Federal Courts Draft Proclamation (Ethiopia)

Amharic

English

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ
ላይ የቀረበ አጭር ማብራሪያ

 1. ስለረቂቅ አዋጁ መቅድም (Preamble)

 
ከአዋጅ ቁጥር 25/1988 ጋር ሲነፃፀር በረቂቅ አዋጁ መቅደም ላይ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ድረስ እንዲገቡ የተደረጉት አንቀፆች (paragraphs) አዳዲስ ናቸው፡፡
ሁለተኛ አንቀጽ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ (1) ላይ የማንኛውንም ሰው ፍትህ የማግኘት መብትን በተመለከተ የተደነገገውን መሠረት በማድረግ ተቀርፆ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ነው፡፡
ሶስተኛው አንቀጽ ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትን ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ አዋጁ የወጣ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
 አራተኛው አንቀጽ ላይ ደግሞ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ ላይ ስለዳኝነት ነፃነት በተጠቀሰው መሠረት ተግባራቸውን ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እና ተገማች የሆነ አገልግሎት መስጠታቸው አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ መታወጁ ተመልክቷል፡፡
አምስተኛዉ አንቀጽ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በበጀት ምደባ እና አስተዳደር በሰዉ ሀብት ቅጥር እና ምደባ እንዲሁም አስተዳደር ራሳቸዉን ችለዉ የሚሰሩበትን ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ አዋጁ እንዲወጣ ተመላክቷል።
አዋጅ ቁጥር 25/1988 ቁጥራቸው 138/1991፣ 254/1993፣ 321/1995 እና 454/1997 በሆኑ አዋጆች መሻሻሉና በተጨማሪም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 መታወጁ አዋጆቹ በዝተው ለአሰራር አመቺ ያልሆነ ሁኔታን ስለፈጠሩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን አንድ ወጥ በሆነ አዋጅ መተካት በማስፈለጉ መታወጁ ስድስተኛው አንቀጽ (paragraph) ላይ ተጠቅሷል፡፡

 1. የሐረጐችንና የቃላት ትርጓሜን በተመለከተ የተደረጉ ለውጦች እና አዲስ ስለገቡ ትርጓሜዎች

  በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 2 ላይ ትርጓሜ በሚለው ስር ትርጉም ከተሰጣቸው ሀረጐች ለ "ሕገ መንግሥት" ፣ "መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት"፣ "የመጨረሻ ውሳኔ" እና «የአስተዳደር ሰራተኛ» ለሚሉት ሀረጐች ትርጉም የተሰጠባቸው አራት አዳዲስ ንዑስ አንቀፆች ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 ላይም ሆነ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ "ሕገመንግሥት" የሚለው ሀረግ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ በመሆኑ የዚህ ሀረግ ትርጓሜው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ የመጨረሻ ውሳኔ መሠታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለበት የሚባለው ውሳኔው ምን ዓይነት ስህተት ሲኖርበት ነው? ለሚለው ምላሹ እስካሁን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት ላይ የሚሰየሙ ሶስት ዳኞች የመጨረሻ ውሳኔው መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለው ወይም የለውም ብለው ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ አለበት የተባለው ለሰበር ሰሚው ችሎት ቀርቦ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ እነዚህ ሶስት ዳኞች መሠታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለበት ብለው ያስቀርባል በማለት ትዕዛዝ የሰጡበት የመጨረሻ ውሳኔ አምስት ዳኞች የሚሰየሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከቀረበ በኋላ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ የሚወሰንበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ይህ ሁኔታ ሶስት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት ዳኞች መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለበት ብለው ትዕዛዝ የሰጡበት ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ በአምስት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኞች ውድቅ የሚደረገውን ያህል መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለባቸው ነገር ግን አያስቀርቡም የተባሉ ጉዳዮች ሊኖሩ አይችሉም ማለት ያስቸግራል፡፡ መሠረታዊ ስለሆነ የሕግ ስህተት በረቂቅ አዋጁ ላይ ትርጉም እንዲኖረው ማድረጉ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን ችግር ጭምር በጉልህ ከማቃለሉም በተጨማሪ ባለጉዳዮችም በተሰጠባቸው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሰበር አቤቱታ ከማቅረባቸው በፊት አቤቱታቸው የሚያዋጣ መሆን አለመሆኑን በቅድሚያ ለመመዘን ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በረቂቅ አዋጁ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ለሚለው ሀረግ ትርጉም እንዲገባ ተደርጓል፡፡
    መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ለሚለው ሀረግ የተሰጠው ትርጓሜ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 2 ከንዑስ አንቀጽ(4)(ሀ) እስከ(4)(ሰ) በተጠቀሱት መመዘኛዎች ላይ ብቻ ሳይወሰን በተጨማሪ በአንቀጽ 4 (ሸ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተትን ትርጉም በተመለከተ እስካሁን የሰጣቸው አስገዳጅነት ያላቸው ውሣኔዎች እና ወደፊትም በችሎቱ የሚሰጡ እንዲሁም በመሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ለሚለው ሀረግ በረቂቅ አዋጁ ላይ ትርጉም ሲሰጥ አንድ የመጨረሻ ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው የሚባለው የመጨረሻው ውሳኔ ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ስህተት ስለሆነ፧ አላግባብ ስለተተረጐመ፣ ጭብጥ አላግባብ ስለተያዘ፣ ወዘተ ብቻ ሳይሆን ስህተቱ በውሳኔው ላይ ፍትህን የሚያዛባ ጉልህ ውጤት አስከትሏል ወይ? የሚለው ነጥብ መታየት የሚገባው ነው ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የመጨረሻ ውሳኔዎች በውሳኔያቸው ላይ መንደርደሪያቸው ላይ ጉልህ ስህተት ቢኖራቸውም በውጤት ደረጃ ፍትህ የማያዛቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ በውጤት ደረጃ ስህተተ የሌለበት ነገር ግን በውሳኔ አፃፃፍ ረገድ ግን ስህተት ቢኖርበትም የግድ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት የመጨረሻ ውሳኔ ነው ሊባል አይገባም።
ሌላዉ ትኩረት የተሰጠው ነጥብ ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የክልል ፍርድ ቤቶች የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተሞች ፍርድ ቤቶች እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን የመጨረሻ ውሳኔ በተመለከተ የሚቀርቡ የሰበር ማመልከቻዎችን ሁሉ የግድ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መቅረብ አለባቸው ወይ? የሚለው ነጥብ መፍትሔ የሚሻ ነበር፡፡ ለዚህም መነሻ የሆነው በአሁኑ ጊዜ የገጠር መሬት ይዞታን እና ከመሬቱ ላይ የሚገኘውን አላባ በተመለከተ በክልል ፍርድ ቤቶች በተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ የሰበር አቤቱታ ለማቅረብ በጣም እሩቅ ከሆኑ የሀገሪቱ ክልሎች ጭምር ባለጉዳዩች አዲስ አበባ መጥተው ሲጉላሉ መታየታቸው አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በማህበራዊ ፍርድ ቤቶችና የመጀመሪያ እርከን ላይ ባሉ የክልል ፍርድ ቤቶች ተጀምረው በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ሰበር ሰሚ ችሎቶች እና በከተሞች ፍርድ ቤቶች ሰበር ሰሚ ችሎቶች የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠባቸው ባለጉዳዮች ጭምር ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ለማቅረብ ለከፍተኛ ወጪ እና መጉላላት ይዳረጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህንና ሌሎች ተመሣሣይ ችግሮችን ለማስቀረት ሲባል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሰበር ሰሚ ችሎት ሊቀርቡ የማይገባቸውን የጉዳይ አይነቶች በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተጠቅሷል።
   የፊደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአቃጅ 25/88 ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የፌደራልም ይሁን የክልል ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት በማረም ረገድ ዳኝነት መስጠቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀርቡ ጉዳዮች አይነት እየጨመሩ መጥተዋል። በተለይም አዋጅ 454/97 የሰበር ችሎቱ የሚሰጣቸዉ የህግ ትርጓሞዎች በማንኛዉም ደረጃ ለሚገኝ የስር ፍርድ ቤት አስገዳጅ መሆኑ ሰበር ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል። ይሁንና በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚስተዋለዉ የጉዳዮች ፍሰት ከታች ጠበብ ብሎ ከላይ ሰፋ ያለ የዋርካ አይነት ቅርጽ የያዘ ሲሆን መሆን የነበረበት ግን የፒራሚድ ቅርጽ ነዉ። ለሰበር የሚቀርቡ ጉዳዮች መብዛት ሰበር የሚሰጠዉ የህግ ትርጉም ጥራት ላይ ጥላዉን እንዳያጠላ ስጋት ሊሆንም ይችላል። በመሆኑም ጉዳዮችን የማጣራት ተግባር በህግ ማእቀፍ ዉስጥ ማካተት አንዱ ስራ ነዉ።
  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣንን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ላይ የነበረው ድንጋጌ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለባቸውን እና አንቀጹ ላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በሰበር የማየት ሥልጣን ያለው መሆኑ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 10 ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ ንዑስ አንቀፆች እንዳሉ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
  በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ (1)፣ (2) እና (3) ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን ያለው መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ጉዳይ ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን ያለው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ያለውና ዝርዝሩም በሕግ የሚወሰን መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን በክልል ጉዳዮች የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ያለውና ዝርዝሩም በሕግ የሚወሰን መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
 ከፍ ሲል የተጠቀሱት የሕገ-መንግስቱን ንዑስ አንቀጾች በተመለከተ በህገ-መንግስት ጉባኤው ውይይት በተደረገበት ጊዜ በተያዘው ቃለ-ጉባኤ ላይ የተመዘገበው የአንድ አባል አስተያየት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎችን በሰበር ማየት እንደሚችል አመላካች መሆኑ የተጠቀሰ ቢሆንም ይህ መሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የክልልን ጉዳይ በተመለከተ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎችን የግድ በሰበር የማየት ሥልጣን አለው ማለት አለመሆኑ ክርክር የቀረበበት ነጥብ ነው፡፡
የሰበር ሰበር ህገ-መንግስታዊነት ክርክር ጉዳይ እልባት ሊያገኝ የሚችለዉ በህገ-መንግስት ተርጓሚ አካል መሆኑ የሚታዎቅ ሲሆን ካሉት ችግሮች እና የፍርድ ቤቶች ነባራዊ ሁኔታን ከግምት በማስገባት በመርህ ደረጃ የክልል ጉዳይ የህግ ስህተት በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ከታረመ ቡሃላ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ሊቀርብ የሚችለዉ በሶስት ነገሮች ብቻ እንዲሆን ተደርጓል።
የመጨረሻ ዉሳኔ ተደርጎ የሚቀርበዉ የክልል ሰበር የወሰነዉ ዉሳኔ

