆኑን የመዝገቡ  ግልባጭ ያመለክታል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር መርመሮ መቃወሚ አቅራቢዎቹ የሟች ስሜ ደገፋ ልጆች እና ወራሾች መሆናቸው አልተካደም በማለት የቀድሞውን ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 360 (2) መሰረት አሻሽሎ ክርክር ያስነሳውን የእርሻ መሬት፣እንዲሁም የእንስሳት ግምት ብር 7,000 (ሰባት ሺህ) ከሳሾች፣ተከሳሽ እና መቃወሚያ አቅራቢዎቹ እኩል ሊካፈሉ ይገባል በማለት በ09/11/2006 ዓ.ም.ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የአሁኖቹ አመልካቾች ባቀረቡት ይግባኝ ሳቢያ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔን አጽንቷል፡፡

 

አመልካቾቹ አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የክልሉ  ሰበር  ችሎት የቀረበለትን አቤቱታ ዘግቶ በማሰናበቱ ሲሆን ለዚህ ችሎት የቀረበው አቤቱታ ተመርምሮ የአሁኖቹ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ እና በደመወዝ የሚተዳደሩ በመሆናቸው የገጠር የእርሻ ይዞታን የመውረስ መብት የላቸውም በማለት የአሁኑ 1ኛ አመልካች ያቀረቡት ክርክር በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ተጠሪዎቹ ባሉበት ለማጣራት ይቻል  ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በጉዳዩ እልባት ማግኘት የሚገባቸው፡-

 

1. 2ኛ ተጠሪ በዚህ መዝገብ በአመልካችነት የመከራከር መብት አላቸው ወይስ የላቸውም?

2. 1ኛ አመልካች በ27/07/2006 ዓ.ም. በወረዳው ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ላይ በዚህ መዝገብ ያቀረቡት የክርክር ነጥብ በዚህ መዝገብ ሊስተናገድ የሚችል ነው ወይስ አይደለም?


3. የቀድሞውን ውሳኔ በማሻሻል በወረዳው ፍርድ ቤት ተሰጥቶ በክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው ውሳኔ የተሰጠው ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ፍሬ ነገሮች በአግባቡ እንዲጣሩ ከተደረገ በኃላ ነው ወይስ አይደለም?

የሚሉ መሆናቸውን በመገንዘብ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ከእነዚሁ ነጥቦች አንጻር መርምረናል፡፡

የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ አመልካች በወረዳው ፍርድ ቤት በጣልቃ ገብነት የክርክሩ ተካፋይ የነበሩት የመቃወም አቤቱታ ከመቅረቡ በፊት በነበረው ሂደት ነው፡፡የመቃወም አቤቱታው ከቀረበ በኃላ 2ኛ አመልካች የክርክሩ ተካፋይ የነበሩ ስለመሆኑ የመዝገቡ ግልባጭ አያመለክትም፡፡ቀደም ሲል እንደተገለጸው የመቃወም አቤቱታው ከመቅረቡ በፊት  ውሳኔ የተሰጠው በ27/07/2006 ዓ.ም. ሲሆን የመቃወም አቤቱታ ከቀረበ በኃላ ውሳኔ የተሰጠው ደግሞ በ09/11/2006 ዓ.ም. ነው፡፡2ኛ አመልካች በ27/07/2006 ዓ.ም. በተሰጠባቸው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካላቸው በውሳኔው ላይ ያላቸውን ይግባኝ እና አቤቱታ ስርዓቱን ጠብቀው ማቅረብ ይችሉ የነበረ ከመሆኑ ውጪ ተካፋይ ባልተደረጉበት ክርክር በ09/11/2006 ዓ.ም. በተሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እና አቤቱታ ማቅረብ የሚችሉበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ የለም፡፡በመሆኑም 2ኛ ተጠሪ በዚህ መዝገብ በአመልካችነት የመከራከር መብት አላቸው ማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ሁለተኛውን ነጥብ በተመለከተ ለዚህ ሰበር ክርክር መነሻ የሆነው የመቃወም አቤቱታ ከቀረበ በኃላ በ09/11/2006 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ በመሆኑ 1ኛ አመልካች ይግባኝ እና አቤቱታ ማቅረብ የሚገባቸው ይህንኑ በ09/11/2006 ዓ.ም. የተሰጠውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ከሚሆን በቀር የኃለኛውን ውሳኔ አስታከው የመቃወም አቤቱታ ከመቅረቡ አስቀድሞ በ27/07/2006 ዓ.ም.በተሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እና አቤቱታ ሊያቀርቡ የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡በመሆኑም 2ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች ጭምር የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመሆናቸው የእርሻ መሬት የመውረስ መብት የላቸውም፣በ3ኛ ተጠሪ እጅ የሚገኝ የውርስ ንብረት ጭምር መኖሩን በመጥቀስ ያቀረበኩት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ የታለፈብኝ አላግባብ ነው በማለት 1ኛ አመልካች ያቀረቡት ክርክር በዚህ መዝገብ ሊስተናገድ የሚችል ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ሶስተኛውን ነጥብ በተመለከተ 1ኛ አመልካችም ሆኑ ተጠሪዎቹ የሟች ስሜ ደገፋ ልጆች እና ወራሾች መሆናቸው በግራ ቀኙ ያልተካደ ሲሆን የአንድ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር በመሬት ይዞታ የመጠቀም መብት በውርስ የሚተላለፈው በውርስ ሕግ መሰረት በይዞታው የመጠቀም መብቱን የመውረስ መብት ላለው የቤተሰብ አባል ስለመሆኑ በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 9 (1) ስር የተመለከተው ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅድሚያ የውርስ መብት የሚሰጠው ከመሬቱ በሚያገኙት ገቢ ለሚተዳደሩ ወይም  ሌላ  መተዳደሪያ  ገቢ  ለሌላቸው  ወራሾች  እንደሆነ  በአዋጁ  አንቀጽ  9  (2)  ስር


