105921 Labor dispute Unlawful termination of contract of employment

Labor dispute

Unlawful termination of contract of employment

አንድ አሠሪ ሠራተኛው ህጋዊ የመብት ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት የስራ ውሉን ማቋረጥ ህገወጥ ተግባር ስለመሆኑ 

 

አዋጅ ቁ.377/96 አንቀፅ 26(2)(ሐ)

የሰ//. 105921

 ቀን 14/07/2007 /

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሱልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- ፒተርድስ ፕሮዳክስት ማንፋክቸሪንግ (.) አልቀረቡም

ተጠሪች፡- 1. / ይፍቱስራ ነጋሽ

  2. / ገነት ወንድሙ

ጠበቃ ኤሊያስ አበበ ቀረቡ

ጉዳዩን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተጠሪ አንደኛ ከሳሽ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ያልሆነችው /ሪት መድሀኒት ሙቃ ሁለተኛ ከሳሽ ሁለተኛ ተጠሪ ሶስተኛ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ 

የክርክሩ መነሻ ተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ ነው፡፡ ከሳሾች ተከሳሽን ለምንድን ነው ለእኛ የቦነስ

ክፍያ የማይከፈለን በማለት በእረፍት ሰዓት በመጠየቃችን ከስራ አግዶ አቆይቶ ሚያዝያ 2 ቀን 2005 / በተፃፈ ደብዳቤ ከህግ ውጭ ያሰናበተን ስለሆነ የካሳ ክፍያ የማሰጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ክፍያ የዘገየበት ክፍያና ወጭና ኪሳራ እንዲከፍል ይወስንልን በማለት ክስ አቅርበዋል፡፡ አመልካች በስር ፍርድ ቤት ተከሳሽ ሆኖ ቀርቦ ከሳሾች ህገ ወጥ የስራ አድማ እንዲያደርጉ ሌሎች ሠራተኞችን በማስተባበርና በመቀሰቀስ የአድማ ስራ በመሆንና ረብሻና ሁከት የመፍጠር ሙከራ ማድረጋቸው ተረጋግጦ ከስራ የተሰናበቱ በመሆኑ ስንብቱ ህግን መሰረት ያደረገ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡

2.    የስር ፍርድ ቤት በግራ ቀኙ በኩል ያቀረቡትን ምስክሮች ከሰማ በኃላ ተከሳሽ ከሳሾችን ከስራ ያስናበታቸው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1() መሰረት በመሆኑ ስንብቱ ህግን መሰረት ያደረገ ነው በማለት የከሳሾችን ክስ ውድቅ አድርጎታል፡፡ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ተጠሪዎች ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ግራ ቀኙ በስር ፍርድ ቤት አቅርበው የሰማቸውን ምስክሮች ቃል በሰፊው ከዘረዘርና ከመርመር በኃላ አመልካች የቦነስ ክፍያ የማይከፈል መሆኑን በማስታወቂያ በመግለጽ ሰራተኞች ለምን አይከፈለንም የሚል ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑን አመልካች ሰራተኞችን በሁለት ከፍሎ ማነጋገር እንደጀመርና ይግባኝ ባዮች (ተጠሪዎች) መብታችን ይከበር በማለት መግለፃቸውን አመልካች ይህንን በመናገራቸው ምክንያት አድማ ቀስቅሰዋል በማለት ይግባኝ ባዮችን (ተጠሪዎችን) ከስራ ያገደና ያስናበታቸው መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠው ፍሬ ጉዳይ እንደሆነ ገልፆና አንደኛ ይግባኝ ባይ (አንደኛ ተጠሪ) ዘግይተው ወደስራ የገባች መሆኑና እሷ ስራ ከመግባቷ በፊት ሌሎች ሰራተኞች ቦነስ ለምን አይከፈለንም የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን በአመልካች (መልስ ሰጭ) ምስክር የተረጋገጠ መሆኑን በውሳኔው አስፍሮ በዕለቱ ይግባኝ ባዮች የተናገሩት ንግግር የመብት ጥያቄ እንጅ ህገ ወጥ የስራ ማቆም አድማ ቅስቅሳ አይደለም፡፡ ይግባኝ ባዮች ረብሻና ሁከት የመፍጠር ተግባር አልፈፀሙም በማለት ስንብቱ ህገ ወጥ ስለሆነ መልስ ሰጭ (አመልካች) ለይግባኝ ባዮች (ለተጠሪዎች) የስራ ስንብት ክፍያ የካሳ ክፍያና የማስጠንቀቂያ ክፍያ ይክፈል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