 • የኢፌዲሪ ህገ-መንግስትን ድንጋጌዎች የሚቃረን ሲሆን

 • የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጣቸዉን አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች የሚቃረን ሲሆን

 • የህግ ስህቱቱ የተፈጠረበት ጉዳይ ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ክፍልን በሚነካ መልኩ ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖረዉ ሲሆን

 

 1. ስለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወል የዳኝነት ሥልጣን፡፡

   በአዋጅ ቁጥር 25/1988 ላይ ስለፌዴራል ፍርድ ቤት የወል የዳኝነት ሥልጣን መሠረቱን (Principle) ከሚጠቅሰው አንቀጽ 3 በተለየ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 3 ላይ አዲስ ንዑስ አንቀጽ (2) እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ንዑስ አንቀጹም የዜጐችን ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸዉን በፍርድ ቤቶች የሚያስከብሩበት ጠቅለል ያለ ስልጣን የሚሰጥ ሲሆን መሰረቱም የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 9(2) እና 13(1) ነዉ። ህገ መንግስትን የሚተረጉመዉ የፌደሬሽን ምክር ቤት ነዉ የሚለዉ አገላለጽ ፍርድ ቤቶች የህግ መተርጎም ስራቸዉን በህገ-መንግስቱም ላይ በማድረግ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት የላላ በመሆኑ ይህ ንኡስ አንቀጽ ችግሩን ለመፍታት ያስችላል።
 የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ (9) በአዋጅ ቁጥር 321/1995 ከመሻሻሉ በፊት የውጭ ሀገር ዜጎችን በተመለከተ በሁሉም የወንጀል ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን የነበራቸው መሆኑን ይደነገግ ነበር፡፡ይህ ንዑስ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 6 ሆኖ ሲሻሻል ግን ተፈፃሚነቱ ጠበብ ተደርጎ ፍርድ ቤቶቹ ዓለም አቀፍ የዲኘሎማቲክ ሕጎች እና ልምዶች እንዲሁም ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው ሌሎች አለም አቀፍ ስምምነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ልዩ መብትና ጥበቃ ያላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ሰዎች ተበዳይ ወይም ተከራካሪ የሆኑባቸው ወንጀሎች እንዲሁም አዋጁ ላይ የተጠቀሱ ሌሎች ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከአምስት አመት ጽኑ እስራት በላይ ሊያስቀጡ የሚችሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ተበዳይ ወይም ተከሳሽ በሆኑባቸው ወንጀሎች ላይ የዳኝነት ሥልጣን እንዲኖራቸው ተደርጐ ተሻሽሏል፡፡
    አሁን በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ ላይ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ(2) ላይ የተጠቀሱት የውጭ ሀገር አምባሳደሮች፣ ቆንስላዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የውጭ መንግሥታት ወኪሎች ንዑስ አንቀጹ ውስጥ እንዲጠቀሱ ተደርጓል፡፡ ይህም የተደረገው የእነዚህን ሰዎች ጉዳይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን እንዲያየው ማድረጉ የሰዎቹን የይግባኝ መብት ስለሚያጣብብ እና በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 2ዐ ንዑስ አንቀጽ(6) መሠረት ይግባኝ መብት በመሆኑ የተጠቀሰው ሀረግ ከአንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ(2) ወጥቶ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ (6) ውስጥ እንዲገባ እና ጉዳዮም በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ(1) መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 4 ላይ አዲስ ንዑስ አንቀጽ(17) እንዲገባ የተደረገ ሲሆን ንዑስ አንቀጹም በሌሎች ሕጐች የሚጠቀሱ ጉዳዮችም ሲኖሩ አዋጁ እነዚህንም ማካተት በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቱል፡፡ ሌሎቹ የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀፆች ግን ባሉበት ሁኔታ ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 4 ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
  የውጭ ሀገር ዜጎችን በተመለከተ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሊኖራቸው ስለሚገባው የወንጀል የዳኝነት ስልጣን ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በአዋጅ ቁጥር 321/1995 የተሻሻለ ቢሆንም የውጭ ሀገር ዜጋ ተከራካሪ የሆነበትን የፍትሕ ብሔር ጉዳይን በተመለከተ የተቀረጸው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (4) ግን በተመሣሣይ አልተሻሻለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ገብተው ስራ ላይ የሚሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብዛት ስለሚጨምር እነሱ ተከራካሪ የሚሆኑባቸው የፍትሕ ብሔር ጉዳዮች ሁሉ የፌዴራል ጉዳዮች ስለሆኑ ጉዳዩቹ በሙሉ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እንዲታዩ ማድረግ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላይ የሥራ ጫና መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ሀገር ዜጎችን በተመለከተ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ በተሻሻለው መሰረት የፍትሕ ብሔር የዳኝነት ስልጣንን የሚመለከተው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (1)(ሠ) ተሻሽሎ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ (2) ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሥልጣን ክልላቸውን መሠረት አድርገው የሚያዩት ጉዳይ ወይም ክርክር የክልል ሕግን የሚመለከት ሆኖ ሲገኝ እና የክልሉ ሕግ ከፌዴራል ሕጐችና ከአለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የሚጋጭ ሲሆን የክልሉ ሕግ በጉዳዩ ላይ ተፈፃሚነት የማይኖረው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ንዑስ አንቀጹን ግልፅ በሆነ ቋንቋ ለማስቀመጥ ሲባል ረቂቅ አዋጁ ላይ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በጉዳዩ ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑት የፌዴራል ሕጐች እና አለም አቀፍ ስምምነቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና ይህ አገላለጽ የፌደራል ስርዓታችንን ግምት ያላስገባ እና የፌደራል ህግ ከክልል ህግ ይበልጣል የሚል አይነት አተያይ የሚፈጥር በመሆኑ በረቂቅ አዋጁ እንዲገባ አልተደረገም።
 