ተመልክቶአል፡፡አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ቁጥር 151/2005 አንቀጽ 10 (1) ስር ያለው ድንጋጌም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው፡፡ የአሁኖቹ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ እና በደመወዝ የሚተዳደሩ በመሆናቸው የገጠር የእርሻ ይዞታን የመውረስ ቀዳሚ መብት ያላቸው የሟች ቤተሰብ አባል ሆነው ከእርሻ መሬቱ በሚገኘው ገቢ የሚተዳደሩ የአሁኑ 1ኛ አመልካች መሆናቸውን በመግለጽ የአሁኑ 1ኛ አመልካች መከራከራቸውን እና 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሳይሆኑ የእርሻ መሬቱ የሚገኝበት ቀበሌ ነዋሪዎች መሆናቸውን በመግለጽ የተከራከሩ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች ይህንን መከራከሪያ ሳይቀበሉ የቀሩት ሁሉም ወራሾች በእርሻ መሬት አወራረስ ላይ እኩል መብት እንዳላቸው በመቁጠር እንደሆነ የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡በመሆኑም በአንድ በኩል በ1ኛ አመልካች አና በሌላ በኩል ደግሞ በ5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች መካከል የተነሳውን ክርክር በማስረጃ ሳያጣራ ሁሉም ወራሾች በእርሻ መሬት ላይ እኩል መብት እንዳላቸው በመቁጠር መሬቱን እኩል እንዲካፈሉ በወረዳው ፍርድ ቤት የተሰጠው እና በክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው ውሳኔ በስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከተውን የክርክር አመራር ስርዓት መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ አልተገኘም፡፡ከእርሻ ይዞታው ውርስ ጋር ተያይዞ በተነሳው ክርክር ከሟች የተላለፉት እንስሳት ውርስ ጉዳይ የሚገዛው ውርስን በሚመለከቱ የፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች መሰረት በመሆኑ የእንስሳቱን ግምት ብር 7,000 (ሰባት ሺህ) ከሳሾች፣ተከሳሽ እና መቃወሚያ አቅራቢዎቹ እኩል ሊካፈሉ ይገባል በማለት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል የሚነቀፍበትን ሕጋዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡

 

ሲጠቃለል አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. 2ኛ አመልካች ተከራካሪ ወገን ባልነበሩበት በ09/11/2006 ዓ.ም. በተሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እና አቤቱታ የማቅረብ መብት የላቸውም በማለት ወስነናል፡፡

2. በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ሊባኖስ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 12083 በ09/11/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 47817 በ28/12/2006 ዓ.ም. በፍርድ እና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 187287 በ09/04/2007 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

3. የእንስሳቱን ግምት ብር 7,000 (ሰባት ሺህ) ከሳሾች፣ተከሳሽ እና መቃወሚያ አቅራቢዎቹ እኩል ሊካፈሉ ይገባል በማለት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል፡፡


4. ክርክር ያስነሳውን የእርሻ ይዞታ ከሳሾች፣ተከሳሽ እና መቃወሚያ አቅራቢዎቹ እኩል ሊካፈሉ ይገባል በማለት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል፡፡

5. የአሁኖቹ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች የመኖሪያ አድራሻ እንደ 1ኛ አመልካች አባባል በአዲስ አበባ ከተማ ነው ወይስ እንደ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች አባባል ክርክር የተነሳበት የእርሻ መሬት በሚገኝበት ወረዳ እና ቀበሌ ነው? 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች ከደመወዝ በሚገኝ የሚተዳደሩ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚሉትን እና ተያያዥ ነጥቦችን በግራ ቀኙ ማስረጃ፣እንደሁም ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ሁሉ በፍርድ ቤት በትዕዛዝ በሚቀርብ የማጣሪያ ማስረጃ እንዲጣራ ካደረገ በኃላ 5ኛ እና 6ኛ ተጠሪዎች በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 9 (2) እና በደንብ ቁጥር 151/2005 አንቀጽ 10 (1) ድንጋጌዎች አነጋገር መሰረት ክርክር የተነሳበትን የእርሻ ይዞታ ውርስ የመካፈል መብት ያላቸው መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 343 (1) መሰረት ለደብረ ሊባኖስ ወረዳ ፍርድ ቤት እንዲመለስ ወስነናል፡፡

6. የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ተገቢውን መፈጸም ያስችለው ዘንድ ለደብረ ሊባኖስ ወረዳ ፍርድ ቤት፣እንዲያውቁት ደግሞ ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይላክ፡፡

7.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

8.  ውሳኔ ያገኘ ሰለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

የ/ማ