92826 criminal law/ corruption/ breach of official duty

የወንጀል ህጉ አንቀጽ 420 ድንጋጌ ተፈፃሚነት የሚኖረው የመወሰን ስልጣን በሌላቸው እና የሙያ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው በመንግስት ስራ ተመድበው ባሉበት ሁኔታ በመንግስት ንብረት ላይ የሥራ ኃላፊነት ወይም ግዴታቸውን ባልተወጡት ላይ ስለመሆኑ፣

 

የወ/ህ/አንቀጽ 420/1/

የሰ//.92826 ጥር 05 ቀን 2007 ዓ/ም

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- የደ/ብ/ብ/ሕ/ብ/ክልላዊ መንግስት ዐቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡-  ወ/ሮ ፀሐይ መጫሎ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ጉዳይ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች የክልሉን የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን በመወከል በአሁኗ ተጠሪና በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ በካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡የአመልካች ክስ ይዘትም፡- ተጠሪና በስር ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ ኢምቶ ወ/ማሪያም አቶ ዳዊት ደስታ የተባሉት ግለሰቦች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ በዬቻ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት ውስጥ የስር 1ኛ ተከሳሸ የነበሩት አቶ ኢምቶ ወ/ማሪያም ዋና ገንዘብ ያዥ፣የአሁኗ ተጠሪ ደግሞ የክፍያ ኦፊሰር፣ቼክ አዘጋጅና ፈራሚ፣የስር ሶስተኛ ተከሳሽ የነበሩትና በብይን በነፃ የተሰናበቱት አቶ ዳዊት ደስታ ደግሞ የክፍያ ሰራተኛ እና ቼክ ፈራሚ በመሆን እየሰሩ የአሁኗ ተጠሪ ከኢትዩጵያ ንግድ ባንክ ቦንጋ ቅርንጫፍ ከሂሳብ ቁጥር GOV 787 ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ) ብር ወጪ ተደርጎ ለስር አንደኛ ተከሳሽ እንዲከፈል ቁጥሩ 0741998 የሆነውን ቼክ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም አዘጋጅተው ከስር ሶስተኛ ተከሳሽ ጋር ፈርማ በኃላፊ ሳይታዘዙ በመስጠታቸውና የስር 1ኛ ተከሳሽም ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ) ከተጠቃሹ ባንክ አውጥቶ ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1(ሀ)) እና 676(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በግብረአበርነት ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ነው፡፡ ተጠሪ ክሱን ክደው የተከራከሩ ሲሆን አቃቤ ሕግ በበኩሉ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎቸን አቅርቦ ካሰማ በሁዋላ የተጠሪ የመከላከል መብታቸው ተጠብቆላቸው የመከላከያ ምስክሮችን አሰምተዋል፡፡የሥር ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ በመከላከያ ምስክሮች የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ሊያስተባብሉ አልቻሉም በሚል ምክንያት ክስ በቀረበባቸው ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ አድርጓል፡፡ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት በመቀበልና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 መሰረት አስልቶ በአስራ  አራት


አመት ፅኑ እስራት እና በብር 7000.00(ሰባት ሺህ) እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኛቸውን ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ተጠሪ የሰበር አቤቱታቸውን ለክልል ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግን ግራ ቀኙ እንዲከራከሩ ተደርጎ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ የወንጀል ድርጊት መፈፀማቸው መረጋገጡን ተቀብሎ አድራጎቱ የሚሸፈንበትን ድንጋጌ በተመለከተ አመልካች ተጠሪ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው ስለማዋላቸው ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ስለማዋላቸው በማስረጃ አልተረጋገጠም በሚል ምክንያት በዓቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ የተጠቀሰውን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 113 (2) መሰረት ወደ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 420(1) ለውጦ በዚሁ ድንጋጌ ስር የሙያ ግዴታ የመጣስ አድራጎት ፈጽመዋል በማለት ወስኗል፡፡ቅጣቱንም በተመለከተም በዚሁ በተለወጠው ድንጋጌ ስር በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ደረጃ ላልወጣላቸው የወንጀል ድንጋጌዎች ደረጃ የሚወጣበትን አግባብ ዘርዝሮና ከግራ ቀኙ የቅጣት አስተያየት ጋር በማገናዘብ  መመርመሩን ገልፆ ተጠሪ በአንድ አመት ቀላል እስራት እና በብር 5000.00 (አምስት ሺህ) ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-የተጠሪ አድራጎት ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል ሁኖ እያለ የስራ ኃላፊነትን ባለመወጣት የተፈፀመ ነው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም የተጠሪ አድራጎት የሚሸፈነው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 676(1) ሳይሆን በአንቀጽ 420(1) ስር ነው ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸውም ቀርበውም በፅሑፍ በሰጡት መልስ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ሕጋዊ ነው የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው ውሳኔው ሊፀና ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ  ችሎትም ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