 1.  ስለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን

በአዋጅ ቁጥር 25/1988 ስለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን በሚደነግገው አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ(1) እና (2) ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረጉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ(6) ላይ የተጠቀሰውን የሰዎቹን የይግባኝ መብት የሚያጣብብ ከመሆኑም በላይ በንዑስ ቁጥር(2) ላይ የተጠቀሱት የፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣኖች በሥራ ኃላፊነታቸው ምክንያት ተጠያቂ የሚሆኑባቸው የወንጀል ጉዳዮች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን እንዳይታዩ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ውሳኔ የተሰጠበት ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ንዑስ አንቀፆች ወጥተው የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ(3) ላይ የተጠቀሰውን በሕግ በሚወሰነው መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድን ጉዳይ ከአንድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ወደ ሌላ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ወይም በውክልና ለክልል ፍርድ ቤቶች የተሰጡ የፌዴራል ጉዳዮችን በሚመለከት ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲዛወር የሚቀርብን ጥያቄ እና ምናልባትም በሌሎች ህጎች የሚጠቀሱ ጉዳዮች ካሉ ብቻ በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን እንዲያይ እራሱን የቻለ አንቀጽ 8 ሆኖ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
 ጉዳያቸው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን ሲታይ የነበሩት ከፍ ሲል የተጠቀሱት ሰዎች ጉዳይ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ (1) ፣ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ (6) እና (14) ፣ እና አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል፡፡
  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ስልጣንን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9 ሥር የነበሩት ሁለቱ ንዑስ አንቀጾች እንዳለ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ አዲስ በገቡት ንዑስ አንቀጽ (3) እና (4) ላይ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ጉዳዮችን በተወካይነቱ በቀጥታ ዳኝነት አይቶ ውሳኔ የሰጠባቸውን እና በይግባኝ አይቶ የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሰጠው ውሳኔ የተለየ ውሳኔ የሰጠበትን ውሳኔ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የማየት ስልጣን ያለው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች ሕጐች መሠረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ እንዲታዩ የሚወሰኑ ጉዳዮችም በይግባኝ የሚታዩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲባል ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 9 ሥር ይህንኑ የተመለከተ አዲስ ንዑስ አንቀጽ (5) ገብቷል፡፡
 በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ላይ የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ችሎቶች በሰበር የሚሰጡት የመጨረሻ ውሳኔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሊታይ እንደሚችል በግልጽ ስላልተጠቀሰ ይህ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ (1)(ረ) ላይ በግልፅ ተጠቅሶ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱት ዉስጥ ሌላዉ ነጥብ በህግ የመዳኘት ስልጣን የተሰጠዉም ይሁን ሌላ አካል የሚሰጡት የመጨረሻ ዉሳኔ በሰበር ሊታረም የሚችል መሆኑን ነዉ። ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በተቋቋሙባቸው አዋጅ መሠረት የሚሰጡት ውሳኔ እና በሌሎች ሕጐች የሚጠቀሱ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ የሰበር አቤቱታ ማቅረብ እንዲቻል አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ (1)(ሰ) ገብቷል፡፡
  የአዋጅ ቁጥር 25/1988ን ባሻሻለው አዋጅ ቁጥር 454/1997 የአንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ (4) ሆኖ አዋጁ ውስጥ የገባው ንዑስ አንቀጽ ማሻሻያ ተደርጐበት የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ (3) ሆኖ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ (4) ላይ ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ የህግ ትርጉም ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በየትኛዉም ደረጃ በሚገኝ የፌደራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤት አስገዳጅነት ይኖረዋል። ነገር ግን የሰበር ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተለየ ትርጉም ሊሰጥበት እንደሚችል የሚጠቅስ የነበረዉ አንቀጽ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት የሆነዉ የፌደራል ሰበር ችሎት በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የህግ ትርጉሞችን በመስጠት ቀድሞ የተሰጠዉ ትርጉም በግልጽ ሳይሻር እና መሻሩ አንኳን ሰይታወቅ ሰዎች በተለምዶ እርስ በርሱ የሚቃረን የሰበር ዉሳኔ አለ እስከማለት ደርሰዋል፡፡
 
   ስለዚህ ይህን ችግር ለማስቀረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመታየት ላይ ካለ ጉዳይ ጋር ተመሣሣይነት ያለው አስቀድሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ አስገዳጅነት ያላቸው ውሳኔዎች እርስ በርሳቸዉ የሚቃረኑ ሆነዉ ሲገኙ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 25 ንዑስ አንቀጽ(1) (ሀ) ላይ በተደነገገው መሠረት ጉዳዩ ከሰባት ያላነሱ ዳኞች በሚሰየሙበት የሰበር  ችሎት ታይቶ ሊወሰን እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍ ሲል በተጠቀሰው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ(3) ላይ የሰበር ሰሚ ችሎት በሌላ ጊዜ በተመሣሣይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል  የሚለው የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር እንዲወጣ ተደርጐ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የክልል ወይም የፌዴራል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት የሚኖረው መሆኑን እና ውሳኔ ታትሞ የሚሰራጭ መሆኑን እንዲገልፅ ተደርጐ የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ(3) ሆኖ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
   የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እስካሁን ከሰጣቸው አስገዳጅነት ካላቸው ውሳኔዎች መካከል ተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተሰጠ የተለያየ የህግ አተረጓጎም ባለበት የችሎቱ አስገዳጅ ውሳኔዎች እንዴት መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የሚለውን ሀረግ ለመተርጐም እንደመመዘኛ ሊወስዱ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከሚሰጠው ምላሽ መካከል በተመሣሣይ ጉዳይ ላይ መጨረሻ የተሰጠው ውሳኔ ቀደም ሲል የተሰጠውን ውሳኔ አስገዳጅነት ስለሚያስቀረው ጉዳዩ አከራካሪ አይደለም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በኋላ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በእርግጥ በፊት ከተሰጠው ህጋዊ እና ፍትሐዊ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ሊያስነሣ ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነቶቹን እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ የሚመስሉ ውሳኔዎችን ወይም ሰበር በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ በተለያየ ጊዜ የተለያየ የህግ ትርጉም የሰጠባቸዉን ዉሳኔዎች በተመለከተ የሚነሳ ክርክር በረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 25 ንዑስ አንቀጽ (1)(ሀ) ላይ በተጠቀሰው መሠረት መፍትሔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመታየት ላይ ካለ ጉዳይ ጋር ተመሣሣይነት ያላቸው አስቀድሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ አስገዳጅነት ያላቸው ውሳኔዎች አከራካሪ ሆነው ሲገኙ ጉዳዩ በሰበር ሰሚው ችሎት ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት ከሰባት ያላነሱ ዳኞች በሚሰየሙበት የሰበር ችሎት ታይቶ እንዲወሰን በሚያስችል መልኩ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም የሚሆነዉ ከተከራካሪዎቹ አንደኛዉ ከአምስት ያላነሱ ዳኞች ለሚሰየሙበት የሰበር ችሎት አመልክቶ የሰበር ችሎቱም ቀድሞ የተሰጠዉን የህግ ትርጉም ለመቀየር በቂ ምክንያት በመጥቀስ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መምራት ይኖርበታል። ፕሬዝዳንቱም ባለ ሰባት ዳኞች የሰበር ችሎት በመሰየም ጉዳዩ ከሰባት ዬነሱ ዳኞች የሰበር ችሎት እንዲታይ ያደርጋል። ይሁንና ባለሰባት ዳኞች ሰበር የወሰነዉን ዉሳኔ በሌላ ጊዜ መቀየር ካስፈለገ ተመሳሳይ ሰባት ዳኞች የሚሰየሙበት ችሎት የቀደመዉን ዉሳኔ በግልጽ በመተቸት ሊቀይር እንደሚችል በረቂቁ ተካቷል።
 
 
 
 
 
 

