አንድነት በሽብር ስም የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀረበ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጻፈው ደብዳቤ፣ በሽብር ስም እየታሰሩ ያሉ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸውና ከእስር እንዲፈቱ ጠየቀ፡፡ የአንድነት ፓርቲ ወቅታዊ ፕሬዚዳንት በሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፊርማ መስከረም 15 ቀን 2004 ዓ.ም. የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ በሽብርተኝነት ስም የታሰሩ አባሎቹና ሌሎች ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸውና ከእስር እንዲፈቱ ይጠይቃል፡፡



ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም የፓርቲውን ጥያቄ በቀናነት ተመልከተውና ከሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲመለከቱት ደብዳቤው ጠይቋል፡፡ የአንድነት ደብዳቤ በተለይ ሰባት ጉዳዮችን መንግሥት እንዲያጤንና እንዲያስተካክል አጽንኦት በመስጠት ይጠይቃል፡፡ ከነዚህም መካከል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ ሁለት በተደነገገው መሠረት፣ የዜጎች የግል ሕይወት መከበርና መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በተለይም ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው ደብዳቤዎች፣ የስልክ ልውውጦች፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎች የሚደረጉ የመልዕክት ልውውጦች መደፈር እንደሌለባቸው በመግለጽ እንዲከበሩ ይጠይቃል፡፡

‹‹ሕዝብን አፍኖ ለመግዛት ታስቦ የተዘጋጀው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከበርካታ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሻሻል፤›› በማለት አንድነት ይጠይቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸውና ከሐኪሞቻቸው ብሎም ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና የመጎብኘት መብታቸው እንዲከበርም አንድነት ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ እንዳስታወቀው፣ 78 ሰዎች በሽብርተኝት ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ናትናኤል መኮንንና አቶ አሳምነው ብርሃኑ እንዲሁም የመድረክ አባል ድርጅት ከሆኑት መካከል የኦፊዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦሕኮ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ የመኢዴፓ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ይገኙበታል፡፡ ‹‹ከፓርቲው አባላት በተጨማሪ በጋዜጠኝነታቸው የሚታወቁት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ የታሰሩ ጋዜጠኞችም እንዲፈቱ፤›› ሲል አንድነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቋል፡፡

የአንድነት ደብዳቤ በግልባጭ ለፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስና ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበርን ጨምሮ ለስምንት ተቋማት ተልኳል፡፡