 

በመሠረቱ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቋሙት  ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 414/1996 የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 (2) በግልፅ ደንግጓል፡፡እንግዲህ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ብሎ ለመወሰን ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተጣምረው መገኘት የግድ ይላል፡፡ሕጋዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት አለው ተብሎ የተጠቀሰውን ድንጋጌ ለማቋቋም ሙሉ በሙሉ መሟላት ያለባቸውን ነጥቦች የሚመለከት ሲሆን ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ እንደየቅደምተከተላቸው ከድርጊት ማድረግ ወይም አለማድረግና ከሐሳብ ክፍል ጋር በሕጉ አንቀፅ 24፣57 እና 58 ድንጋጌዎች ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎችን የሚመለከቱ መሆኑ ይታመናል፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመጣ ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉት በመንግስት መስሪያ ቤት በክፍያ ኦፊሰርነት፣ቼክ አዘጋጅነትና ፈራሚነት የስራ መደብ ላይ ተመድበው ሲሰሩ በቀን 30/10/2002 ዓ/ም ቁጥሩ 0741998 በሆነ ቼክ ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ) ለስር አንደኛ ተከሳሽ እንዲከፈል አዘጋጅተው በቼኩ ጉማጅና በባንክ ክፍያ ደረሰኝ ላይ ሳያስፈርሙ ሰጥተው የስር አንደኛ ተከሳሽ ከኢትዩጵያ ንግድ ባንክ ቦንጋ ቅርንጫፍ ከሂሳብ ቁጥር GOV 787 ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ) ብር ወጪ አድርጎ ለግል ጥቅሙ እንዲያውል  አድርገዋል፣ተጠሪ


ይህንኑ ያደርጉትም ያዘዛቸው ኃላፊ ሳይኖር መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ተጋግጧል በሚሉ ምክንያቶች መሆኑን ከስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ ተገንዝበናል፡፡ከክርክሩ አመጣጥና ከስር ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ይዘት አንጻር በዚህ ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ የተጠሪ አድራጎት የሚሸፈነው በየትኛው ድንጋጌ ስር ነው? የሚለው ነው፡፡

 

ተጠሪ በአመልካች የተከሰሱትና በስር ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉት የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 676/1/ የተመለከተውን በመተላለፍ ከመንግስት የሂሳብ ቁጥር ብር 100,000.00 ለሌላ ሰው ጥቅም እንዲውል በማድረጋቸው ከባድ የእምነት ማጉደልና የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ተብሎ ነው፡፡የወንጀል ሕጉ 676 በወንጀል ሕግ 675 የሚፈፀመውን የእምነት ማጉደል ወንጀል የሚከብ ድበትን ሁኔታ የሚዘረዝር ነው፡፡የድንጋጌው መሰረታዊ ማቋቋሚያ ነጥቦች በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675 ስር የተመለከቱት የእምነት ማጉደል ወንጀል ማቋቋሚያ ሁኔታዎች ስለመሆናቸው የሁለቱ ድንጋጌዎች ይዘት ያስገነዝባል፡፡ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል የሚሆነው ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ ወይም የመንግስት ሰራተኛ ያልሆኑት ሰዎች በመንግስት ንብረት ላይ የእምነት ማጉደል ተግባሩን መፈፀማቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡በወንጀል ሕጉ 675 ንዑስ አንቀጽ 3 ተከሣሹ ሲጠየቅ በእምነት ወይም ባደራ የተሰጠውን ዕቃ ወይም ጥሬ ገንዘብ ለመመለስ ወይም ለመክፈል ወይም ዕቃው ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ወይም ለተገቢው አገልግሎት ያዋለው መሆኑን ለማስረዳት ካልቻለ ንብረቱን ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ጥቅም የማዋል ሀሳብ እንዳለው የሚቆጠር መሆኑን በግልፅ ደንግጓል፡፡ይህ የህግ ግምት የሚስተባበለው ደግሞ በተከሳሹ ነው፡፡የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪን ተጠያቂ ያደረጋቸው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 420(1) ስር ነው፡፡በዚህ ድንጋጌ የወንጀል ተጠያቂነት የሚመጣው ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ የሥራ ግዴታ ተግባሩን በአግባቡ ሳይፈጽም በመቅረቱ በመንግስት፣በህብረተሰብ ወይም በግለሰብ ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሶ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 420 ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚኖረው የመወሰን ሥልጣን የሌላቸውና የሙያ ግልጋሎት የመስጠት ኃላፊነት ባለባቸው ሰዎች ነው፡፡ስለሆነም በአንቀጽ 420 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መሰረት አንድን ሰው ተጠያቂ ለማድረግ የሙያ ተግባሩንና ሥራው በአግባቡና በጥንቃቄ ባለመፈፀሙ ምክንያት  በመንግስት ላይ ጉዳት መደረሱ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡

ወደተያዘው ጉደይ ስንመለስ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የተጠሪ አድራጎት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 420(1) ስር የሚሸፈን ነው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው ተጠሪ አድራጎቱን የፈፀሙት ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ለግል ጥቅሙ ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ለማዋል በማሰብ መሆኑን በማስረጃ አልተረጋገጠም በሚል አቢይ ምክንያት ነው፡፡በእርግጥ ተጠሪ የተከሰሱት በከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል መሆኑ ሲታይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 676(1) የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675 መሰረታዊ የወንጀል ማቋቋሚያ የያዘ በመሆኑ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675(3) በተመለከተው የሕግ ግምት መሰረት ተከሣሹ ሲጠየቅ በእምነት ወይም ባደራ የተሰጠውን ዕቃ ወይም ጥሬ ገንዘብ ለመመለስ ወይም ለመክፈል ወይም ዕቃው ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ወይም ለተገቢው አገልግሎት ያዋለው መሆኑን ለማስረዳት ካልቻለ ንብረቱን ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ጥቅም የማዋል ሀሳብ እንዳለው የሚቆጠር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግን ተጠሪ የክፍያ ኦፊሰር፣ቼክ አዘጋጅና ፈራሚ መሆናቸው እንጂ በመሰረታዊ የስራ ሂደት መሰረት በጉርዱ ላይ ለመመዝገብ የስራ ሂደቱን አስተባባሪ ትዕዛዝ መጠበቅ የግድ የሚላቸው መሆኑን የክርክሩ ሂደት ማስገንዘቡ ሲታይ ተጠሪ ብቻቸውን የመወሰን ሥልጣን የሌላቸውና የሙያ ግልጋሎት የመስጠት ኃላፊነት ብቻ የነበራቸው ናቸው  ለማለት  የሚያስችል  ሁኖ  አግኝተናል፡፡በስራ  መደባቸው ተጠሪ  ብቻቸውን የመወሰን


ስልጣን ሳይኖራቸው ባልተገባ መንገድ ቼኩን አዘጋጅተውና ፈርመው ለስር  1ኛ ተከሳሽ በመስጠት ከመንግስት የባንክ ሂሳብ ውስጥ ብር 100,000.00 ወጪ ሁኖ ለስር 1ኛ ተከሳሽ የግል ጥቅም እንዲውል ማድረጋቸው በመንግስት ሰራ ተመድበው በመስራት ላይ ባሉበት ሁኔታ በመንግስት ንብረት ላይ የስራ ኃላፊነት ወይም ግዴታቸውን ያለመወጣታቸውን የሚያሳይ ሁኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 420(1) የተፈፃሚነት አድማሱን ከተጠሪ የስራ ኃላፊነት ዝርዝር ይዘት እና በወቅቱ  ከነባራቸው  ተሳትፎ ጋር በማዛመድ የተጠሪ አድራጎት የሥራ ኃላፊነትን ባለመወጣት የሚፈፀም ወንጀል ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስላላገኘን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሣኔ

 

1. በደ/ብ/ብ/ሕ/ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር  00723 ሐምሌ 02 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2)(ለ-2)) መሰረት ጸንቷል፡፡

2.  የተጠሪ አድራጎት የሚሸፈነው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 420(1) ስር ነው መባሉ  በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 


 

መ/ተ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