 1. ስለ ፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የፍትሐብሔር፣ የወንጀል እና የይግባኝ የዳኝነት ሥልጣን እንዲሁም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የወንጀል እና የፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣንን እና ይግባኝን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 ከአንቀጽ 11 እስከ 16 ድረስ የተዘረዘረ ሲሆን እነዚህ አንቀጾች ቀጥሎ የተጠቀሱት ማሻሻያዎች ተደርገውባቸው ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጥታ ክስን የሚቀበል እና ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ወይስ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን በማጠናከር አብዛኛው ጉዳይ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፌዴራል ከፍተኛ በአብዛኛው ይግባኝ ሰሚ ሊሆን ይገባል የሚለው ነጥብ የዚህ ረቂቅ ሕግን አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ሲያወያይ የቆየ ነጥብ ነው፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ኮሚቴው ያሰራጨውን ቃለመጠየቅ የተሰጠውን ምላሽ እና ውይይት መሠረት በማድረግ የረቂቅ አዋጁ ከአንቀጽ 11 እስከ 16 ያለው አሁን በቀረበበት መልኩ ተዘጋጅቶ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
  በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 11 መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግምታቸው ከብር 10,000,00 በላይ በሆኑና በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 3 እና 5 መሠረት በሚቀርቡ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፤ በአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተሞች ውስጥ በሚነሱ ሌሎች የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፣ ጉዳይን የማዛወርና በሌሎች ሕጐች በፍርድ ቤቱ እንዲታዩ የሚወሰኑ ጉዳዮችን እንደሚያይ ተጠቅሷል፡፡ ቀድሞ የነበረዉን ከ500,000 በላይ የሚገመት የፍታብሄር ጉዳይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይቀርብ የነበረን ጉዳይ ወደ 10 ሚሊዮን ብር ከፍ ሲደረግ በርከት ያሉ ምክንያቶች የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ዉሥጥ የመጀመሪያዉ ህግ ሲወጣ በ1988 ዓም የነበረዉ ገንዘብ በምን ያክል መጠን ጋሽቧል፣ አሁን ያለዉ የክርክር ብዛት ምንያክል ነዉ እና ወደ ፊትም የገንዘብ ግሽበትን ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታዎችን ግምት ዉስጥ በማስገባት ነዉ።
   በአንቀጽ 12 እና 15 ላይ ስለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የወንጀል የዳኝነት ሥልጣን እና ስለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተጠቀሰ ሲሆን አንቀጽ 13 ላይ ደግሞ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ የዳኝነት ሥልጣን ተጠቅሷል፡፡ የወንጀል የዳኝነት ስልጣንን በሚመለከት የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግ እየተሻሻለ በመሆኑ የየፍርድ ቤቶቹን የወንጀል የስረ-ነገር የዳኝኘት ስልጣን በፌደራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ ዝርዝሩን ከማካተት ይልቅ አግባብነት ያለዉ የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግ ተግባራዊ እንዲሆን ማመላከት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። በተለይም ድግግሞሽን ከማስቀረት አንጻር እና የወንጀል ስረ-ነገር ስልጣንን በዝርዘር መደንገግ የስነ-ስርዓት ህጎች እንጅ የፍርድ ቤት አዋጅ መሆን አንደሌለበት በመገንዘብ አግባብነት ያለዉ የስነ-ስርዓት ህግ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸን አልፈነዋል።
  ሌላዉ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 11 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የፍታብሄር ስልጣን እንዲሆን የተካተተዉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍርድ ታይተዉ ሊዎሰኑ የሚችሉ በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት ስር የተመለከቱ መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን ለማስከበር ለጉዳዩ ተገቢ የሆነ ፍርድ፣ትዕዛዝ ወይም ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን እንዲኖረዉ ነዉ። እዚህ ላይ በረቂቁ አንቀጽ 3 ስር የፌደራል ፍርድ ቤቶች የህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ማድረግ እናዳለባቸዉ ጠቅለል ባለ ሁኔታ ያስቀመጠ ሲሆን የትኛዉ የፍርድ ቤት ደረጃ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ያሰቀመጠዉ ነገር በላመኖሩ በዚህ አንቀጽ ዉስጥ ተካቷል። ለምን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመረጠ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የመጀመሪያዉ መልስ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚሾሙ ዳኞች በልምድም የሁን በብስለት ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሻሉ በመሆናቸዉ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚወከል በመሆኑ ተደራሽነትን ግምት ዉስጥ በማስገባት ነዉ።
ከዚህ በተጨማሪ ማንኛዉም በጉዳዩ ላይ መብት ወይም ጥቅም ያለዉ ሰዉ ወይም ጉዳዩን ለማቅረብ በቂ ምክንያት ያለዉ ሰዉ መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን ለማስከበር ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ መብት እንዳለዉ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 11(4) ስር ተመላክቷል። አንድን መብት መጣስ የግድ መብቱ የተጣሰበት ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሌላ ሶስተኛ ሰዉ በቂ ምክንያቱን አቅርቦ ክስ ሊመሰረት እንሚችል ነዉ። በተለይም ፐብሊክ ኢንተረስት ሊቲጌሽን ባለመኖሩ አንዳንድ የሲቪክ መብቶች ሲጣሱ አቤት የሚልላቸዉ ማጣታቸዉ የነበረዉን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ ድንጋጌ ነዉ።
የሰብዓዊ መብት ይከበርልኝ አቤቱታዉ ከመደበኛዉ የክርክር ስረዓት ለየት ባለ ሁኔታ የሚስተናገድ መሆኑን የፍታብሄር ስነ-ስርዓት ህግ ስለ አጭር ሁኔታ በሚወሰኑ ክርክሮች ላይ ስለሚፈጸሙ ስነ-ስርዓት በሚል በተደነገገዉ መሰረት መሆን እንዳለበትም በንኡስ አንቀጽ 5 ስር ተካቷል። ይህ በተለይ ህገ-መንግስታዊ መብቶች ይከበርልኝ አቤቱታ በፍርድ ቤቶች በተቀላጠፈ እና በተፋጠነ መንገድ እንዲስተናገዱ መንገድን የሚከፍት ድንጋጌ ነዉ።
 

 1. ስለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች ስልጣንና ተግባር

   የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶችን ስልጣንና ተግባር በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 ከአንቀጽ 16 እስከ 18 የተደነገገ ሲሆን የእነዚህ አንቀጾች የወንድና ሴት ፆታ አገላለጽን ባገናዘበ መልኩ የሁለቱም ጾታ አገላለጽን በመጠቀም አንቀፆቹ ተሻሽለው ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
 በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀት 16 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ) ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት በአንቀጹ ላይ በተጠቀሰው መሠረት የፌዴራል ፍርድ ቤት ችሎቶች ሰብሳቢ ዳኞችን እና ሌሎች ዳኞችን እንደሚደለድሉ፣ ሥራ እንደሚሰጡ እና እንደሚያስተዳድሩ የተጠቀሰ ሲሆን በረቂቅ አዋጁ ላይ ከዚህም በተጨማሪ የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች ተጠሪ ዳኞችን እና ሰብሳቢ ዳኞችን እንደሚደለድሉ ፣ ሥራ እንደሚሰጡ እና እንደሚያስተዳድሩ በሚያመለክት መልኩ ንዑስ አንቀጽ ተሻሽሎ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
 በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ2(መ) የነበረው ንዑስ አንቀጽ ሌሎች ፅሁፎችም እንዲዘጋጁ ሊያደርጉ የሚችሉ መሆኑን የሚገልፅ ሀረግ ተጨምሮበት ተቀራራቢ ከሆነው ጋር ተጣምሮ ንዑስ አንቀጽ(2)(ቸ) ሆኖ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
 በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ(2)(ቸ) ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት የተከላካይ ጠበቆን ቢሮ እንደሚያደራጁ የተጠቀሰ ሲሆን በረቂቅ አዋጅ ላይ ከዚህ በተጨማሪ ስለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈፃፀም ተቋም እንዲሁም ለፌ/ፍ/ቤቶች የተሰጡ ተግባራትን ለማስፈፀም የሚያስችሉ የሥራ ክፍሎች እንዲደራጁ እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል፡፡
የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ(2)(ነ) አዲስ የገባ ንዑስ አንቀጽ ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት የፌዴራል ሸሪአ ፍርድ ቤቶች በተቋቋሙበት አዋጅ መሠረት ተግባራቸውን እንዲወጡ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡
በረቂቁ አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ(2)(ኘ) ላይ ደግሞ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኘሬዝዳንት በሕግ እና በረቂቅ አዋጁ ላይ የተጠቀሱትን ሌሎች ጉዳዩች እንዲፈፀሙ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ ሌሎቹ ለውጥ ያልተደረገባቸው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀፆች እንዲሁም አንቀጽ 17 እና 18 ባሉበት ሁኔታ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረገ ሲሆን አንቀጽ 18 ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
 