3.    አመልካች ጥቅምት 3 ቀን 2007 / በተፃፈ የሰበር አቤቱታ በዕለቱ አመልካች ምርት ባለማምርቱ ኪሳራ እንደደረሰበት ተረጋግጧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአመልካች ምስክሮች ቃል ተዓማኒነትና ክብደት በአግባቡ ሳይመዝን ስንብቱ ህገ ወጥ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ ተጠሪዎች ጥር 12 ቀን 2007 / በተፃፈ መልስ ተጠሪዎች ህገወጥ አድማ ሰራተኛ ያነሳሳን ስለመሆኑ በማስረጃ እንዳላስርዳ በማረጋገጥ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት የሌለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ አመልካች የካቲት 5 ቀን 2007 / የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

4.    ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪዎችን ከስራ ያስናበተው ከህግ አግባብ ውጭ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ የህግ መሰረት አለው? ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5.    ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ፍሬ ጉዳይ የማጣራት ማስርጃ የመመርመርና የመመዘን ስልጣኑን በመጠቀም የደርሰበትን የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ መመልከት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ አመልካች ህገ ወጥ አድማ ተደርጓል በሚልበት ቀን ፣ የቦነስ ክፍያ እንደማይከፍል ማስታወቂያ በመለጠፍ ፣ የድርጅቱ ሰራተኞች ለምን ቦነስ አይከፈለንም? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ፣ አመልካችም በሰራተኞች ጥያቄ ምላሽ በመስጠትና ሰራተኞችን በሁለት ከፍሎ ያነጋገረ መሆኑን ፣ አመልካች ሰራተኞችን በሚያነጋግርበት ጊዜ ተጠሪዎች ፣ መብታችን ይከበር በማለት መናገራቸውን ፣ ከዚህ ውጭ ተጠሪዎች የፈጸሙት ፣ ተግባር የሌለ መሆኑንና አንደኛ ተጠሪ ወደ ስራ የገባችው ዘግይታ እንደሆነ አመልካች በማስረጃ የተረጋገጠ ፍሬ ጉዳይ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና ስህተት በይግባኝ የመመርመርና የማረም ስልጣኑን በመጠቀም የደረሰበት የፍሬ ጉዳይና የማስርጃ ምዘና መደምደሚያ ያሳያል፡፡

6.    ይህንን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የደረሰበትን የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያን አመልካች ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የምስክሮችን ቃል ተአማኒነትና ክብደት ሲመዝን ፈጽሞታል የሚለውን ስህተት በሰበር የማየትና የማረም ስልጣን ለዚህ ሰበር ችሎት በህገመንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3() እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 አልተሰጠውም፡፡ በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የደርሰበትን የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ ዕውነት ነው ብለን በመቀበል ተጠሪዎች አመልካች ሰራተኞች በሁለት ቡድን ከፍሎ ሲያወያይ መብታችን ይከበር በማለት ሀሳባቸውን መግለፃቸው ወይም መናገራቸው የህገወጥ የስራ ማቆም አድማ መሪና የረብሻና የሁከት መፍጠር ሙከራ ነው ተብሎ ተጠሪዎችን ያለማሰጠንቀቂያ ከስራ ለማሰናበት የሚያበቃ ምክንያት መሆኑን አግባብነት ካላው የህግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

7.    ሰራተኞችን አመልካች ቦነስ ክፍያ ስለማይከፈልበት ምክንያት በሁለት ከፍሎ በሚያነጋግርበት ወቅት ተጠሪዎች መብታችን ይከበር የሚል ንግግር መናገራቸው ህጋዊ መብታችን ነው የሚሉት የቦነስ ክፍያ እንዲከፈላቸው ሀሳባቸውን የገለጹ መሆኑን እንጅ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1() መሰረት በአሰሪው ንብረት ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው በማናቸውም ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት የማድረስ ጥፋት የፈፀመ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ አንድ አሰሪ ሰራተኛው ህጋዊ የመብት ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት የስራ ውሉን የሚያቋርጥ ከሆነ ህገወጥ ተግባር እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 26(2) ) ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪዎችን ከስራ ያስናበተው ከህግ አግባብ ውጭ ነው በማለት አመልካች ለተጠሪዎች የካሳ ክፍያ የስንብት ክፍያና የማስጠንቀቂያ ክፍያ እንዲከፍል የሰጠው ውሳኔ ከላይ የጠቀሳቸውን የህግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገና መሰረታዊ የህግ ስህተት የሌለው ነው በማለት ወስነናል፡፡

1.    የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139262 ሀምሌ 30 ቀን 2006 / የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል፡፡

2.    በዚህ ፍርድ ቤት ህዳር 15 ቀን 2007 / የሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል ይፃፍ፡፡

3.    በዚህ ፍርድ ቤት የወጣውን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

መዝገበ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ

 

ማይነበብ የአመስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