 1. ስለምድብ ችሎት ተጠሪ ዳኛ እና የችሎት ሰብሳቢ ዳኛ፡፡

  የፌዴራል ከፍተኛ እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተሞች ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ምድብ ችሎቶች አሏቸው፡፡ እነዚህን ምድብ ችሎቶች የሚያስተባብሩት የየምድቡ ተጠሪ ዳኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ምድብ ችሎቶች ችግር የሚያጋጥማቸው ባለጉዳዩች የፍርድ ቤቶቹ ኘሬዝዳንቶች ወይም ምክትል ኘሬዝዳንቶች ወደሚገኙበት ዋናው መሥሪያ ቤት በመጓዝ አንዳንድ አቤቱታዎችን ከማቅረብ ይልቅ እነዚህ የምድብ ችሎቱ ተጠሪ ዳኞች አቤቱታዎቹን ማስተናገድ የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ይህን በተመለከተ አንቀጽ 20 ተዘጋጅቶ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
 ሶስትና ከሶስት በላይ የሆኑ ዳኞች በሚያስችሉባቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ችሎቶች ውስጥ ሰብሳቢ ዳኛ ሆነው የሚሰሩ ዳኞች ተግባራቸው ምን መሆን እንዳለበት የሚጠቅሱ እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 ውስጥ ያልነበሩ ስለችሎት ሰብሳቢ ዳኛ እና ስለ ሥልጣንና ተግባራቸው የሚጠቅሱ አዳዲስ አንቀጽ 21 እና 22 በረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ አንቀጽ 21 ላይ ሰብሳቢ ዳኛ የችሎቱ ሥራ በሕግ መሠረት መካሄዱን እና በችሎቱ የሚወሰኑ መዝገቦች በሁሉም የችሎቱ ዳኞች ግንዛቤ የወሰደባቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም ሁሉም የችሎቱ ዳኞች በችሎቱ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በማዘጋጀት ተመጣጣኝ ተሳትፎ ማድረጋቸውን መከታተል ያለባቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ሰብሳቢ ዳኛው የተጠቀሱትን ተግባራት የችሎቱን ሌሎቹን ዳኞች የዳኝነት ነፃነት በማይጋፋ ሁኔታ መፈፀም እንዳለባቸውም ተጠቅሷል፡፡
 

 1. ስለፌዴራል ፍርድ ቤቶች አደረጃጀትና የዳኝነት ስራ አካሄድ

    የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አደረጃጀትና የዳኝነት ስራ አካሄድን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 ላይ ከአንቀጽ 23 እስከ 34 ድረስ የተጠቀሰ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ ላይ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው አዳዲስ አንቀጽ 20፣ 21 እና 22 ስለገባ ነባሮቹ አንቀፆቹ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ማሻሻያዎች ተደርገውባቸው እና የተራ ቁጥር ሽግሽግ ተደርጐባቸው ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
  የረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 23 ከቀድሞው አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 19 በተለየ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመንግሥት ሰራተኞች አስተዳደር ሕግ መሠረት ሳይሆን እራሱ የሚያስተዳድራቸው ዳይሬክተሮች፣ ሬጅስትራሮች ፣ የዳኞች ረዳቶች ፣የሕግ ምርምር ባለሙያዎች እና ሌሎች ሠራተኞች እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 454/1997 የተሻሻለው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 23 ስለፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ችሎቶች ብቻ ይገልፅ የነበረ ሲሆን የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 28 ሆኖ የገባው የተሻሻለው አንቀጽ ርዕሥ ግን የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ችሎቶች፣ ዳኞችና ሌሎች ሠራተኞችን በሚያካትት መልኩ ተስተካክሎ ረቂት አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
  ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ(1) ላይ የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ለሥራቸው አስፈላጊ የሆኑ ችሎቶች እንደሚኖሯቸው ተገልጿል፡፡ ይኸውም ከፍ ሲል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ(1) እንደተገለፀው የፌዴራል ከፍተኛ እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ለሥራቸው በሚያመቻቸው መሠረት የተለያዩ ችሎቶችን ማደራጀት በሚያስችላቸው መሠረት ንዑስ አንቀጹ ተቀርጿል፡፡ ሌላው በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ(2) ላይ በተሻሻለው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 ንዑስ አንቀጽ(2) ላይ ያልነበረ አዲስ ሃሣብ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይኸውም የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት አማካይነት የሚመደቡ እና ከኘሬዝዳንቱ በሚሰጥ ውክልና መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ኘሬዝዳንቶች ፣ ምክትል ኘሬዝዳንቶች እና የየምድብ ችሎቱ ተጠሪ ዳኞች የሚያስተዳድሯቸው ሬጅስትራሮች፣ የዳኞች ረዳቶች፣ የሕግ ምርምር ባለሙያዎች እና ሌሎች ሠራተኞች እንደሚኖሯቸው ተጠቅሷል፡፡ ዝርዝሩም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘጋጅቶ የፌዴራል ዳኞች  አስተዳደር ጉባኤ በሚያፅድቀው መመሪያ የሚወሰን መሆኑ ተመልክቷል፡፡
    የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ(2) ላይ የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ችሎቶች በአንድ ዳኛ እንደሚያስችሉ ተገልäÿል፡፡ ነገር ግን ይህ መሆኑ አንድ ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአንድ ዳኛ ታይቶ በአንድ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኛ ከፀና የመጨረሻ ውሳኔነት ውጤት ይኖረዋል፡፡ ይህ መሆኑ የተከራካሪ ወገኖችን መብት ስለሚጐዳ ንዑስ አንቀጹ ወጥቶ አዲስ በገባው የረቂቂ አዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ(3) ላይ የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ችሎቶች በሶስት ዳኞች እንደሚያስችሉና ከችሎቱ ዳኞች መካከል የሚመደብ ሰብሳቢ እንደሚኖራቸው ተገልäÿል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት በሶስት ዳኞች እንዲታዩ ከተወሰኑት ጉዳዮች መካከል ተለይተው የሚታወቁ ጉዳዮች በአንድ ዳኛ እንዲታዩ መመሪያ በማውጣት በፌዴራል በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሊያፀድቅ እንደሚችል ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ(4) ላይ ተጠቅሷል፡፡
   የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የማስቻያ ሥፍራ  በተመለከቱ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ(1)፣(2) እና የነበሩት ንዑስ አንቀፆች የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ(1)፣(2) እና (5) ሆነው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ (3) እና (4) ግን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 ላይ የተጠቀሱት አንቀፆች ተወስደው በንዑስ አንቀጽነት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 30/1995 ባደረገው ስብሰባ በአፋር ክልል፣ በቤንሻንጉል ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሶማሌ ክልል እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲደራጁ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሰረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 ወጥቷል፡፡ ነገር ግን የዚህ አዋጅ ይዘት በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ተጠቃልሎ መውጣቱ የተሻለ በመሆኑ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የአዋጅ ቁጥር 322/1995 አንቀጽ 2 እና አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ (3) ሆኖ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 322/1995 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (2) ላይ የተጠቀሰው ደግሞ የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ (4) ሆኖ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
 የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የሥራ ቋንቋ እና ፍ/ቤቶቹ በግልፅ ችሎት ማስቻል እንዳለባቸው በሚገልፅ መልኩ የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 25 እና 26 ማሻሻያ ተደርጎባቸውና አንቀጽ 30 እና 31 ሆነው ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ማሻሻያውም የችሎት ቋንቋ የሚለው ከእንግሊዝኛው አቻ ትርጉም ጋር የችሎት የሥራ ቋንቋ በሚለው የተተካ ሲሆን በአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ(2) የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤቶቹ ለሕዝብ ግለፅ በሆነ ችሎት ማስቻል እንዳለባቸው በአፅንኦት ተገልäÿል፡፡
 የዳኞች ከችሎት መነሳትን የሚጠቅሰው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 27 የፆታን አገላለፅ ባገናዘበ መልኩ ተሻሽሎ እና አንቀጽ 32 ሆኖ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ ስለሚቀርብ ማመልከቻ የሚጠቅሰው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 28 ደግሞ ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ የሚቀርበው ማመልከቻ አመልካች ዳኛው ከችሎት መነሳት የሚገባው “መስሎ የታየውን” ሳይሆን “ያለበትን” ምክንያት መጠቀስ ያለበት መሆኑን በሚገልፅ መልኩ ተሻሽሎና አንቀጽ 33 ፣34 እና አንቀጽ 35 ሆነው ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቂ ምክንያት ሳይኖር ዳኛ ከችሎት እንዲነሣ አላግባብ የሚያመለክት ተከራካሪ የሚከፈለው ቅጣት እስከ ብር 1,000 (አንድ ሺህ ብር) ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
9. የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በጀትና የሰው ሀብት አስተዳደር (አንቀጽ 35-39)
በረቂቅ አዋጁ የተመለከተው የዳኝነት ሥርዓት ከሚጠበቅበት የአገልግሎት ደረጃ አኳያ አስፈላጊው በጀትና የሠራተኞች አስተዳደር ሥርዓት ያስፈልገዋል፡፡ ከአንቀጽ 35 እስከ 39 የተደነገጉት አዲስ አንቀጾች ይህን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የዳኝነት ነፃነት ከሚረጋገጥባቸው ሁኔታዎች መካከል አንዱ የበጀት ዝግጅት፣ በጀት የሚፀድቅበት ሂደትና አፈፃፀም ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ያለው አሠራር የፍርድ ቤቶችን የሥራ አፈፃፀም ሊያውክ አይገባም፡፡
ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቂ የሆነ ጥቅል በጀት ስለመመደብ (አንቀጽ 39)
አንቀጽ 35(1) ለፍርድ ቤቶች ጥቅል የሆነ በጀት እንደሚመደብላቸው ይገልፃል፡፡ የጥቅል በጀት (lump sum budget) ምደባ አጠቃላይነት ባለው ሁኔታ የተፈቀዱ የወጭ አርዕስቶቸንና ክፍያዎችን ቢገልፅም፣ በዝርዝር አፈፃፀም ረገድና ተገቢ ሽግሽጎችን በሚመለከት በጀቱ ለተመደበለት አካል ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑ ለሥራ ቅልጥፍናና ውጤታማነት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በአንቀጽ 35(2) እንደተደነገገው፣ “ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚመደበው ጥቅል በጀት፣ በሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችል መሆን አለበት”፡፡
በጀቱ የዳኝነትን ሥራ በአግባቡና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን ያስችል ዘንድ አንቀጽ 39(2) አራት መሠረታዊ ሁኔታዎችን አመልክቷል፡፡ እነርሱም የሚመደበው በጀት፡-
- አንደኛ፣ በቂ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለዳኞችና ለአስተዳደር ሠራተኞች ለመክፈል፣ 
- ሁለተኛ፣ “አስፈላጊ የሆኑትን የሥራ ማከናወኛ መሣሪያዎቸንና አገልግሎቶችን ለመግዛት” ፣
- ሦስተኛ፣ “የካፒታል ዕቃዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት” ፣
- አራተኛ፣ “የጉባዔውንና የጽ/ቤቱን ሥራ በአግባቡ ለማስፈፀም”
የሚያስችል መሆን እንዳለበት የሚደነግጉ ናቸው፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በጀት ዝግጅት፣ መጽደቅ እና አፈፃፀም (አንቀጽ 36)
አንቀጽ 36 በጀት የሚዘጋጅበትንና ለተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብበትን አንዲሁም በጀቱ የሚፀድቅበትንና ከፀደቀ በኋላ ያለውን የበጀት አፈፃፀም የሚመለከት ነው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79(6) እንደተደነገገው “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን መንግሥት የዳኝነት አካል የሚያስተዳድርበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስወስናል፣ ሲፈቀድም በጀቱን ያስተዳድራል” ፡፡ ማናቸውም ሰነድ ለአንድ አካል ከመቅረቡ በፊት መዘጋጀት ስላለበት “አቅርቦ” የሚለው ቃል “ዝግጅትንና ማቅረብን” ይመለከታል፡፡ ስለሆነም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79(6) የበጀት ዝግጅትን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ በጀት መቅረቡን፣ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጀት ከተፈቀደ በኋላ የበጀቱን አስተዳደር የሚመለከት ነው፡፡
በአንቀጽ 36(4) መሠረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል መንግሥቱን የበጀት ዓመት (ከሐምሌ 1 እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ 30 ያለውን ጊዜ) የሚከተሉ ሲሆን፣ በአንቀጽ 36 ሥር፣ ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 4 የተደነገጉት ከበጀት ዝግጅት አንስቶ እስከ በጀት አፈፃፀም ሪፖርት ድረስ ያሉትን ሂደቶች የሚገልፁ ናቸው፡፡
- “በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79(6) መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን በጀት አዘጋጅቶ የማቅረብ ሀላፊነቱን የሚያመለክት ሲሆን “አዘጋጅቶ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በተቋም ደረጃ ማለትም ከሁሉም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሥራ ዕቅድና በጀት ተዘጋጅቶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እንደሚቀርብ ነዉ። በአንቀጽ 36(2) በተደነገገው መሠረት፣ “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ከሌሎች የፍርድ ቤት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎቸ ጋር በመሆን ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ የበጀት ጥያቄውን” የሚከላከል መሆኑ ነው፡፡  በአንቀጽ 36(3) እንደተደነገገው፣ “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ለፌዴራል ፍ/ቤቶች የፀደቀ በጀት፣ በበጀት አርዕስት እና ተመሳሳይ መለኪያዎች ሳይወሰን የውስጥ የበጀት ሽግሽግ መብታቸው ተጠብቆና በዕቅድ ላይ በመመሥረት፣ ፍርድ ቤቶች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች በነፃነት ከሥራ ላይ ያውሉታል፡፡” ይህ ድንጋጌ የሚያሳየው ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተፈቀደው ጥቅል በጀት በመርህ ደረጃ በተፈቀደው የበጀት አርዕስት መሠረት ተፈፃሚ እንደሚሆን፣ እንዳስፈላጊነቱም ፍርድ ቤቶች የበጀት ወጭ አርዕስት ለውጥ በማድረግ ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ጉዳዮች በጀቱን የመጠቀም ነፃነት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተፈቀደውን በጀት አጠቃቀም በሚመለከት በአንቀጽ 35(4) መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት እንዲያቀርብ የተደነገገው ነው፡፡
የሰው ሀብት (አንቀጽ 38)
ለዳኝነት ሥርዓቱ የሥራ ቅልጥፍናና ውጤታማነት የሰው ሀብት አስተዳደር ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአንቀጽ 38(1) መሠረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞቻቸውን “የመመልመል የመቅጠርና የማስተዳደር ነፃነት አላቸው” ፡፡ ይህን ተግባራቸውን ሲያከናውኑ፣ ማለትም፣ “ሠራተኞችን በሚመለምሉበት፣ በሚቀጥሩበትና በሚያስተዳድሩበት ወቅት ከአስፈፃሚው ወይንም በሥሩ ከሚገኙ ማናቸውም ተቋማት ጣልቃ ገብነት ነፃ” መሆናቸውን አንቀጽ 38(2) ያረጋግጣል፡፡
ይህን ማሳካት ይቻል ዘንድ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች “ምልመላ፣ ምደባ፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ ሥልጠና፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የጥቅማ ጥቅም ክፍያ” እና የዲሲፕሊን ጉዳይ የሚመራበትን ደንብ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲያዘጋጅና ይኸው ደንብ በዳኝነት አስተዳደር ጉባዔው እንዲፀድቅ አንቀጽ 38(3) ይደነግጋል፡፡ የሠራተኞች የእኩልነት መብት፣ በቅጥር ረገድ የሚደረገው ግልጽ ውድድርና ምዘና እንዲሁም ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በአንቀጽ 38(3) ተገልፀዋል፡፡ እነርሱም፡-
- “የሠራተኞች ቅጥር ከማንኛዉም ወገንተኝነት በፀዳ ሁኔታ መከናውን ያለበት መሆኑን” ፣ (አንቀጽ 38/3/ሀ)
- “ግልጽ በሆነ ማመልከቻና የውድድር ሥርዓት ላይ ተመሥርቶ” አዲስ ሠራተኞች ሊቀጠሩ እንደሚገባና፣ “ከትምህርት፣ ከልምድ፣ ከብቃት፣ ከመልካም ሥራ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ” ክፍት የሥራ ቦታ የሚጠይቀውን ልዩ ችሎታና ብቃት ተወዳዳሪዎች አሟልተው መገኘታቸው በምዘና ሊረጋገጥ እንደሚገባ፣ (አንቀጽ 38/3/ለ)
- “ብቃት ያላቸው የአስተዳደር ሠራተኞችን ለመቅጠርና ለመሳብ እንዲቻል በየጊዜው የሚከለስ በቂ የሆነ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ” ሊዘጋጅ እንደሚገባ (አንቀጽ 41/4/ሐ)
የሚገልፁ ናቸው፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞችን በሚመለከት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘጋጅቶ በዳኝነት አስተዳደር ጉባዔው የሚፀድቀው ደንብ ከላይ የተዘረዘሩን መረሆች ጨምሮ የሠራተኞችን አስተዳደር፣ የዲሲፕሊን ጉዳይ ወዘተ የሚዘረዘር ሲሆን የሚያስገኛቸው መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች የመንግሥት ሠራተኞች በሚተዳደሩበት አዋጅ ከተፈቀዱት ያነሱ ሊሆኑ እንደማይችሉ የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 38(4) ደንግጓል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤት ሠራተኞችን የሚመለከቱ ልዩ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ ከተደረጉም በኋላ በደንቦቹና በመመሪያዎቹ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች የመንግሥት ሠራተኞችን የሚመለከቱ ሕጎች ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፡፡

 1. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ

ስለ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ የሚጠቅሰው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 31 ጉባኤውን "የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ" ብሎ የሚጠቅስ ቢሆንም የጉባኤውን ስያሜ "የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ" መባሉ የተሻለ በመሆኑ የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 36 የጉባኤውን ስያሜ በተመለከተ በዚሁ መሠረት እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ ስለ ጉባኤው አባላት ጥንቅር የሚዘረዝረው የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ(1) በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ ላይ አባላት ከነበሩት በተጨማሪ በፌዴራል ከፍተኛ እና በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች የተወከሉ ሁለት ዳኞች ከእያንዳንዳቸዉ አንድ ወንድ አንድ ሴትየአዲስ አበባ እና የድሬድዋ ከተማ ፍርድ ቤቶች ኘሬዚዳንቶች  እንዲካተቱበት ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በንዑስ አንቀጽ(2) ላይ “ፍትህ ሚኒስቴር” የሚለው ሀረግ “ፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ” በሚለው ተተክቶ  እና የቃላት ማስተካከያ ተደርጐበት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን ንዑስ አንቀጽ(3) እንዳለ ረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ያልተጠቀሱ ዳኞች እና አግባብ ያላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ ማኀበራትን ፣ ድርጅቶችን ፣ ከፍተኛ የሕግ ትምህርት ተቋማት እና የሳይንስ ተቋሞችን የሚወክሉ ሰዎች ወይም ሌሎች ግለሰቦች በጉባዔው እንዲሳተፋ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊጋበዙ እንደሚችሉ እና ድምጽ የመስጠት መብት እንደማይኖራቸውም ጭምር ተገልጿል፡፡
   ጉባዔው የራሱን ፀሐፊ በመመደብ፣ ስራዉን ለማከናዎን የሚረዱ ኮሚቴወችን ማዋቀር፣ የራሱ ላይዘን ቢሮ እና ተጠሪዎች አስፈላጊ በሆኑ ፍርድ ቤቶች ማቋቋም እንደሚችል እንዲሁም የሥራ ባልሆኑ ቀናት በዓመት አንድ ጊዜ መሰብሰብ እነዳለበት የሚገልጽ ድንጋጌ ተካቷል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተጨማሪ ስብሰባም መጥራት ይችላል ። ከጉባዔው   አባላት ሁለት ሶስተኛው ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡ ውሣኔ በድምጽ ብልጫ ይተላለፋል፡፡ ድምጽ እኩል ለእኩል በተከፈለ ጊዜ የጉባዔው ሰብሳቢ ወሳኝ ድምጽ ይኖራቸዋል።

 1. የፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና የጉዳዮች አስተዳደር

የፍርድ ቤት መር አስማሚነት
የፌደራል ፍርድ ቤቶች በተለመደዉ የአሰራር ዘየ እና ስርዓት የመስራት ልማዳቸዉን ከቀጠሉ ችግሮቻቸዉን ሳይፈቱ ህብረተሰቡንም ማስደሰት ሰይችሉ እንደሚቀጥሉ እሙን ነዉ። ያደጉ ሀገሮች የደረሱባቸዉ የዳኝነት ስርዓት ማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ጥረት ማድረጋቸዉ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አንዱ የለዉጥ አቅጣጫ ነዉ። ለዚህ ደግሞ የሀግ ማእቀፎችን በመፈተሽ አዳዲስ የማሻሻያ ሃሳቦችን ማካተት አስፈለጊ ነዉ። ለዚህም የፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ስራዎችን ዉጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ዉስጥ ማካተት ተገቢ ነዉ።
የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማለት መደበኛዉን የክርክር ሂደት መከተል ሳያስፈልግ በማስማማት ሙያ በተካኑ ኤክስፐርቶች እገዛ ተደርጎላቸዉ ግራ ቀኙ ተስማምተዉ ጉዳያቸዉን በአጭሩ እልባት እንዲያገኝ የሚደረግበት ስርዓት ነዉ። ምንም እንኳን ባለጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ከመምጣታቸዉ በፊት አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለዉ ግንዛቤ እንዳለ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ደግሞ ባለጉዳዮቹ እንዲስማሙ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ወደ ክርክር ሂደት ሳይገቡ እንዲጨርሱ ማድረግ የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። እንደሚታወቀዉ ፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሚሰጠዉ አገልግሎት አስማሚዎች በማስማማት ሙያ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የመስማሚያ ቢሮዎችን ማመቻቸት፣ ፎረሞችን አዘጋጅቶ የስምምነት አንቀጾችን አንዲጸድቁ ማድረግ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ሲሆን በፌደራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
 በረቂቅ አዋጁ እንደተመላከተዉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያወጣዉ መመሪያ የሚለዩ የፍታብሄር ጉዳዮች ሁሉ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማለፍ እንዳለባቸዉ ይገልጻል። ይህ ማለት አንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ከመስተናገዱ ቀደም ብሎ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል እልባት እንዲያገኝ እድል ያገኛል።  መስማማት ግዴታ ሳይሆን በስርዓቱ ማለፍ ግን እንደ ግዴታ ይሆናል ማለት ነዉ። ስለሆነም የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 44 በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ የፍታብሄር ጉዳዮች ዉስጥ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያወጣዉ መመሪያ የሚወሰኑ ጉዳዮችበፍርድ ቤቶቹ በሚቋቋም የፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል እንዲያልፉ ይደረጋል በማለት ደንግጓል።
ተከራካሪ ወገኖች በፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል ጉዳያቸዉን በስምምነት ካልጨረሱ ይህንኑ የሚገልጽ በአስማሚዎቹ የተፈረመ ደብዳቤ ለፍርድ ቤት በማቅረብ የፍርድ ሂደቱ እንዲቀጥል ይደረጋል። የተስማሙ ከሆነ የስምምነቱ ሁኔታዎች በአስማሚዉ በግልጽ ተለይተዉ ከቀረቡ እና ተከራካሪዎቹ ከፈረሙበት ቡሃላ አስማሚዉ ይህን ሰነድ ለፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ያደርጋል። ሰነዱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ሰምምነቱ ለህግ እና ለሞራል ተቃራኒ አለመሆኑ ከተረጋገጠ ቡሃላ እንዲጸድቅ ያደረጋል። የጸደቀዉ የስምምነት ሰነድ እንደማንኛዉም የፍርድ ቤት ዉሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል። በአንደኛዉ ተከራካሪ ወገን ያለመቅረብ ምክንያት የመስማማት ሂደቱ ካልተሳካ አስማሚዉ ይህንኑ በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት ያደርጋል። መደበኛዉ የፍርድ ሂደትም ይቀጥላል። ይሁንና በፍርድ ቤት መር አስማሚነትም ይሁን በሌላ አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ ግራ ቀኙ ከተስማሙ በደንቡ መሰረት ወጭዎች ተቀንሰዉ የከፈሉት የዳኝነት ክፍያ ተመላሽ ይደረግላቸዋል። የዚህን ድንጋጌ ለማስፈጸም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዝርዝር መመሪያ ያወጣል።
በፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሚደረገዉ ማንኛዉም ሂደት በእኩልነት እና በባለጉዳዮቹን ሙሉ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።በማስማማት ሂደቱ ተከራካሪ ወገኖች የሚሰጡት የእመነት ቃሎች ወይም ማንኛዉም ንግግሮች ለፍርድ ቤት በማስረጃነት አይቀርቡም። ለዚህም አስማሚዉ ማረጋገጫ ይሰጣል። በፍርድ ቤት አስማሚነት በኩል የሚደረጉ ማናቸዉም የሃሳብ ልዉዉጦች ሚስጥራዊነት የተጠበቀ ነዉ።
የአስማሚነት ስልጠና ወስደዉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያወጣዉን ምዘና ያለፉ ቢያንስ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸዉ እና ከአምስት አመት ያላነሰ ጊዜ በህግ ሙያ ያገለገሉ አስማሚ ሆነዉ ሊመረጡ ከመቻላቸዉም በላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያዘጋጀዉ የአስማሚዎች ሮስተር መዝገብ ዉስጥ እንዲካተቱ ይደረጋሉ። ይህ በግልጽ እንደሚያሳየዉ ብቁ የሆነ አስማሚ የሚገባበት የማስማማት ስራ ስኬታማነቱ አያጠራጥርም። ማስማማት ልዩ ሙያ እንደመሆኑ መጠን የስነ-ልቦና፣ ህግ፣ ስነ-ምግባር እና ብስለትን የሚፈልግ ነዉ። ስለሆነም በቂ ስልጠና ያገኘ እና ተመዝኖ ብቁ የሆነ ብቻ አስማሚ ሊሆን እንደሚገባ እሙን ነዉ። የባለ ጉዳዮችንም በማን መስማማት እንዳለባቸዉ እንዲለዩ ለማድረግ የብቁ አስማሚዎችን ስም ዝርዝር የያዘ ሮሰተር መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነዉ። አንዳንድ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቋሚ የሆኑ ወይም በጊዜያዊነት ብቁ አስማሚዎችን ሊቀጥር ይችላል።
  ክፍያን በሚመለከት አስማሚዎችም ይሁን ተስማሚዎች የሚፍሏቸዉ የክፍያ አይነቶች ይኖራሉ። አሳሚዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያወጣዉ መመሪያ የሚወሰን ለአስተዳደራዊ ጉዳይ እና አመታዊ ክፍያ ይከፍላሉ።  በማስማመቱ ሂደት ዉስጥ የሚያልፉ ባለጉዳዮች ለፍርድ ቤት መር አስማሚነት ተገቢዉን ክፍያ ይፈጽማሉ። የክፍያዉ አይነት በመመሪያ የሚወሰን ሆኖ የፍርድ ቤት ክፍያ ከፍለዉ ከሆነ ግን ተቀናሽ ይደረግላቸዋል። አስማሚዎች በባለጉዳዮች ተመርጠዉ የማስማማት አገልግሎት ከሰጡ ተገቢዉ ክፍያ ይከፈላቸዋል። አስማሚ ሆኖ የተመረጠ ሰዉ ተመጣጣኝ የአግልግሎት ክፍያ ካላገኘ ድጋሚ ጊዜዉን የሚያጠፋበት ምክንያት ላይኖረዉ ነዉ። የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ቀጣይነት እንዲኖረዉ ከተፈለገ የግድ አስማሚዎች ክፍያ ሊያገኙ ይገባል በበጎ ፈቃድ የሚሰራ አይሆንም። እዚህ ላይ ሊታሰብበት የሚገባዉ ጉዳይ አስማሚዎች የሚከፈላቸዉ ዝቅተኛ መጠን እና ባለጉዳዮች መክፈል የሚገባቸዉ ያገልግሎት ክፍያ ተመጣጣኝ እንዲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመሪያ በማዉጣት ሊወስን ይገባል።
የጉዳዮች ፍሰት
የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡላቸዉን ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ወይም የሚጠናቀቁበትን የጊዜ ሰሌዳ ገደብ ባለማስቀመጣቸዉ አንድ ጉዳይ መች ተጀምሮ መች እንደሚያልቅ ግልጽ የሆነ የጊዜ መጠን የላቸዉም። በዚህም ምክንያት የፍርድ ቤት ጉዳይ ማለቂያ ጊዜ ተገማች ያልሆነ እና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 47 ስር የጊዜ ሰሌዳ እንዲቀመጥ የህግ ማእቀፍ በመስጠት የፍትህ አሰጣጥ ስርዓቱ የተሳለጠ እና ጥራቱ የሚረጋገጥበት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስችል አንቀጽ ተካቷል። ለዚህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለማስፈጸም ዝርዝር መመሪያ ያወጣል።
የፌደራል ፍርድ ቤቶች በማንኛዉም የፍርድ ቤት ደረጃ የሚቀርቡ የፍታብሄር ወይም የወንጀል ጉዳይ ክርክሮች አዳዲስ የመረጃ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ዳጂታል ወይም አዉቶሜትድ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ ስርዓት ሊዘረጉ እንደሚችሉ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል። ስለሆነም በቀጣይ ጊዜ ባለጉዳዮች ዶሴ ተሸክመዉ ፍርድ ቤት ከመምጣት ይልቅ የቴክኖሎጅ ዉጤቶችን በመጠቀም የክስ ዝርዝርም ይሑን ማንኛዉም አቤቱታ በዲጂታል ሰቶር ወይም በሶፍት ኮፒ ለፍርድ ቤቱ በማስገባት በዘመነ መንገድ እንዲስተናገዱ ለማስቻል ነዉ። ለዚህም ተከራካሪ ወገኖች በተዘረጋዉ ስርኣት መሰረት ክርክሮቻቸዉን የማካሄድ ግዴታ እንዳለባቸዉ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል።ለዚህም ዝርዝሩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመሪያ መዉጣት እንዳለበት ግልጽ ነዉ።

 1. ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን በተመለከተ

  በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 5ዐ ላይ የገባው ንዑስ አንቀጽ (1) አዲስ ሲሆን ይዘቱም በማንኛውም የፌዴራል ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ እና ትዕዛዝ በህገ መንግሥቱ ላይ በተጠቀሰ ፍርድ ቤት ወይም ፍርድ ሰጪ አካል እስካልተሻረ ድረስ የፀና ሆኖ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸዉን ዉሳኔዎች ወይ ተእዛዞች በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ በማንኛዉም ክልል ዉስጥ የሚገኝ የመንግስት አካል፣ተቋም ወይም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ወይም ማንኛዉም ሰው ውሳኔዎቹን ወይም ትእዛዞቹን የመፈጸም እና የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸዉ በረቂቅ አዋጁ መካተቱ የፍርድ ቤት ዉሳኔ ተፈጻሚ የሚሆንበትን የህግ ሽፋን በመያዙ ከበፊቱ የተሻለ ነዉ። በተለይም ማንኛዉም ሰዉ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ የተጣለበትን ግዴታ የማይወጣ ከሆነ በዚህ አዋጅና አግባብ ባለው ሌላ ህግ ተጠያቂ ይሆናል። የፍርድ ቤት ወይም የዳኞችን በነጻነት መስራት የሚጋፋ ወይም በዳኞች ላይ ተጽእኖ የሚያደርግ ወይም ለማድረግ የሞከረ ማንኛው ሰዉ በሌላ ህግ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ከሦስት ወር እሥራት ባላነሰ ከሁለት አመት ባላበለጠ ጽኑ እስራት ይቀጣል። የፍርድ ቤትን ትእዛዝ ወይም ዉሳኔ የማይፈጽም ወይም ለመፈጸም መሰናክል የሚፈጥር ወይም ሲጠየቅ ለመፈጻም ተባባሪ የማይሆን ማንኛዉም ሰዉ በሌላ ህግ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ከሁለት አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ ገንዘብ ይቀጣል። ይህ የቅጣት ድንጋጌ አዋጁ ጥርስ የሌለዉ አንበሳ እንዳይሆን ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነዉ።
 አንድን ጉዳይ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የክልል ወይም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወይም የአዲስ አበባ ወይም የድሬዳዋ ከተሞች ሥልጣናችን ነው ብለው የያዙት ወይም ሥልጣናችን አይደለም ብለው የመለሱት እንደሆነ ስልጣኑን በሚመለከት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገቢውን ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት መካተቱም የስልጣን ግጭቶች ሲኖሩ ማን እንደሚወስን የሚያሳይ ነዉ፡፡   በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 55 ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988ን ያሻሻሉ ቁጥራቸው 138/1991 ፣ 254/1993 ፣ 321/1995 እና 454/1997 እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 የተሻሩ መሆኑ የተጠቀሱ ሲሆን ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ከመሆኑ በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በተጀመሩበት ፍርድ ቤት እና በነባሩ ህግ መስተናገዳቸዉ ይቀጥላል። በረቂቅ አዋጁ ከአንቀጽ 11 እስከ አንቀጽ 15 ድረስ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑት አዋጁ ከጸደቀ ከ6 ወር ቡሃላ መሆኑ ፍርድ ቤቶቹ በቂ ዝግጅት ካደረጉ ቡሃላ የስር-ነገር ስልጣን ለዉጡ በመኖሩ ለሚፈጠር የሰዉ ሀይልም ይሁን የመሰረተ ልማት ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ነዉ።
የአስተዳደር ሠራቶኞች መተዳደሪያ ደንብ እስከሚወጣ ድረስ የሠራተኞች ቅጥር፣ ምደባ፣ ዝውውር፣ እድገትና አስተዳደር የዚህን አዋጅ መርሆዎች ሳይቃረን ቀድሞ ሲሰራበት በነበረው ሕግ መሰረት እንዲቀጥል የሚል አንቀጽም መካተቱ እንዲሁ የህግ ክፍተት እንዳይኖር ለማድረግ ነዉ፡፡